‹‹ይህ የብዙ ሀገሮች ታሪክ ነው፤ የኃይለሥላሴዋ እና የመንግሥቱ ኃይለማርያምዋ ኢትዮጵያ፣ የዚያድባሬዋ እና የመንግሥት የለሽዋ ሶማሊያ፣ የሱዳን…፡፡ ይህ የብዙ ድርጅቶች ታሪክ ነው፤ የ UNICEF, UNHCR, ICRC, LIVING BIBLES INTERNATIONAL, ሕያው ተስፋ ሬዲዮ፣ ብርሃን መጽሔት፣ WORLD VISION INTERNATIONAL... ፡፡ ደግሞም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ታሪክ ነው - የወንዶችና የሴቶች፣ ሕፃናትና ታዳጊዎች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች፣ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች… ወዘተ፡፡››
‹‹የምድረ በዳው እረኛ›› በሊሻን አጎናፍር፤ 2013 እ.ኤ.አ
* * *
‹‹የሞቱና የደረሱበት ያልታወቁ ሲቪሊያን የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ አንድ መቶ አርባ ሺህ ሲደርሱ፣ በጦሩ በኩል ደግሞ ወደ አስራ አምስት ሺህ ገደማ ይጠጋል፡፡ አጠቃላይ አሀዙ ከአንድ መቶ አምሳ ሺህ በላይ ሆነ ማለት ነው፡፡ በእጃቸው የገባውን ሁሉ ዘርፈዋል፣ የቻሉትንም ያህል አጥፍተዋል፡፡ ምን አልባት የተውት ነገር ካለም ያው ከእንግዲህ የእኛው ነው በሚል ሒሳብ ብቻ የተደረገ ነው፡፡ ያመለጠው አምልጦ፣ በምርኮኛነት የተያዘው ደግሞ ከስድስት ሺህ በላይ (ሲሆን)፤ ከዚህ ውስጥ ወደ አገሩ የተመለሰው 3508 ብቻ ነው፡፡››
‹‹የኛ ሰው በሶማሊያ እስር ቤት›› በጥላሁን አትሬሶ፤ 2004 ዓ.ም
* * *
‹‹… በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ እኔም ሆንኩ አብረውኝ የታሰሩት ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የመከራ የሥቃይ ውርጅብኝ በሕሊናችንና በአካላችን ላይ ደርሶብናል፡፡ እያንዳንዱ ቅጽበት ረዥም የፍዳ ዝግመት ሆኑብን፤ ለከባድ የጉልበት ሥራ ተዳረግን፤ በረኃብ፣ በጥማትና በርዛት ተጎሳቆልን፡፡ በሕፃናትና በእናቶች፣ በደካማ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች እንዲሁም በወጣት ሴቶችና ወንዶች፣ የታመመ እንኳን ሳይቀር፣ ይህ ነው የማይባል የጭቆና ቀንበር በሁላችንም ላይ ወደቀብን፡፡ ኢ-ሰብአዊ በሆነ ‹የሕይወትና ሞት› ጥያቄ ተፈተንን፡፡ ብዙዎች ተሸነፉ፡፡ የሞትን ሞት ተቀበሉ፡፡ ሬሳቸው እንደውሻ ሬሳ በየጥሻው ተጣለ፡፡ ይህን አልፈን ለእናት ሀገራችን የበቃነው፤ የማይሽርና የማይረሳ የግፍ አሻራ ወይ በሕሊናችን ወይ በአካላችን ላይ ደርሶብን ነው፡፡››
ከ‹‹የት ነው ?›› በከበደች ተክለአብ፤ 1983 ዓ.ም
* * *
ከላይ የቀረቡት ቅንጭቦች፣ በ1969 ከተከሰተው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ጋር በተያያዘ፤ በተለያየ አጋጣሚ፣ ቦታና ሁኔታ ለእስር የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን፣ የእስር ዘመናቸውን ማዕከል በማድረግ ከታተሙ ሦስት መጻሕፍት የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሁለተኛውና ሦስተኛው ቅንጭቦች፣ በጠላት እጅ ተማርኮ ‹‹ታሳሪ›› መሆን ያስከተለው ስቃይ ምን እንደሚመስል ያሳያሉ፡፡
ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ
የመጀመሪያው ቅንጭብ የተወሰደው፤ ከታሳሪዎቹ አንዱ ከነበሩት የዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ የሕይወትና የሥራ ታሪክ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ሀገራዊና ዓለማቀፋዊ በርካታ ታሪኮች የተሰነዱበት ቢሆንም፤ የእኔ ትኩረት በዚያ የመከራ ዘመን ለ‹‹ታሳሪ›› የመወገን ስሜት፣ ፍላጎትና ድጋፍ በመጽሐፉ በምን መልኩ ተግባራዊ እንደሆነ በወፍ በረር ለማስቃኘት ብቻ ነው፡፡ በጠላትነት በሚተያዩ ሀገራት በሚገኙ እስር ቤቶች፤ ከ‹‹አሳሪ››ው ወገን ያሉ ሰዎች ለ‹‹ታሳሪ››ዎች ሰብአዊነት ተሰምቷቸው፣ አዝነው፣ አርቀው አስበው እና ነግ በእኔ ብለው የሚፈጸሙት መልካም ተግባር ውስን ቢሆንም፤ ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ ‹‹ዕድለኛ ናቸው›› በሚያሰኝ መልኩ በጎ ነገር መፈጸም የሚያስደስታቸው የ‹‹አሳሪ›› ወገኖች ቅርባቸው ነበሩ፡፡
በ368 ገጾች የተቀነበበው ‹‹የምድረ በዳው እረኛ›› መጽሐፍ ደራሲ የባለታሪኩ ባለቤት ወ/ሮ ሊሻን አጎናፍር ሲሆኑ፤ ደራሲዋ በተለያዩ ተቋማትና ጊዜያት በሕትመትና ኤሌክተሮኒክስ ብዙኃን መገናኛዎች በጋዜጠኛነት ማገልገላቸው፤ መጽሐፉ በያዘው አስደማሚ ታሪክ ብቻ ሳይሆን፤ በስነ ጽሑፋዊ የአቀራረብ ውበቱ ከጀመሩት የማይለቁት እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ደራሲዋ የዕለት ማስታወሻ (diary) የመያዝ ልምድ ያላቸው ይመስላል፡፡ ያ ልምዳቸው ዛሬ ላይ ሆነው ስለትላንት ለመጻፍ በእጅጉ እንደረዳቸው ይታያል፡፡
ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ እንደማንኛውም የሰው ልጅ የመወለድ፣ የማደግ፣ የመማር፣ ማንነትንና መክሊትን ፈልጎ የማግኘት፣ ትዳር መስርቶ ቤተሰብ የማፍራት ሂደቶችን አልፈው፤ ተምረው በተመረቁበት የሕክምና ሙያ፤ ሀገርና ሕዝባቸውን በምሥራቅ ኢትዮጵያ ቀብሪደሃር ሆስፒታል ተመድበው በማገልገል ላይ እያሉ ነበር፤ በሶማሊያ ወታደሮች ተማርከው ወደ ወህኒ የተጋዙት፡፡ በዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴና በቤተሰቦቻቸው ታሪክ ውስጥ ከሚያስገርሙ በርካታ ገጠመኞቹ መሐል፤ ባለታሪኩ ለእስር በተዳረጉበት ዕለት የሆነው ነገር አንዱ ነው፡፡
‹‹ሐምሌ 17 ቀን 1969 ዓ.ም የቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ ተወለደች - በናዝሬት፡፡ በዚያው ዕለት የሊሻን አያት ሞቱ - በዚያው ቤት፡፡ በዚያው ዕለት ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ ከብዙ ሺህ ኢትዮጵውያን ጋር ተማረከ፤ በሶማሌ መንግሥት ጦር - በሕክምና ከሚያገለግልባት ከቀብሪደሀር፡፡››
አማርኛ ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ ዐባላት ጭምር በተካተቱበት የሶማሊያ ወታደሮች፣ ከቀብሪደሀር ሆስፒታል ተማርከው የተወሰዱት ምርኮኞች፤ የመጀመሪያ ማረፊያቸው የሆነው ‹‹ኤል ሃር›› በምትባል ከተማ ነበር፡፡ ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ የሕክምና ባለሙያ መሆናቸውም ጭምር አስተዋጽኦ አድርጎላቸው፤ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ከ‹‹አሳሪ››ው ወገኖች በኩል አክብሮትና ድጋፍ ማግኘት የጀመሩት ወዲያውኑ ነበር፡፡
‹‹ጫካ ውስጥ የገጠሙት ሁለት የሶማሌ የሕክምና ባለሙያዎች ክብር አሳዩት፡፡ አንደኛው ‹ልጅህና ነፍሰ ጡር ሚስትህ አዲስ አበባ በመሆናቸው ደስ ሊልህ ይገባል› ሲለው ሌላኛው ‹… እኛ ልንለቅህ እንችል ነበር ግን ጦርነት ጦርነት ነው ምን ይደረጋል፡፡ እዚህ ቁስለኞቹንና የጦር ጉዳተኞችን ማከሙ እምብዛም ያለ ሥራ አያስቀምጥህም፡፡ ትልቅ የሐኪም እጥረት አለብን… › ›› ብለው በአንጻራዊነት በክብር ሊባል በሚችል መልኩ ለእስረኛው ሐኪም አቀባበል አደረጉ፡፡
ከቀብሪደሀር ሆስፒታልና ከአካባቢው የተማረኩ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ ማረፊያቸው ከነበረው ‹‹ኤል ሃር›› በመቀጠል ሁለተኛ ማረፊያቸው ወደሆነው ‹‹ደናን እስር ቤት›› ሲወሰዱ፤ ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴን ከተቀበሉት አንዱ ‹‹አንተ የኦጋዴን አውራጃ ለቀህ ወደ ቤተሰቦችህ ገና ድሮ መሄድ ነበረብህ›› ብሎ ሀዘኔታውን ለመግለጽ አልዘገየም፡፡ በዚያ ስፍራም ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ በሙያቸው ኢትዮጵያውያንንና ሶማሌዎቹን ማገዛቸውን ቀጠሉ፡፡
ለወህኒ ቤቱ የወታደር ቀለብ የሚያቀርቡ አንድ ሶማሊያዊ ነጋዴ ስላሳዩት የሰብአዊነት ተግባርም በመጽሐፉ የሚከተለው ምስክርነት ቀርቧል፤ ‹‹ነጋዴው የጥበቡን ታሪክ ከሰማ በኋላ ‹ከዛሬ ጀምሮ አንተ ልጄ ነህ! በየዕለቱ ሁለት ኪሎ ስኳር፣ አንድ ሊትር ወተት፣ አንድ ኪሎ ስጋ፣ ሰላጣ፣ ቲማቲም... ሩዝ ፓስታ፣ ዘይትና ሳሙና የመሳሰሉትን (ደግሞ) በየሳምንቱ እልክልሀለሁ› አሉት፡፡
በ1969 ዓ.ምቱ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጦርነት፣ ለእስር ተዳርገው ወደ ሶማሊያ ስለተጋዙት ኢትዮጵያውያን ‹‹ይሙቱ ይኑሩ›› ለማረጋገጥ ቤተሰቦቻቸው በብዙ ደክመዋል፡፡ የዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ ባለቤት ወ/ሮ ሊሻን አጎናፍርም ከእነዚያ አንዷ ሆነው ብዙ ለፍተዋል፡፡ ወ/ሮ ሊሻን ለፍለጋቸው ምንም ፍንጭ ከማግኘታቸው በፊት ግን ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ ከ‹‹አሳሪ››ው በኩል ባለ ደጋፊያቸው ይህንን ይህንን መረጃ ሰምተው ነበር፡፡
‹‹ ‹ሚስትህ ለዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ያቀረበችው ጥያቄ ወደዚህ ደርሷል› አለው፤ ቀጥሎ ‹በእርግጥ የባለቤትህ ጥያቄ ‹ቀብሪደሃር ሆስፒታል ይሰራ የነበረው ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ በሶማሌ መንግሥት እጅ መኖር አለመኖሩ ይጠየቅልኝ› የሚል ቢሆንም የሶማሌ መንግሥት ግን ለጥያቄዋ መልስ መስጠቱን ላረጋግጥልህ አልችልም፡፡ ሆኖም ግን አግባብ ባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት በኩል እየፈለገችህ መሆኑን መረዳቴ ደስ ስላለኝ ነው ልነግርህ የመጣሁት› አለው፡፡›› በዚህ መልኩ ትብብር ያደርጉ የነበሩት ሶማሊያውያን ሕክምና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ባለከፍተኛ ማዕረግ ወታደሮችም ይገኙበት ነበር፡፡
በዚህ ምክንያት ‹‹በሶማሊያ በምርኮ ካሉት ኢትዮጵያውያን በሙሉ በጥሩ ሁኔታ ያለ እሱ ብቻ ነው›› የተባለላቸው ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ፤ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ሊሻን አጎናፍር ጋር፤ በአንድ የሶማሊያ ጄኔራል አማካይነት፤ በሚስጥር ደብዳቤ የመላላክ ዕድል ሁሉ አግኝተው ነበር፡፡ የደብዳቤ ልውውጡ ግን ጥብቅና በኮድ መግባባት ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ከ‹‹አሳሪ››ዎቹ ወገን በስውር ብቻ ሳይሆን በግልጽ ኢትዮጵያውያኑን የመርዳት፣ የመደገፍና የመቆርቆር ስሜት እንደነበር ማሳያ ሆነው የቀረቡ ምስክርነቶችም አሉ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ እስረኞች በሶማሊያ እስር ቤቶች ከወላጆቻቸው ጋር ለእስር የተዳረጉ ልጆች ለማስተማር ለሚያደርጉት ጥረት፤ ‹‹የሶማሊያ ወታደሮች ተማሪዎቹ መጻሕፍት እንዲያገኙ›› ያደርጉት የነበረው ትብብር አንዱ ነው፡፡ በወቅቱ የሶማሊያ ወህኒ ቤቶች አጠቃላይ ዳይሬክተር የነበሩት ጄኔራል እስማኤል አህመድ የሰጡት መመሪያ ደግሞ ከሰብአዊነትም በላይ ታሪክን ማሳያና ማጣቀሻ ሆኖ የቀረበ ነበር፡፡
‹‹… ዛሬ ምርኮኛ ሆነው በእናንተ እጅ የሚገኙት ሰዎች በሀገራቸው የተከበሩ ሰዎች መሆናቸውን አትርሱ፡፡ በሁለት ሀገሮች መካከል በሚሆን ጦርነት ሳቢያ ሰዎች ምርኮኛ ይሆናሉ፡፡ ኢትዮጵያና ሶማሊያ እርቅ ቢፈጥሩ ነገ ከእነዚህ መኻል በሹመትና በሥራ ወደ እኛ ሊመጡ ይችላሉና በኋላ የምናፍርበት ነገር አናድርግ… ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረራት ጊዜ ከማረካቸው ምርኮኞች መኻል አንዱ አቶ ከተማ ይፍሩ የታሰሩት ደናን እስር ቤት ነበር፡፡ በኃይለሥላሴ ዘመን አቶ ከተማ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ወደ ሶማሊያ ለስብሰባ መጡ፡፡ መጎብኘት የፈለጉት የመጀመሪያ ቦታ፣ ጣሊያን በምርኮኝነት አስሯቸው የነበረበትን የደናን ወህኒ ቤትን ነበር፡፡ ስለዚህ እነዚህም ነገ በምን ስልጣን ወደ አገራችን ተመልሰው እንደሚመጡ ስለማናውቅ በጥንቃቄ ልንይዛቸው ይገባል፡፡››
በመጨረሻ የሆነውም ይኸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሶማሊያ እስር ቤቶች ተፈቱ፡፡ ዶ/ር ጥበቡ ኃይለሥላሴ የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ ሆነው በተለያዩ ሀገራት ዞረው ሲያገለግሉ በዩኒሴፍ (UNICEF) ስር ሆነው ‹‹መንግስት አልባ›› በምትባለዋ በሶማሊያ ለሁለት ዓመት አገልግሎት ሰጡ፡፡ ‹‹የምታመልከው አምላክ ቅንነትህን አይቶ ዛሬ አንተን ለዚህ አብቅቶሃል፡፡ እባክህ የኩሊነት ሥራ እንኳ ቢሆን ፈልግልን›› ለመባልም በቁ፡፡
ከአዘጋጁ
ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡
Monday, 25 November 2024 07:17
Published in
ህብረተሰብ