Saturday, 23 November 2024 20:31

የዲጂታል ኢትዮጵያ ተስፋዎች!!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የ“ENJOY AI” አገር አቀፍ የመጨረሻ ውድድር አሸናፊዎች ተሸለሙ

• አሸናፊዎቹ በቻይና በሚደረግ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ


ቦሌ መድሃኒያለም ወረድ ብሎ በሚገኘው ቤስት ዌስተርን ፐርል አዲስ ሆቴል፣ 11ኛ ፎቅ ላይ በተሰደረው አዳራሽ፣ ከወትሮው ለየት ያሉ እንግዶች ታድመዋል፡፡ አህጉራዊ ጉባኤ ላይ ለመካፈል የመጡ እንግዶች አይደሉም፡፡ ኢትዮ ሮቦቲክስ ባዘጋጀው የ2024 “ENJOY AI” አገር አቀፍ የመጨረሻ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የተገኙ ታዳጊዎች ናቸው - የዲጂታል ኢትዮጵያ ተስፋዎች የሚለው ይገልጻቸዋል፡፡

የሮቦ ሮቦቲክስ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰናይ መኮንን ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤ታዳጊዎቹ በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ በኮዲንግ ስኪልስ ቻሌንጅ ነው የተወዳደሩት፤ በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑት በቅርቡ በቻይና በሚደረገው ዓለማቀፍ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡

በውድድሩ ላይ ከተሳተፉት የታዳጊ ቡድኖች መካከል ቲም ናይል፣ ቲም አልፋ፣ ቲም ዊነርስ፣ ቲም ላየንስ፣ ቲም ኤግል፣ ቲም አቢሲኒያና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

የውድድሩን አሸናፊዎች ለመለየት በታዳጊ ቡድኖቹ መካከል እልህ አስጨራሽ ፍልሚያና ፉክክር መደረጉን በአካል ተገኝተን ታዝበናል፡፡ ታዳጊዎቹ ስፔስ ትራቭሊንግ፣ ጋላክቲክ ዲፌንስ ባትል እና ክሎዚንግ ሰረሞኒ ኦቭ ስፖርትስ በተሰኙ ውድድሮች ለሦስት ዙር ተወዳድረዋል፡፡

በመጨረሻም፣ ከየዘርፉ ከ1ኛ እስከ 3ኛ የወጡ አሸናፊዎች የወርቅ፣ የብር፣ የነሓስ ሜዳልያና የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተሸልመዋል፡፡ የወርቅ ተሸላሚዎቹ ሦስት ቡድኖች ከዚህ በታች ቀርበዋል፡-

• ቲም ኤግል -በ120 ነጥብ በክሎዚንግ ሰረሞኒ ኦቭ ስፖርትስ

• ቲም ስፓርታ - በ630 ነጥብ በስፔስ ትራቭሊንግ ዘርፍ

• ቲም ናይል - በ100 ነጥብ በጋላክቲክ ዲፌንስ ዘርፍ

ለአሸናፊዎቹ የወርቅ ሜዳልያ የሸለሙት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትሩ ተወካይ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮ ሮቦቲክስ ከወትሮው ውድድር በተለየ የኤአይ እና ዲጂታል ስኪል አቀላቅሎ መምጣቱን ጠቅሰው፤የድርጅቱ መሥራች አቶ ሰናይ ላደረገው ወደር የለሽ ጥረትና ትጋት አመስግነዋል፡፡

አክለውም፤ ውድድሩ ሰፋ ብሎ እንዲካሄድና ተደራሽ እንዲሆን ለኢትዮ ሮቦቲክስ እገዛችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

 

 

Read 813 times