Saturday, 23 November 2024 20:28

“የጃርት እናት፤ ልጆችሽን እንዴት ትልሻቸዋለሽ?” ቢሏት “እንደየዕድሜያቸው” አለች

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አንድ ንጉሥ ከሦስት ልጆቻቸው ለአንደኛው መንግሥታቸውን ለማውረስ አስበዋል፡፡
ልጆቹ ግን “እኔ ልውረስ፣ እኔ ልውረስ” እያሉ አስቸገሯቸው፡፡ ስለዚህ አውጥተው አውርደው ካጠኑ በኋላ ልጆቻቸውን ጠርተው፤
“ከሦስታችሁ ማንኛችሁ በትረ ሥጣኔን ይውሰድ?” ሲሉ ጠየቁ፡፡ በመጀመሪያም በትምህርቱ፣ በዕድሜው ትልቅ የሆነው የበኩር ልጃቸው እንዲመልስ ዕድል ሰጡ፡፡
የመጀመሪያ ልጅም፣
“ለእኔ ይገባኛል”አለ፡፡
“ለምን?”
“እኔ የበኩር ልጅ ስለሆንኩና፤
በመጀመሪያ ት/ቤት እንዲከፈት አድርጌአለሁ፡፡ አገሬን ጠቅሜአለሁ” አለ፡፡ ቀጥለው ሁለተኛውን ልጅ ጠየቁት፤ እሱም፤
“ለእኔ ይገባኛል፡፡ ምክንያቱም ባለፈው ጠላት አገራችንን ሲወር ሰበብ ፈልጎ በብዙ መንገድ ሲተነኩስ ዝም ማለት ነው፤ ብዬ ምክር ለግሼዎ፤ ለማሸነፍ ችለናል፡፡ አገራችንን ያዳንኩ እኔ ነኝ” አለ፡፡
ሦስተኛው ልጅ እድል ተሰጠው፡፡ እሱም፤
“ባለፈው ጊዜ መንግሥታችን በዕዳ ተይዞ ሳለ የሀገራችንን ወርቅና የከበረ-ደንጊያ ሁሉ ልሸጠው ነው ሲሉ፣ እኔ ግዴለም የዘንድሮን አዝመራ በትዕግሥት እንጠብቀው” ብዬ፤ አዝመራችን ተሸጦ ዕዳችንን ከፈልን፡፡ ሀገሬን ያዳንኩ እኔ ነኝ” አለ፡፡
ንጉሡ የሦስቱንም በጥሞና ካዳመጡ በኋላ፤
“ልጆቼ ጥንት ልዑል ሳለሁ አንድ መምህር ነበሩኝ፡፡ የበሰሉ፣ አዋቂ የተባሉ ናቸው፡፡ አንድ ቀን ‹መምህር ሆይ፤ ዕድሜዬ እየጨመረ አባቴም እየደከሙ ናቸውና፣ ንጉስ ለመሆን የሚያስፈልጉኝን ሦስት ነገሮች ይንገሩኝ› ስል ጠየቅኋቸው”
መምህሩም ጥቂት ካሰላሰሉ በኋላ፤
“ልዑል ሆይ ከሁሉ አስቀድሞ፤ ሌላው የማይቀማዎን ንብረት ይስጥዎ” አሉኝ፡፡
እኔም፤ “ሌላው የማይነጥቀኝ ንብረት ምንድን ነው?” ስል ጠየቅኋቸው፡፡
መምህሩም፤ “ዕውቀት ነው” ሲሉ መለሱልኝ፡፡ ቀጠሉናም
“ሁለተኛው ደግሞ፤ ሁሉን የሚፈታ ኃይል ይስጥዎ” አሉኝ፡፡
“ሁሉን የሚፈታ ኃይልስ ምንድነው?” አልኳቸው፡፡
“ብልሃት፣ ዘዴ” አሉና መለሱ፡፡
“እሺ ሦስተኛው ምን እንደሆነ ይንገሩኝ?” አልኳቸው፡፡
መምህሩም፤ “አገሩን በሙሉ ለመግዛት የሚበቃ የማያጠራጥር አቅም ይስጥዎ፡፡”
እኔም፤ “ይህ የማያጠራጥር አቅም ምን ሊሆን ይችላል? ይግለጡልኝ?” አልኳቸው፡፡
መምህሩም፤ “ትዕግሥት፤ ትዕግሥት ነዋ!” አሉኝ፡፡
ይህን የመምህሩን ታሪክ ከተናገሩ በኋላ ንጉሡ ወደ ልጆቻቸው ዞረው፤
“አያችሁ ልጆቼ አገር ለማስተዳደር ዕውቀት፣ ብልሃትና ትዕግሥት ያስፈልጋል፡፡ እናንተ ደግሞ አንዳችሁ የዕውቀት፣ አንዳችሁ የብልሃት፣ አንዳችሁ የትዕግሥት፣ ባለቤት ናችሁ፡፡ ችሎታችሁን ካላስተባበራችሁ ሀገር አታስተዳድሩምና፣ አስቡበት” ብለው ሸኟቸው፡፡
***
ሀገራችን አዋቂ፣ ብልህና ታጋሽ መሪ ትፈልጋለች፡፡ ሁሉም ተሰጥዖዎች በአንድ መሪ ውስጥ ተሟልተው የማይገኙ ሊሆኑ ይችላሉና አቅምን አስተባብሮና አዋዶ መጓዝ ግዴታ ይሆናል፡፡ ህብረ-ኃይል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ህብረ-ቀለም ቀለም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ያለ ዕውቀት ከዓለም ጋር መጓዝ አይቻልምና አዋቂዎችን ማሰባሰብ የግድ ነው፡፡ ያለ ብልሃት እንኳን ማህበረሰብን ቡድንን መምራት አይቻልምና፤ የቅርብ የቅርብ ችግርን መፍቻና የሩቅ ኢላማን መምቻ ብልሃት ማዘጋጀት የዕለት-ሰርክ ተግባሬ ብሎ መያዝ ያሻል፡፡ ማናቸውንም ተግባር ዐይኑ ሊበራ ቃል- እንደተገባለት ሰው “ዛሬን እንዴት አድሬ” በሚል ለመከወን ማሰብ “ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ” ያደርጋል፡፡ ከሚኬድበት መንገድ ሁሉ መድረሻ ላይ ሀገርና ህዝብ መኖሩን አለመርሳት፤ በሁሉም ወገን ልብ ላይ መታተም አለበት፡፡ “ከዚህ ሁሉ ትግልና ፍትጊያ በኋላ በሚዶው መጀመሪያ የሚያበጥርበት ማነው?” ተብለው እንደተጠየቁት መላጦች ላለመሆን፤ ዓላማንም ሆነ ዒላማን ልብ-ማለት መቼም ቢሆን ወሳኝ ነው፡፡
ወደ ሰላም የሚወስዱንን መንገዶች ሁሉ ከአውራ- ጎዳና እግር- መንገድ ድረስ እሾ ካማም ሆኑ ሣር-ሜዳ፤ በራስ ድርድርም ይለቁ በዓለም ሽማግሌ፤ በጥንቃቄና በብሩህ መነጽር ማየት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በትዕግሥትም እስከ ኬላው ድረስ ለመጓዝ መቁረጥ መልካም ነገር ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ሲታሰብ፤ እንኳ እንደኛ በዳዴ ላይ ላሉ አገሮች፣ ብዙ በተለማመዱትም ዘንድ ከቀድሞው አስተሳሰብ መላቀቅና የቀድሞውን ጥቅም አጣለሁ የማለት ራስ-ወዳድነት፤ ያለ የነበረ ነገር ነው፡፡ ጉዞውን ረዥም የሚያደርገውም የአዲሱ አለመለመድና ከአሮጌው ለመላቀቅ ያለመቻል አባዜዎች ናቸው፡፡ ከዚህ አልፎ ተርፎ ለየፖለቲካ ተግባሩ የሚለጠፍ ቅጽል ስም ነገሮች ከማወሳሰብና ከማክረር ያለፈ ጠቀሜታ አይኖረውም፡፡ ይህን ስላልክ ወይም ስላደረግህ የዚህ ወይም የዚያ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም አመለካከት ደጋፊ ነህ የሚል አስተሳሰብ ጎጂነቱ አያጠያይቅም፡፡ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ነገሮች እልባት ባላገኙ ቁጥር አገር፤ እንደ ጃርቷ “ የጃርት- እናት፤ ልጆችሽን እንዴት አድርገሽ ትልሻቸዋለሽ?” ስትባል፤” እንደየዕድሜያቸው” ከማለት ያለፈ መልስ የላትም፡፡ ሀገርን ለማገዝ አሁንም ዕውቀት፣ አሁንም ብልሃት፣ አሁንም ትዕግሥት ያስፈልጋል፡፡

Read 719 times