Monday, 27 June 2011 16:12

የህብረ ቃሉ ምስጢር

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

ሊቃውንቶቹ ለምን እውቀታቸውን ደበቁን?... ለምን የስልጣኔው ድልድይ ተሰበረ? ስልጣኔ እንደነበረ ሐውልቶቹ ይመሰክራሉ፡፡ ሚስጢሩን መፍቻ ቋንቋ ይዘው የተቀመጡት ለምን ለኛ በጨለማ ለምንጓዘው መግባቢያውን አልሰጡንም?  ፕሮማቲየስ እንኳን በራሱ እጅ ያልሆነውን የአማልክት ንብረት ሰርቆ ለሰው ሰጥቷል፡፡ የእውቀት እሳቱን ከኦሊምፒያ አውርዶ ለሰው ለኩሷል፡፡ አማልእክቶቹን ለመበቀል ቢሆን እንኳን ሰውን ጠቅሟል፡፡ ...የምድር ልሂቃን፤ ሰው ሆነው እሳታቸውን ለምን ሸሸጉን?  ለራሳቸውም እንዳይሞቁ፣ የበረደው የሰው ልጅን እንዳያሞቁም ንፉግ ሆነው፡፡ ...ብቻ የተደበቀ ሚስጢር አለ ይሉናል፡፡ ሚስጥሩን ሳያመሳጥሩን . . . ለምን

እንደምናከብራቸው ሳይነግሩን ፀደቁብን፡፡ ...የዋናውን ታቦት አምሳያ እንደበተኑት ዋናው እንዳይሰረቅ፤ የዋናውን ሚስጢር አምሳያም ..ሰም እና ወርቅ.. ብለው ቅኔ አስተማሩት ምንዝሩን፡፡ ግልፁን በመሸሸግ ሽሽጉን እንዳንገል አጠሩን፡፡ ቀላሉን ውስብስብ አድርገው በመቀኘት ..ከባዶ.. ውስጥ ..ምንምን.. በቋንቋ ትብታብ . . . ጠፈሩን ከእግረ ሙቅ ቀይጠው ሰጡን፡፡ በተምሳሌት ተሸብበን ዋናውን ከነአካቴው ዘነጋነው፡፡ መድሐኒት አዋቂው መድሐኒቱን ሳይነግረን በመቅረቱ በሽታችን በዛ፡፡ ቋንቋውን ደብቆን መዘላበዳችን በረታ፡፡ የባቢሎን ታሪክ የእኛም ታሪክ ነው፡፡

 

በሰው እና በፈጣሪ መሀል ያለው መሰላል ከሚስጥር የተሸመነ ነው፡፡ ሚስጥሩን የደበቀ ሁሉ ፍጡር እና ፈጣሪን ሆን ብሎ አስተጣጥቷል፡፡ አራርቋል፡፡ ለምንድነው የማይነግሩን መነሻችንን፣ ለምንድነው የማይጠቁሙን መድረሻችንን... ምንስ ቅኔ ያስፈልገዋል? ሰምና ወርቅ ድብቁን ለመግለ ካላገለገለ ምን ረብ አለው? ...እኛ በግል እያየን የማናየው፣ በግል እየተናገርን የማንግባባው፣ በግል እያለምን የምንስተው . . . የግል ድብቆች እያለን፤ ከኛ በላይ ምን ቅኔ ያስፈልጋል?( ሰምና ወርቅ እኛው ራሳችን ነን፡፡ የበቆሎውን ሽፋን ስንገሸልጥ ውስጡ ወርቅ ሳይሆን አንድ የእሸት ፍሬ የማይገኝብን፡፡ ህብረ ቃሉ ተሰውሮብናል፡፡ ሰው እና የሰው መሆንን ትርጉም ያዘለው ህብረ ቃል፡፡ ላቱ ተደብቆብናል፡፡ ለላቱ በመሰሰት፤ ላቱ እንዲያገለግለን የተበረከተልን እኛ ከአገልግሎት ውጭ ሆንን፡፡ ተረቶቻችን ሚስጢር ናቸው፡፡ ስንክሳሮቻችን ሽሽግ ናቸው፡፡ እንቁዎቻችንን በሰው ፊት ካልዘነጥንባቸው፣ ካላማርንባቸው አፈር ስር መቀበራቸው የዋጋቸው ተመን መግለጫ ይሆናል? በድህነት ያረረ መሬት ይዘን፤ ታሪክ የሚሰራ መድሃኒት እንደ ሬሳ ከአፈር በታች ቀብረናል፡፡ ስለ ትንሳኤ እየፎከርን መሞት የሁልጊዜ እጣ ፈንታችን ሆኗል፡፡ ...ትንሳኤን የሚጠብቅ የዋህ ነው? . . . ድብቁን ሳይሆን ግልፁን ቅኔ ፈትቶ እፎይ ያለ ነው፡፡ ...ሞቱን ተሸክሞ እፎይ የሚል ማነው፡፡ ርሀቡን፣ ድህነቱን፣ የአካል ስቃዩን፣ ጥላቻውን... ? . . . ያልሆነውን ለመሆን የተሸነፈ እፎይታ ነው፡፡ ...የራሱን የአስከሬን ሳጥን እድሜ ልኩን እያሰማመረ እንደሚሰራ ባለሞያ ህይወቱን ለሞት ለመሸጥ እድሜ ልክ የሚለማመጥ ሰባራ ልብ... እስኪሞት እና እስኪገነዝ ድረስ በህይወት ዘመኑ የተገነዘበትን የጨለማ ማቅ የማይለውጥ፡፡...

አውቃለሁ ፤ አዎ አውቃለሁ፤ የአላዋቂ ልብ እና የንፉግ እጅ አይፈለቀቁም፡፡ ሚስጥሩን የጨበጠበትን ሳይሆን ባዶውን በሰም እና ወርቅ ጨብጦ ግለ እንደሚሉኝ አውቃለሁ፡፡ ቀላሉን በከባድ ምትሀት አወሳስበው፡፡ ባዶ የጨበጠ እጅ ሲፈለቀቅም ባዶ ነው፡፡ ብዙ ባዶ እጆች በብዙ ከባድ ቅኔ ተጨብጠው ፍቺ ይፈልጋሉ፡፡ የእጅን ጭብጦ የሚዘረጋው ሳይሆን፤ የአስተሳሰብ ጭብጦን የሚፈታው ምስጢር ነው የሚያስፈልገን... የሊቃውንቶቹን ልብ ያራራልን... ተጨብጦ ተወልዶ ተጨብጦ የሚሞት ፍትህ የልባቸውን አይን ያብራ፡፡ ህይወታችንን አለመኖራችንን እንኳን አናውቀውም፡፡ የህይወት ዋጋ (ግብ)፤ የራስን አስከሬን ሳጥን ሰርቶ ጨርሶ፤ ሲጨርሱ ከእነ ቤተሰብ (ባል ሚስት እና ልጅ) አብሮ መከርቸም አይደለም፡፡ ...ዘር ወደ ኋላ ጥሎ ማለፍ የጥሎ አላፊውን ሬሳ ለመገነዝ ወይም ሚስማር መቺ ላለማጣት አይደለም፡፡ ለመሞት አይደለም ፍጭርጭሪቱ፤ ለመኖር ነው፡፡ አይን ለማልቀሻ ሳይሆን ለመመልከቻ ነበር አሰራሩ፡፡ሚስጢርን መስጠት ነው ሀጢአትነቱ? አለመስጠቱስ የቱ ላይ ነው ድቁ? እንቁን ለእርያ እንደመጣል ስለሆነ ነው ሚስጢር እና እውቀት ለሁሉም ይፋ የማይሆነው? ለማያከብር የተከበረውን እንደመስጠት፡፡ እንቁው እውነት የእርያው ከሆነ፤ አንዱ እሪያ ሊይዘው እና ሌላውን ከማግኘት ሊነፍገው አይችልም፡፡ እንቁ ያዥ ሊቃውንትም ይሁን ልሂቅ፡፡ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ እንቁውን ሁሉም ይጠቀምበታል፤ ካልሆነ ማንም አይጠቀምበትም፡፡ አንዳንድ ሰው ከሌላው የበለጠ እኩል አይደለም፡፡ ለሁሉም ይሆናል ሚስጢሩ፤ ወይንም ለማንም አይሆንም፡፡ ምንድነው አስፈላጊነቱ? ማናቸው እነሱ ማንስ ነን እኛ? የአንድ አባት እና እናት ልጅ ባንሆንም በአንድ የአለም ኳስ ላይ እስከነጠርን ድረስ የአንድ እውነት ልጆች ነን፡፡ ብቻውን የሚተርፍም ሆነ ብቻውን የሚጠፋ ማንም/አንዳችም የለም፡፡ እሪያው የተሰራው ዞሮ ዞሮ ከእንቁ ነው፡፡ እንቁውም ደግሞ ከእሪያ፡፡ አህያውም አንበሳ ነው፤ አንበሳውም አህያ፡፡ አዳኙ እና ታዳኙ የአደኑ ግብአት ናቸው፤ ወጣም ወረደ፡፡ሰሙም ወርቁን አይሸፍነውም በስተመጨረሻ፡፡ ወርቅ ፈላጊውም ሰምን ጨብጦ አይቀርም፡፡ በገሀነም የተጓዘውም በስተመጨረሻ በንግስተ ሰማይ በኩል ብቅ ማለቱ አያጠራጥርም፡፡ ልሂቅም በሞት እረፍቱ እንደ ደቂቅ ከአፈር ይደባለቃል፡፡ አፈርም ከስጋ፡፡ ሚስጥሩም በህይወት ካልተፈታ በሞት ይፈታል፡፡ሚስጥር ደባቂውም፤ ያወረሰው ለልጁ ብቻ ከሆነ፤ ያወረሰው ምስጢሩን ነው እንጂ ፍቺውን አይደለም፡፡ ፍቺውንም ቢሆን፤ በአንድ ሰው ላይ ብቻ ተፈትቶ በሌላው ላይ ግን እንደተቋጠረ ከቀረ፤ ፍቺው ሚስጢር ይሆናል መልሶ፡፡ ለብቻው እውቀትን የበላ ለብቻው በሞት ይበላል፡፡ የእውቀቱንም ትዝታ ከስጋው ጋር አብሮ ተጨምሮ፡፡

ድብቅ ማህበረሰቦች፣ የደም ምህላ ወንድማማችነቶች፣ ገደማት እና ገድል አፋኞች... እኛ የማናውቀው የተደበቅነውን ያህል ብናጣም፤ የጠፋንን ወይንም የተጋረደብንን ያህል ግን ፃድቅ ነን፡፡

 

 

Read 2500 times Last modified on Monday, 27 June 2011 16:29