Saturday, 14 July 2012 12:15

“ከድጡ ወደ ማጡ”

Written by  ጌታቸው አበበ አየለ
Rate this item
(0 votes)

ሃይማኖትን ብቻ ሳይሆን አንባቢንም መዳፈራቸውን ሳይ ምን ዓይነት ሰው ይሆኑ? አሰኝቶኛል፡፡ ይህን ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሐሳባቸውን በመቃወም ምላሽ ለሰጧቸው ሁለት ግለሰቦች የመልስ መልስ በሰጡበት በዚሁ “የምናደንቀው የአትሌቱን ብቃት ነው ወይስ ሃይማኖቱን” በሚል ርዕሳቸው ሥር እንዲህ ይላሉ፡፡ሰው ስለራሱ ብቻ ሳይሆን በእሱ ዙሪያ ስላሉት ነገሮችና ክስተቶች ሁሉ ለማሰብ፣ ለመመራመርና ምርምሩንም ከውጤት ለማድረስ የሚያስችል አዕምሮ የተቸረው ፍጡር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት የሆነ አስተሳሰብና አመለካከት አለው ማለት አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሣ በሰዎች መካከል የአስተሳሰብ፣ የፍላጎትና የአመለካከት ልዩነት ይኖራል፡፡

ምንም ዓይነት ልዩነት ይኑረው እንጂ ሰው ብቻውን መኖር አይችልም፡፡ ማኅበራዊ ፍጡር በመሆኑ ከአካባቢው ጋር የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና ባሕላዊ ግንኙነት መፍጠሩ የግድ  ይላል፡፡ ስለሆነም ሰው በአካባቢው ማኅበራዊ ሕግና ሥርዓት ተገዢ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ግንኙነቱ ውስጥ ታድያ የሌሎችን ሐሳብ የመካፈል ወይም የራሱን ሐሳብ የማጋራት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ እናም አንድ ሰው ለራሱ ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን አንድ ጉዳይ በጋዜጣ፣ በመጽሔት ወይም ባገኘው አጋጣሚ ወደ ሕዝብ ጆሮ ሊያደርስ ይችላል፡፡ ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ እሰየው ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ ግን የተላለፈው ሐሳብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝንና ትችትን የሚያስከትል ሊሆን ይችላል፡፡

እዚህ ላይ ነው የሰውየው ማንነት የሚታየው፡፡ ብልህ ከሆነ ትችቱን ተመልክቶ ራሱን እንደገና ይመረምራል፡፡ ከስሕተቱም ይማራል እንጅ ለምን ተተችሁ ብሎ አይቆጭም ግትር አመለካከት ያለው ሰው ከሆነ ግን “የእኔ ሐሳብ ለምን ይተቻል?” በማለት ያለ አስፈላጊ ጭቅጭቅ ውስጥ ይገባል፡፡

ለእንደዚህ ዓይነቱ ሰው ምሳሌ ሆነው ሊቀርቡ የሚችሉት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነፃ አስተያየት አምድ የሰኔ 9 ቀን 2004 ዓ.ም እትም ላይ “ፈጣሪ ያዳላል እንዴ?” በሚል ርዕስ ፅሁፍ ያቀረቡት አቶ ዓለሙ ከድር ናቸው፡፡

ይህ ጽሑፍ ያዘለው መልእክት የእምነት ተከታዮችን መብት የሚነካ መሆኑን በማስመልከት እኔ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢና ሌላ ግለሰብ በ23/10/04 በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አስተያየት ሰጥተናቸዋል፡፡

በጣም የሚገርመው ግን አቶ ዓለሙ ከድር የተሰጣቸውን አስተያየት ከቁብ ሳይቆጥሩ በ30/10/04 በወጣው አዲስ አድማስ “የምናደንቀው የአትሌቱን ብቃት ነው ወይስ ሃይማኖቱን?” በሚል ርዕስ ጭራሽ ከመጀመሪያው የባሰ ሐሳብ ይዘው ብቅ አሉ፡፡

መቼም ለምን ጻፉ የሚል አመለካከት የለኝም፡፡ ለሰዎች ጠቃሚ ያልሆኑ አመለካከቶች በጋዜጦች ወይም በመጽሔቶች ለምን ይቀርባሉም? አልልም፡፡ በእርግጥ ለቀረቡ አጉል አመለካከቶች ምላሽ ሳይሰጣቸው ከቀረ ጉዳታቸው የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡

በተረፈ ግን አሳሳች ሆነው ከሚቀርቡ ነገሮች ትምህርት ሊገኝባቸው ስለሚቻል መቅረባቸው አይከፋም፡፡ ጥሩ ነገር የሚታወቀው መጥፎ ነገር ሲኖር ነውና፡፡

ስለሆነም አቶ ዓለሙ ከድር ለራሳቸው ትክክል መስሎ የታያቸውን ሃሳብ ማቅረባቸው መብታቸው ነው፡፡ ተጠቅመውበታልም፡፡ ይሁን እንጂ ከፅሁፋቸው እንደተረዳሁት፡-

1ኛ. “ጥረት፣ እምነት (ሃይማኖት) እና ስብከት የሚሉት መጠሪያ ቃላት ትርጉምና አጠቃቀም አልገባቸውም፡፡ ወይም እያወቁ ሊያበላሹ ፈልገዋል፡፡

2ኛ. አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የሰዎችን እምነት ተጋፍተዋል፡፡

3ኛ. በፈጣሪ ማድላትና አለማድላት ላይ ውይይት እንዲደረግ የማይገባ ጥሪ አድርገዋል፡፡

አቶ ዓለሙ ከድር ደግመው ደጋግመው “ታዋቂ አርቲስቶችና አትሌቶች ሃይማኖታቸውን ይሰብካሉ …” በማለት በጽሑፎቻቸው ያነሣሉ፡፡

ለመሆኑ “ስብከት” የሚለውን ቃል ምን ዓይነት ትርጉም ቢሰጡት ይሆን ይህንን ያህል የተጠቀሙበት፡፡

ስብከት ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ማለትም አንድ ዓይነት የእምነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች በሚገኙበት ቦታ የሚደረግ የእምነት ትምህርት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚሰጠው በእዚያው በእምነቱ ባለሙያ (በቄስ፣ በዲያቆን፣ በፓስተር፣ በሼህ፣ … በመሳሰሉት) መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዋቂ አርቲስቶች፣ ስፖርተኞች፣ ደራስያን፣ ሠዓልያን ግን በእርሳቸው በአቶ ዓለሙ ከድር አመለካከት እንዴት የሃይማኖት ሰባክያን ሊሆኑ እንደቻሉ ግልጽ አይደለም፡፡

እናም ታዋቂ አርቲስቶች፣ ስፖርተኞች፣ ደራስያን፣ ሠዓሊያንና የመሳሰሉት ሁሉ በተፈጥሮ ያገኙትን ተሰጥዖ በጥረታቸው አዳብረውና አሳድገው በተሰለፉበት ሙያ ስኬታማ ሲሆኑ “ለዚህ ያበቃኝን እግዚአብሔርን፣ ጌታ ኢየሱስን፣ አላህን፣ …ወዘተ አመሰናግለሁ” ብለው መናገራቸው የሃይማኖት ስብከት ነው ማለት ተገቢነት አይኖረውም፡፡

አቶ ዓለሙ ከድር ሰኔ 09 ቀን 2004 ዓ.ም በጻፉት “ፈጣሪ ያዳላል እንዴ?” በሚለው ርዕስ ሥር በሠፈሩት ሐሳቦች ስንደነቅ በሰኔ 30/2004 ዓ.ም ደግሞ “የምናደንቀው የአትሌቱን ብቃት ነው ወይስ ሃይማኖቱን?” በሚል ርዕስ ሥር የሰነዘሯቸው ነጥቦች ጭራሽ የባሱ ሆነዋል፡፡ “ከድጡ ወደ ማጡ” ይሏል እንዲህ ነው፡፡

1ኛ. “የምናደንቀው የአትሌቱን ብቃት ነው ወይስ ሃይማኖቱን?” የሚለውን ጥያቄያዊ ርዕስ የሰጡትን ጽሑፋቸውን ያነበበ ሁሉ ሳይገረምበት አይቀርም፡፡ ለመሆኑ ይህ ጥያቄአቸው በተከታታይ ካስተላለፉአቸው ሐሳቦቻቸው ጋር መጣረሱ እንዴት አልታያቸውም? ዋናው ሐሳባቸው የታወቁ አርቲስቶች፣ አትሌቶች፣ ወዘተ “በጥረቴ ተሳካልኝ ብቻ ለምን አይሉም?...” በሚል ነጥብ ላይ የተመሠረተ እንደነበረ ለምን ዘነጉት ታድያ! ተደናቂዎችን ትተው ወደ አድናቂዎች ምን አምጥቶ ሰነቀራቸው? ከመገረም ሌላ ምን ይባላል!!

እንዲያው ለነገሩ አቶ ዓለሙ ከአድናቂዎች መሐል “…አይ! የእገሌ ሃይማኖት ሯጭ፣ አርቲስት፣ … አሸነፈ፡፡ የእገሌ ሃይማኖት ጎበዝ ነው፣ …” ሲባል ሰምተው ያውቃሉ? እኛ ግን የምናውቀው “..አይ! እገሌ እንዴት ዓይነት ሯጭ፣ አርቲስት፣ ደራሲ፣ … መሰላችሁ፡፡ እገሌ እኮ በእንደዚህ ዓይነቱ ተግባር ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ጎበዝ …ነው፡፡” ሲባል ነው፡፡

2ኛ. አቶ ዓለሙ ከድር በፈጣሪ ማድላትና አለማድላት ላይ ውይይት እንዲደረግ የጠሩት ጥሪ እጅግ! እጅግ! … ጥሩ አይደለም፡፡

ጥሩ ስለአለመሆኑም እሳቸው ራሳቸው ተመራምረው ይድረሱበት ከማለት ሌላ የምለው የለኝም፡፡ ከፈጣሪ ጋር ግን የሚያደርጉትን መጋፋት እዚያው ለራሳቸዉ ያድርጉት፡፡

3ኛ. ሃይማኖትን ብቻ ሳይሆን አንባቢንም መዳፈራቸውን ሳይ ምን ዓይነት ሰው ይሆኑ? አሰኝቶኛል፡፡ ይህን ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሐሳባቸውን በመቃወም ምላሽ ለሰጧቸው ሁለት ግለሰቦች የመልስ መልስ በሰጡበት በዚሁ “የምናደንቀው የአትሌቱን ብቃት ነው ወይስ ሃይማኖቱን” በሚል ርዕሳቸው ሥር እንዲህ ይላሉ፡፡

“…በእርግጥ አላስፈላጊ ስድብና ውግዘትም ጨምረውበታል፡፡ ያው! የተለመደ የአገራችን ባሕል ነው፡፡” ያሳዝናል፡፡ ከሁለቱ ግለሰቦች አልፈው የአገሪቱ ባሕል ስድብ መሆኑን ወረቀት ላይ ሲያሠፍሩ ሕሊናቸዉን እንዴት አልተሰማውም፡፡

እኛ የአገራችንን ሕዝብ ባሕል የምናውቀውና ዓለምም የሚያደንቀው በሰው አክባሪነቱ፣ በእንግዳ ተቀባይነቱና እርስ በርስ ተቻችሎ የመኖር ታሪክ ያለው መሆኑን ነው፡፡

እኔ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ባለፈው ባወጣሁት “ያላስፈላጊ ቁጭት” የተሰኘ ፅሁፌ ላይ አቶ ዓለሙ በሌላው ሰው እምነት ጣልቃ እንዳይገቡ አስተያየት ሰጥቻቸው ነበር፡፡ አሁንም “ከድጡ ወደ ማጡ” እየሔዱ ስለሆነ የጀመሩትን ያላስፈላጊ ጭቅጭቅ ቢተውት የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡

 

 

Read 2843 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 12:19