Saturday, 27 July 2024 21:43

ሁሉ ፈረስ ላይ ልውጣ ካለ፣ ገደሉን ማን ሊያሳይ ነው?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ “ሱካርና ወተት የልጆች ማሳደጊያ።” በሚለው ጽሁፋቸው፤ ስለ አንድ ሽማግሌ ሰውና ስለ አንዲት ልጅ በሚል፤ በመስኮብ የሚነገር አንድ ተረት እንዳለ ይናገራሉ።
በመስኮብ አገር ሦስት ሴቶች ልጆች ያሉት አንድ ሽማግሌ ነበረ። አንዲቱ በመልኳና በጥበብዋ እጅግ ስመ ጥሩ ናት፤ አንድ ቀን ወደ ገበያ ሲወጣ፡-
“ልጆቼ ሆይ፤ ከገበያ ምን ገዝቼላችሁ ልምጣ?” አላቸው። ሁለቱ ልጆቹ “ጌጥ ገዝተህልን ና” አሉት፡፤ አንዲቱ ግን፤ “እኔ ምንም አልፈልግም። ነገር ግን የምመክርህን ምክር ስማኝ” አለችው። ለጊዜው ነገሩ ከበደው፤ ነገር ግን ልጁ እጅግ ብልህ መሆኗን ያውቃልና “እሺ ይሁን ንገሪኝ” አላት። “ወይንማውን በሬ ወደ ገበያ አውጥተህ ስትሸጥ ዋጋ ንገረን ያሉህ እንደሆነ፣ የንጉሡን ግራ አይን አምጡና በሬውን ውሰዱ በላቸው” አለችው።
እርሱም በገበያ ተቀመጠና “የበሬውን ዋጋ ንገር?” ሲሉት፤ ልጁ እንደመከረችው፤
“የንጉሡን ግራ አይን አምጡና ውሰዱት” ይል ጀመረ።
ይህንም ወሬ ንጉሡ ሰሙና፤
“እጁን ይዛችሁ አምጡልኝ!” ብለው አዘዙ።
ሽማግሌውም በቀረበ ጊዜ “ንጉሥ ሆይ፤ እንደዚህ ያደረገችኝ ልጄ ናትና ማሩኝ እያለ ይለምን  ጀመረ። ንጉሡም ይህን በሰሙ ጊዜ “ሔደህ ልጅህን አምጣትና እምርሃለሁ” አሉት።
ሽማግሌው እያዘነና እየተንቀጠቀጠ ሄዶ ልጁን ይዞ ወደ ንጉሡ ቀረበ። ንጉሡም ልጅቱን ባዩዋት ጊዜ፤ “ለበሬው ዋጋ የንጉሡን ግራ ዓይን አምጡና ውሰዱ በላቸው ብለሽ ለአባትሽ የመከርሽው ስለምን ነው?” አሏት።
“ንጉሥ ሆይ አልቀጣሽም ብለው ይማሉልኝና እነግርዎታለሁ” አለች።
“አልቀጣሽም!” ብለው ማሉላት።
“ንጉሥ ሆይ፤ ድኃና ጌታ ተጣልተው ወደርሶ የመጡ እንደሆነ በቀኝ የቆመውን ጌታውን ብቻ ያያሉ እንጂ በግራ የቆመውን ድኃውን አያዩም፤ ስለዚህ መቼም ግራ ዓይንዎ ሥራ ካልያዘ ብዬ ነው” አለቻቸው።
ንጉሡም የልጅቱን ንግግር ሰምተው እጅግ አደነቁ። ወዲያውም ወንድ ልጃቸውን ጠርተው “ልጄ ሆይ፤ በመልክና በእውቀት ከርሷ የምትሻል ሴት የለችምና እርሷን አግብተህ መንግሥቴን ይዘህ ኑር” አሉት። ልጁም እርሷን አግብቶ እርሱ ንጉሥ፣ እርሷ ንግሥት ተብለው ኖሩ።
***
በተናገረው ነገር ዕምነት ያለው ብልህ ህዝብና በኃይል የማያምን መሪ፣ ኃላፊና አለቃ ለማግኘት አለመቻል መርገምት ነው። ይህ አለመቻል በተደጋጋሚ ዕውነትነቱ ታይቷል። ይህ እየሆነ እያዩ ምክር አለመቀበል ደግሞ የባሰው አባዜ ነው።
ቮልቴር እንዳለው፡-
የክፉ ገዢ ጦስ፣
ስም ነው ክፉ ጥላ፣ የቀን ሌት መጋኛ
ስም ዕዳ ያለበት
እንቅልፍ አይወስደውም
ቢተኛም ባይተኛ።
አንዳንድ ጊዜ ገዢዎችና መሪዎች የተናገሩት በተግባራዊ ዕውነታ በተጨባጭ ቢፋለስና ቢረክስም እንኳ፤ ጉዳዩን መርምረው በተቃና መንገድ አገርን ፓርቲንና የሥራ ኃላፊነትን ከመምራት ይልቅ እኔ ያልኩት ከሚፈርስ፣ የኔ ዝናና ስም ከሚጎድፍ የቀረው ይቅር ማለት ይቀናቸዋል። ለዚህም ነው አጋጣሚንና ሁኔታዎችን ተገን በማድረግ፣ ለተቃና ጥያቄ፣ የተዛባ መልስ፤ ለቀላል ጥያቄ ውስብስብ ምላሽ፤… መስጠትን እንደ ልዩ ዘዴ መቁጠር የነጋ ጠባ ትዝብታችን እየሆነ የመጣው።
የኢኮኖሚ አቅም ግንባታንም በተመለከተ የዘመቻ ባህል መቀነስ አለበት ሲባል፣ ሲነገር ሲዘከር ኖሯል። የሚሰማ የለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ከአንድ ሰሞን ግርግርና ዘራፍ ዘራፍ የተለየ እርምጃ ከሌለ፤ እንደ ጧት ጤዛ መሆን ነው። ጥሞና ያለው፣ ከጀርባው ማናቸውም ዓይነት ጥንስስና እኩይ ዓላማ የሌለው፣ ክንዋኔ ብቻ ነው ወደፊት የመጓዝ መሠረት። ተግባራዊ ጽናቱና ጥረቱ በሌለበት፤ በጀማ፣ በኮሚቴ፣ በሸንጎ ላይ ዲስኩር ማድረግ ብቻ፤ እንኳንስ ትላልቅ ፅንሰ-ሀሳቦችን ማስረፅ አፍአዊ ሂደት ከመሆን አይታለፍም። በየጊዜው  አድገናል ተመንድገናል በሚል ዜማ ድግግሞሽ ብቻ የዕውነቱ ብልጽግና አይመጣም። ይብሱንም አንድ አዛውንት፤ “ይህን ሁሉ ያወራህልንን በአይናችን የምናየው ማንኛችን እንሆን? እኛ ነን አንተ?” እንዳሉት እንዳያሰኝ ያሰጋል።
ከቶውንም፤”አልቀጣህም ብለው ይማሉልኝና ዕውነቱን እነግርዎታለሁ” የሚል ህዝብም ሆነ፤ “አልቀጣም!” የሚል የበላይ ባለበት ንፍቀ-ክበብ፤ የዲሞክራሲ አየር እንደማይነፍስ አሌ የሚባል ነገር አይደለም። የምህረት አድራጊና የምህረት ተቀባይ ግንኙነት መኖር የዲሞክራሲ ዋስትና አይሆንም። ይልቁንም የበላይና የበታች፣ የአዛዥና የታዣዥ ቁርኝት ነው። እኔ በነፃነት እናገራለሁ የሚል ህዝብና ነፃነትና መብትህን አከብራለሁ የሚል የበላይ ይኖር ዘንድ ነው የረዥሙ ዘመን ትግል ሁሉ መጠንጠኛ። ይህን የሚገድብ ሁኔታ፣ ማስፈንጠሪያ፣ ለበጣ፣ ትዕዛዝ ወዘተ-- ዛሬም ጊዜያዊ ማስታገሻ እንጂ ዘላቂ ፈውስ አይደሉም።
አጋጣሚን በመጠቀም የሩቅም ሆነ የቅርብ ግላዊ ጥቅምን ለማግኘት መሯሯጤ በህዝብ ዘንድ አይታወቅም ብሎ መገመትም ፍፁም የዋህነት ነው። እንዲህ ያለ ተግባር ከተፈጸመ ግመል ሰርቆ ማጎንበስ ብቻ ሳይሆን፤ ግመሏም እንሽላሊት ናት ብሎ እንደ መሟገት ይሆናል። የህዝብ አደራ እንደ ዩኒቨርሲቲ ማሟያ ኮርስ አይደለም። ስለሆነም የህዝብን አደራ ለግል ህይወት ማሻሻያ፣ ለግል የሩቅ ጊዜ ምኞት ማሳኪያ፤ ለማድረግ መጣር በቀላሉ የማይስተሰረይ ኃጢአት ነው። ያስጠይቃል፤ ያስቀጣል፤ ዋጋ ያስከፍላል። አተርፍ ባይ አጉዳይ ያደርጋል። የገብሬልን መገበሪያ የበላ፤ በገብሬል  በገብሬል! ሲል ይገኛል እንዲሉ፤ ብዙም ሳይርቁ መጋለጥ አለ።
እንዲህ ያለው እኩይ ተግባር የህዝቡን የረዥም ጊዜ ግብና የዕድገቱን ዋስትና ያኮላሻል። የህዝብ አደራ የሥልጣን ጥም መወጫ አይደለም። የወንበር ፍቅር ማሞቂያም አይደለም። የግል ዝና ማካበቻ አይሆንም።  የፖለቲካ ሽኩቻ ማድሪያ ሊሆንም አይገባም። የጀብደኝነት ወሸነኔም ዘመን አይደለም። የውስጥ-አርበኝነት የበግ ለምድም ሊሆን ከቶ አይችልም። የህዝብ አደራ የዳተኝነትና የዐድር ባይነት መሸፈኛም አይደለምና፣ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱን መገንዘብ ያስፈልጋል።
መቼም ቢሆን መቼ የህዝብ አደራ በግልጽ፣ የህዝብን ጥቅም ማስከበሪያ ኃላፊነት ነው።
በአግባቡ ካልያዙት፣ ዙፋኑን ካገኘ በኋላ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቶ “ምነው ይሄን ዘውድ የሰጡኝ ዕለት ማጥለቂያ እራስ ባይኖረኝ ኖሮ?” እንዳለው ንጉሥ መፀፀቻ ይሆናል። በአንጻሩ መደረግ የሚገባውን ነገር በጥሞና ማስተዋል፣ የሂደትና ክንዋኔውን የወደፊት ችግሮችና እንቅፋቶች ከወዲሁ መለየት ያሻል። ምክንያቱም በተነሱት ግላዊ ጉዳዮች ላይ ልብና ልቦናን ከተከሉና ጥቅምን ብቻ ላሳድድ ካሉ፤ እንደ ንጉሱ ከግራና ከቀኝ ላሉ ወገኖች አድሏዊ መሆን አይቀርምና፤ “ግራ ዐይንዎ ስራ አልያዘም ብዬ ነው” ብሎ እሚያሳይ ሰው መኖር አለበት። “ሁሉም ፈረስ ላይ ልውጣ ካለ፣ ገደሉን ማን ሊያሳይ ነው?” ማለትም ይኼው ነው።

Read 1451 times