Saturday, 29 June 2024 19:55

ከሰሞኑ የኬንያ ህዝባዊ ተቃውሞ ምን እንማራለን?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “ጎረቤትህ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ”


          ከሰሞኑ በኬንያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ አልበረደም። ይህ ተቃውሞ ረቂቅ ዓዋጅን ከማሰረዝ አንስቶ የተጓዘባቸው ሂደቶች አነጋጋሪ ሆነዋል። ለተቃውሞው መቀስቀስ እንደ አጣዳፊ ምክንያት የሚጠቀሰው፣ ለኬንያ ምክር ቤት የቀረበው የፋይናንስ ረቂቅ ዓዋጅ ሲሆን፤ በሂደት ግን ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።
እንደቢቢሲ ዘገባ ከሆነ፤ መንግስት ገቢውን በማሳደግ አገሪቱ የተከማቸባትን ከ80 ቢ.ብር በላይ የውጭ ዕዳ ለመቀነስ በሚል ዳቦን ጨምሮ በምግብ ዘይት፣ በሴቶች የንጽህና መጠበቂያ፣ በሞባይል ስልኮች፣ በኮምፒውተሮች፣ በተሽከርካሪዎችና በሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ የቀረጥ ጭማሪን ያካተተ ረቂቅ የፋይናንስ ሕግ አዘጋጅቶ ለፓርላማ እንዲፀድቅ አቀረበ። ሕጉ በተለያዩ የማሕበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ተሰራጭቶ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተቃውሞን ጫረ። ይሁንና ተቃውሞው የኬንያ የሕዝብ እንደራሴዎችን ቀልብ ሊስብ አልቻለም። ነገሩ ያበገናቸው ኬንያውያን ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. አደባባዩን በሰላማዊ ሰልፍ ባረኩት። ሰላማዊ ሰልፉ የዋዛ አልነበረም፤ ‘ፓርላማውን እንቆጣጠር - “Occupy The parliament” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ነበር።
አገሪቷ የነሱ ብቻ አይደለችም። የሁላችንም ናት። ስልጣን የህዝብ ነው። ፓርላማውን ተቆጣጥረን፣ የሕዝብ ተወካዮች የኬንያ ሕዝብ የሚለውን እንዲሰሙ እናደርጋቸዋለን” አለ-በተደጋጋሚ መንግስትን በድፍረት በመቃወም የሚታወቀው ቦኒፈስ ምዋንጊ፣ ለሰልፍ ከመውጣቱ በፊት። ዜጎች ወደ አደባባይ ተመሙ። የኬንያን ሰንደቅ ዓላማና የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው የወጡ ተቃዋሚዎች እየዘፈኑ፣ እየጨፈሩ ነበር- ወደ ፓርላማው ያመሩት።
ተቃውሟቸው ወዲያውኑ ፍሬ አላፈራም!
የምክር ቤቱን አብላጫ ወንበር የተቆጣጠረው፣ የፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት 195 የድጋፍ ድምፃቸውን የሰጡ ሲሆን፣ በ106 ተቃውሞ ረቂቅ ዓዋጁ ፀደቀ። ይሄኔ ወጣቶች የሚበዛበት ኬንያ ተቃዋሚዎች፣ ከምክር ቤቱ አዳራሽ ውጭ ሆነው የተቃውሞ ድምጹን ያሰማ ያዘ፤ ሰሚ ቢያጣም ቅሉ።
የተቃውሞ እንቅስቃሴው በሰላማዊ ሂደቱ ግን አልቀጠለም፤ ከፖሊስ ጋር ፍጥጫው ጠንክሮ ነበር። ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝና ውሃ መርጨት ብቻ ሳይሆን ጥይትም መተኮስ ጀመረ። ፖሊስ ሊቆጣጠረው ባልቻለው ሁኔታ ወጣቶቹ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት የፓርላማ በሮች ገነጣጥለው ወደ ውስጥ ገቡ። ። መስኮቶች ተሰባበሩ። የፓርላማው ሕንጻም እሳት ተለኮሰበት።
የተቆጡ ወጣቶች ፓርላማውን ጥሰው ሲገቡ፣ ተቃውሞ የቀረበበትን ሕግ ያጸደቁትን የፓርላማ አባላት ከአዳራሹ ለማስወጣት ሄሊኮፕተር አንዣበበች። ፖሊስም በምላሹ ጥይት ተኮሰ። በርካታ አስከሬኖችም በጎዳናዎች ላይ ታዩ። በሰላማዊ መንገድ የተጀመረው የኬንያውያን ተቃውሞ ወደ ሁካታ ተለወጠ።
የኬንያው ዋነኛ ተቃዋሚና የአዚሚዮ ጥምረትን የሚመሩት ራይላ ኦዲንጋ፣ መንግስት “በአገራችን ልጆች ላይ ጭካኔ የተሞላበት የሃይል በትሩን እየሰነዘረ ነው” ሲሉ ነቀፉ። በኬንያ የተፈጸመውን ያልተጠበቀ  የዜጎች ግድያ ተከትሎ፣ የትዊተር ገጽ ለሰዓታት ተቋረጠ፣ ኢንተርኔት ተጨናጎለ፣ ዩቲዩብ ቀጥ አለ።
ኢንተርኔት ከመዘጋቱ በተጨማሪ የግል ንብረት የሆነው ኬቲኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ በተቃውሞ ዘገባው ምክንያት፣ ከመንግስት ‘እዘጋችኋለሁ’ የሚል ማስፈራሪያ እንደደረሰው አስታወቀ።
ነገሮች ጦዙ፤ ከረሩም!
ተቃውሞው በመዲናዋ ብቻ ሳይሆን የሩቶ የትውልድ ስፍራ የሆነችው የጊሹ ግዛትን ጨምሮ፤ በኪሱሙ፣ ሞምባሳ ወዘተ ተቀጣጠለ- ከአገሪቷ 47 ግዛቶች ውስጥ በ35ቱ ተቃውሞው ተስፋፋ።
በኬንያ የፓርላማውን በር ጥሰው በገቡ ተቃዋሚ ወጣቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ከተሞችም በዜጎች ላይ ግድያዎች ተፈጽመዋል። አንዳንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሟቾችን ቁጥር ከ20 በላይ አድርሰውታል።
በኬንያ ሕይወትን የቀጠፈና አገሪቱን ያመሳቀለው አወዛጋቢ የፋይናንስ ሕግ ምንጩ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ነው ተብሏል። IMF ኬንያ በአሁኑ ጊዜ ያለባትን 80 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብሔራዊ ዕዳን ለመቀነስ፣ የተለያዩ ግብሮችን መጣል እንዳለባት ምክሩን መለገሱ ተጠቁሟል። ተቋሙ በተለይ በአፍሪካ አገራት ጥሩ ስም እንደሌለው ሲታወቅ፣ ተረኛዋ ኬንያ በዜጎቿ በኩል በመንግሥት ላይ ብቻ ሳይሆን ኬንያን በእጅ አዙር እየጠመዘዟት ነው ባሏቸው ሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም ላይ ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።
ሩቶ በዚያው የተቃውሞ ዕለት ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ መንግስታቸው “ሁከትና ስርዓት አልበኝነት” ሲሉ የጠቀሷቸው ድርጊቶች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ። ከሰዓታት በኋላም የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር የአገሪቱ ሰራዊት እንዲሰማራ ትዕዛዝ መስጠታቸው ተሰማ። ሆኖም ተቃውሞውን አላረገበውም።
በማግስቱ ረቡዕ ግን ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ፣ የተለያዩ ታክሶችን ለመጣል በታቀደው የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ ላይ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ አስታወቁ።
ረቂቅ ህጉን የኬንያ ህዝብ ስለተቃወመው ውድቅ ተደርጓል አሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ዜጎች በደስታ ጮቤ አልረገጡም። ይልቁንስ ሌላ ከባድ ጥያቄ አነሱ- ፕሬዚዳንት ሩቶ ከሥልጣን እንዲወርዱ ጠየቁ።
የኬንያ ተቃውሞ ተምሳሌትነቱ በብዙ መልኩ ሰፊ ነው፤  ነገር ግን አንድ አንጓ አለው። የመንግስት ለሕዝብ ተገዢ መሆን። በሕዝብ ገንዘብና በሕዝብ ድምጽ ስልጣን የተቆናጠጠ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሕዝቡን ድምጽ ካልሰማ፤ እምቢተኝነት ምሳው፣ ተቃውሞ ራቱ ይሆናል። ልክ እንደ ሰሞኑ ኬንያ ማለት ነው። ግልጽነትን ካጎለበተ፣ አገሪቱን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ከመራ ግን ነገሮች ተደላድለው ለዜጎች ምቹ ምሕዳርን ይፈጥራሉ።


Read 791 times