Friday, 28 June 2024 21:01

የታሊስማን ጋለሪ የቅርስ ቤት ተመረቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)


ታሊስማን ጋላሪ የተመሰረተው በአቶ ማሲሞ ዴ ቪታ በ2009 ዓ.ም ብስራተ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ሳልቫቶሬ ዴ ቪታ ኮምፕሌክስ ህንፃ ላይ  ሲሆን፤ የአርትስ ጋላሪውን ታዋቂና ታዳጊ የስነ-ጥበብ አርቲስቶች ስራቸውን ለህዝብ እንዲያሳዩና ከህዝቡም ጋር እንዲተዋወቁ  እድሉን በማመቻቸት እንዲጠቀሙ ሲያደርግ  ቆይቷል፡፡
ፈረንሳይ ለጋሲዮን የሚገኘው አዲሱ ታሊስማን ጋላሪ የቅርስ ቤት፣ ዛሬ ሰኔ 20 ቀን 2016  ዓ.ም፣ ከፍተኛ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የደጃዝማች አምዴ አበራ ካሣ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስነት የመዘገባቸውን የቅርስ ቤቶች የነበራቸውን ይዘት ሳይለቁ ተጠግነውና ታድሰው፣ ቅርሶቹ ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ በርካታ ተግባራት ያከናውናል።

ተቋሙ የገንዘብ አቅምና ሙያዊ ብቃት ላላቸው ወገኖች ተላልፈው እንዲለሙና በእንክብካቤ እንዲቆዩ ለማድረግ ባወጣው መስፈርት ተወዳድረው፣ የደጃዝማች አምዴ አበራ ካሣ መኖሪያ ቤት የነበረውን የቅርስ ቤት ለማልማት፣ ከቢሮው ጋር ውል በመፈፀም፣ ቀድሞ የነበረበትን ይዘት ሳይለቅ በመጠገንና በማደስ፣ አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ የበኩላቸውን አድርገዋል፡፡

በምረቃ ስነስርአቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)፤ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ ያሏት ቅርሶች፣ በአብዛኛው አቧራ ለብሰውና ተጎሳቁለው ነበር የሚታዩት፡፡ አሁን ግን በልማት በተለይም በኮሪደሩ ልማት ቅርሶቻችን ደረጃቸውንና ታሪካቸውን በሚመጥን መልኩ ተጠብቀው እንዲለሙና እንዲጠበቁ እየተደረገ ይገኛል” ብለዋል።
ቅርሶች በመንግስት ብቻ ሊለሙ እንደማይችሉ የገለጹት የቢሮ ኃላፊዋ፤ ቅርሶችን ከባለሀብቶች ጋር በመሆን አልምቶ ለቱሪስት ክፍት እንዲሆንና ጥበብን የምናሳድግበት፣ የምናለማበትና ለትውልድ የምናስተላልፍበት አሰራር ተፈጥሯል ብለዋል።

Read 1237 times