Friday, 28 June 2024 19:54

ሕብረት ባንክ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሕብረት ባንክ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ የአንድ ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ፡፡ የገንዘብ ድጋፉ የተደረገው ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የገንዘብ ድጋፉን ያበረከቱት የሕብረት ባንክ ሲኒየር ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጽጌረዳ ተስፋዬ ባደረጉት ንግግር፤ ማሕበሩ ለሚሰራቸው ሰብዓዊ ስራዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። አክለውም፣ የማሕበሩ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትም የበጐ አድራጎት ስራውን በስፋት ለማከናወን የሚረዳውን የሕንፃ ግንባታ መደገፍ ለባንኩ ትልቅ ኩራት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ባንኩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የባንክ አገልግሎቱን ከመስጠት ባሻገር ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሕበረሰቡ ዕድገት፣ ጤናማነትና ለውጥ የሚሰሩ ድርጅቶችን በተቀመጡት መመዘኛዎች መሰረት ቅድሚያ በመስጠት እየደገፈ እንደሚገኝ ወ/ሮ ጽጌረዳ ተስፋዬ  አብራርተዋል፡፡  

የባንኩ ዕድገትና ስኬት መሰረቱም ከማሕበረሰቡ ጋር በሕብረት መስራቱ መሆኑን በመግለፅ፣ ሕብረት ባንክ የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን በዚህ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። አያይዘውም፣ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተደረገው የገንዘብ ድጋፍም የዝግጅቱ አንድ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋሚካኤል ታፈሰ በበኩላቸው፣ ማሕበሩ እየሰጠ ያለውን የሰብዓዊ አገልግሎት አሁን ካለበት ደረጃ በማሻሻል፣ ለሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግና ራዕዩን ለማስፋት የእያንዳንዱ ባለድርሻ ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕብረት ባንክ ሕዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ይፋዊ የማብሰሪያ መርሐ ግብሩ ላይ፣ ለአስር የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለእያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ በድምሩ 15 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

Read 995 times