የማላዊ መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ ገብተዋል ያላቸውን 238 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው ሊመልስ መሆኑን አስታውቋል። ስደተኞቹ በማላዊ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኙ እስር ቤቶች ታስረው እንደቆዩ ተገልጿል።
የአገሪቱ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ስደተኞቹ የማላዊን ሕግ በመተላለፍ ወደ አገሪቱ መግባታቸውን ጠቅሷል።
የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ሳጅን ፍራንሲስ ቺታምቡሊ፤ “238 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደት በዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ድጋፍ የሚከወን ነው” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም፤ “አሁን ላይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ሃላፊዎች ከዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት አቻዎቻቸው ጋር በማዚምባ እና ምዙዙ እስር ቤቶች የሚገኙ ሕገ ወጥ ስደተኞችን የመለየት ስራ ሰርተዋል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዘንድሮው ዓመት ጥር ወር አንስቶ በሰሜኑ የማላዊ ክፍል ለመግባት ሞክረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የውጭ አገር ስደተኞች ብዛት 173 ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 142 ያህሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የ”ማላዊ 24” ድረ ገጽ ዘገባ ይጠቁማል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት፣ የማላዊ ፖሊስ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ የነበሩ 29 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የተቀበሩበትን የጅምላ መቃብር ማግኘቱን ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ገልጾ ነበር። የጅምላ መቃብሩ የተገኘው ከማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ በስተሰሜን 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሚዚምባ አካባቢ ነበር።
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ የቀድሞ የማላዊ ፕሬዚዳንት ፒተር ሙታሪካ ልጅ የሆኑት ታዲኪራ ማፉብዛ፣ በጥቅምት 2014 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ሲሆን፣ ከእርሳቸው ጋር ሰባት ሰዎችም ታስረው ነበር። ይሁን እንጂ ታዲኪራ ላይ የቀረቡት የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሰውን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል ክሶች ባለፈው ረቡዕ፣ ከ19 ወራት በኋላ ውድቅ ተደርገው፣ ተከሳሹ ነጻ መውጣታቸው ተዘግቧል፡፡
ማላዊ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚሸጋገሩ ስደተኞች ሁነኛ የመተላለፊያ መስመር እንደሆነች ይነገራል።
Saturday, 22 June 2024 00:00
የማላዊ መንግሥት 238 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው ሊመልስ ነው
Written by Administrator
Published in
ዜና