Saturday, 15 June 2024 00:00

በአማራና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ውጥረት ነግሷል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 - ነዋሪዎች ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት ሰግተዋል


          በአማራና ትግራይ ክልሎች የ”ይገባኛል” ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ውጥረት መንገሱ ተገለፀ። ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የትግራይ ሃይሎች ወደ እነዚሁ አዋሳኝ አካባቢዎች መጠጋታቸው ነው ውጥረቱን የፈጠረው።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪ በአካባቢው ከአማራ ክልል ዞኖች በአንጻራዊነት የተሻለ መረጋጋት እንዳለ ይገልጻሉ። ይሁንና እርሳቸው “የህወሓት ታጣቂ” ያሉት የትግራይ ሃይል አደጋ መጋረጡን ጠቁመዋል።
“ይኸው ሃይል በጠለምትና በዋልድባ አካባቢ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው” ያሉት እኚሁ ነዋሪ፣ በቅርቡ “ሰሜን ጎንደርና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞኖችን በሚያገናኘው፤ አዲአርቃይ ወረዳ፣ አሊ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ‘ዱሃር ግዛና’ የሚባል ስፍራ ላይ የህወሓት ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ጥቃት 15 ንጹሃን መገደላቸውንና 3 ሰዎች መቁሰላቸውን ጠቁመው፤ ከጥቃቱ ተጎጂዎች መካከል ታዳጊ ሕጻናት እንደሚገኙበትም አስረድተዋል።
ከጥቃቱ ባሻገር፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ንብረት የሆኑ ከ500 በላይ ከብቶችና 300 ፍየሎች በትግራይ ሃይሎች መዘረፋቸውን ነው የገለፁት።
ነዋሪው “ጥቃቱን አድርሰዋል” ያሏቸው ታጣቂ ሃይሎች መቀመጫቸው እንዳባጉና መሆኑን የጠቀሱት ነዋሪው፤ “ሃይሉን የሚመሩት ወርቂ ዓይኑ የተባሉ ጄኔራል” መሆናቸውን አመልክተዋል። የታጣቂ ሃይሉ ብዛት ከ250 እስከ 300 ድረስ እንደሚገመትና “አርሚ 11” ተብሎ እንደሚጠራም አመልክተዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የትግራይ ሃይሎች ትጥቅ ሳይፈቱ መቅረታቸው የደህንነት ስጋት ጋርጦብናል የሚሉት ነዋሪው፣ “አሁንም ለሌላ ጥቃት እየተዘጋጁ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ የሰሜኑ ጦርነት እንዳያገረሽ ስጋት አለን።” ብለዋል።
በራያ አካባቢ፣ ቀደም ሲል አላማጣ ከተማ ይኖሩ እንደነበርና አሁን ግን ተፈናቅለው ኮረም እንደሚገኙ የነገሩን አቶ አማረ ደሳለኝ የተባሉ መምሕር፣ የጸጥታውን ሁኔታ ሲያብራሩ፣ “በየትምሕርት ቤቶች የትግራይ ታጣቂዎች ገብተዋል። ሕዝቡ ተገቢውን ማሕበራዊ አገልግሎት እያገኘ አይደለም።” ብለዋል። በእነዚሁ ትምሕርት ቤቶች ውስጥ ታጣቂዎቹ የቡድን መሳሪያ ጭምር ይዘው መስፈራቸውንና መንግስታዊ ተቋማት ከስራ ውጭ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ አንድ የባለ ሶስት እግር (ባጃጅ) አሽከርካሪ በትግራይ ሃይሎች መገደሉን ተከትሎ፣ በነጋታው ከቀብር ስነ ስርዓቱ በኋላ በአላማጣ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉን የተናገሩት አቶ አማረ፤ በሰልፉ የተሳተፉ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ በእነዚሁ ሃይሎች ወረቀት መበተኑን  ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት የራያ አካባቢ በአማራ ክልልም ሆነ በትግራይ አስተዳደር ስር አለመሆኑንና መደበኛ አስተዳደር አለመኖሩን በማመልከት፣ ሕብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እየከወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
“ከ50 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወደ ቆቦ ተጉዞ ነበር። ሆኖም መጠለያ አላገኘም። በቂ ዕርዳታ ከመንግስት አልቀረበለትም። ይህንን ተከትሎ ወደ አላማጣ ለመመለስ ተገድዷል። አንዳንድ በትግራይ ሃይሎች የሚታደኑ ግለሰቦች ከአላማጣ ሸሽተው ቆቦ ከትመዋል።”  ሲሉ ነዋሪው ጠቁመዋል።
ኮረም፣ ኦፍላ፣ ራያ አላማጣና አላማጣ ከተማን ጨምሮ በሁሉም የራያ አካባቢዎች የትግራይ ሃይሎች እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ አማረ፣ ኮማንድ ፖስት በማወጅ የአማራ ክልል ግለሰቦችን ትጥቅ ከማስፈታት ባለፈ፣ የፌደራል መንግስቱ የሰጠው ተጨባጭ መልስ እንደሌለ ተናግረዋል።
ከወራት በፊት በፌደራል መንግስቱ፣ የራያ አላማጣ ነዋሪዎችን እንዲያወያዩ የተላኩት የአገር መከላከያ ሰራዊት አዛዦች፤ ከትግራይ ክልል ተፈናቃዮች እንደሚመጡ፣ የአማራ ክልል በራያ ያደራጀው የመንግስት መዋቅር እንደሚፈርስና በሕዝቡ ምርጫ መሰረት አዲስ የጋራ አስተዳደር እንደሚዋቀር መግለጻቸውን አቶ አማረ አውስተዋል።
አዲሱ አስተዳደር አሳታፊ የሆነ መዋቅር እንደሚኖረውና መከላከያና ፌደራል ፖሊስ ጸጥታ እያስከበሩ ሪፈረንደም እንደሚደረግ ከአወያዮቹ መገለፁንም ተናግረዋል።
ነገር ግን ቃል የተገባው ጉዳይ ተግባራዊ ከመሆን ይልቅ የትግራይ ታጣቂዎች የ”ይገባኛል” ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አልፈው ቀድሞም በአማራ ክልል አስተዳደር ስር ወዳሉ አካባቢዎች እየገቡ መሆናቸውን አቶ አማረ  አስታውቀዋል።
ሚያዚያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ለትግራይ ክልል መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016  ባለው ጊዜ፣ በአማራ ክልል በኩል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች የተመሰረቱ “ሕገወጥ” ያሏቸው አስተዳደሮች ሊፈርሱ፣ ተፈናቃዮች ደግሞ ወደቀዬአቸው ሊመለሱ ከፌደራሉ መንግስት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረው ነበር።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ፣ «ህወሓትና ግብረ አበሮቹ» ያላቸው አካላት፣ የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሱባቸውና ሰሞኑን በሃይል ከያዟቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲተገበርም መጠየቁ ይታወቃል።
በሌላ በኩል፤ ከሳምንታት በፊት፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ፤ “የፌደራል መንግስት የህወሓት ታጣቂዎችን በወረራ ከያዟቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ እንዲያደርግና በተደጋጋሚ ወረራ እየተፈጸመበት ለከፍተኛ ችግር ለተጋለጠው ህዝብ አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግ” አሳስቦ ነበር።
እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ የፌደራሉ መንግስት የሰጠው ይፋዊ መግለጫም ይሁን ማሳሰቢያ የለም።



Read 569 times