Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Wednesday, 04 April 2012 07:29

የዋጋ ንረት መንግስትን ይጠቅማል፤ ዜጎችን ይጎዳል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የአፍሪካ ልማት ባንክ፤ የአለም ባንክ እና አይኤምኤፍ፤ የኑሮ ውድነቱ መንስኤ የብር ህትመት እንደሆነ ይገልፃሉ

የዋጋ ንረት መቆጣጠር ያልተቻለው ለምንድነው?

የመንግስት የብቃት ጉድለት ነው ምክንያቱ?

ዜጎች ቢሰቃይ ምንም አያመጡም ተብሎ ነው?

ወይስ ከእሳት ጋር መጫወት  ይዟል?

ስለ ዋጋ ንረትና ስለ ኑሮ ውድነት እያማረርን ስንናገር፤ እጅ ዘርግተን አቤት ስንል፤ ይሄው አምስት አመት አለፈን። ግን ምንም የተሻሻለ ነገር የለም። የዋጋ ንረቱ ከአመት አመት እየባሰበት ነው። የዜጎች ኑሮና ጓዳም በዚያው ልክ እየመነመነ መጥቷል። እየመነመነም ይሄዳል እንጂ። የችጋር ኑሮ ምንም ያህል እየከፋ ቢሄድ፤ መለመዱ አይቀርም ማለት ነው? ሁለት ሶስት አመት ሲያልፍ፤ የቀድሞው አኗኗር የሩቅ ጊዜ ትዝታ ሆኖ ይደበዝዛል።

ያኔኮ... በልተን ጠጥተን

የዛሬ አምስት አመት ... በጣም ሩቅ ሆኖ የሚታያቸው ዜጎች፤ “ያኔኮ ቁርስ እንበላ ነበር” እያሉ በትዝታ ይቆዝማሉ። “ያኔኮ... በየሳምንቱ ባይሞላልን እንኳ፤ አልፎ አልፎ ስጋ ገዝተን ወደ ቤት እንወስድ ነበር”... “ያኔኮ፤ የታክሲ ሂሳብ፤ ኪስን የሚያራቁት አልነበረም” ... “ያኔኮ አንድ ክፍል ቤት ለመከራየት 1 ሺ ብር አያስፈልግም ነበር”... “ያኔኮ፤ አንድ ሊትር ዘይት፤ ብርቅና ቅንጦት አልነበረም” ... እንዲህ እንዲህ እያልን፤ ኑሮውን በየቀኑ እንደሚጨምር ሸክም እየገፋን እንቀጥላለን? መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ የደረሱ በርካታ ዜጎች አሉ። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና መንግስት፤ ይህንን አሳዛኝ የዜጎች ችግር የተረዱት አይመስሉም። ቢገባቸው ኖሮ፤ ቅጥ ባጣ የገንዘብ ህትመት የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ እንዲሄድ ያደርጉ ነበር?

ኢህአዴግና መንግስት፤ የዜጎችን የኑሮ ችግር እንዲገነዘቡና እንዲያውቁ መጠበቅ፤ ከባድ ስራ እንዲሰሩ እንደመጠየቅ ከሆነ፤ እሺ ይቅር። ነገር ግን ዜጎች ፋታ በማይሰጥ የዋጋ ንረት መሰቃየት እንደበዛባቸው ከመናገር፤ ምሬታቸውን ከመግለፅ፤ እሮሯቸውን ከማሰማትና አቤት ከማለት የተቆጠቡበት ጊዜ የለም። ታዲያ፤ መንግስትና ኢህአዴግ፤ ቢያንስ ቢያንስ የዜጎችን እሮሮ መስማት ያቅተዋል?

በአመት 25 ቢሊዮን ብር ኪሳራ

ለነገሩ፤ ካለማወቅ የመጣ ችግር አይደለም። መንግስት፤ የዜጎች ችግር ምን ያህል አስከፊ እየሆነ እንደመጣ ባይገነዘብ እንኳ፤ ...የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በቁጥርና በመቶኛ ማወቅ ይችላል። ኢትዮጵያ፤ በዋጋ ንረት የአለም አንደኛ ሆናለች። የራሱ የመንግስት መረጃዎችም በየወሩ የዋጋ ንረቱን መጠን ያሳያሉ። በዚያ ላይ፤ “የዋጋ ንረት ዋነኛ ጠላታችን ነው”፤ “የዋጋ ንረት ከ10 በመቶ በታች እንዲወርድ እናደርጋለን” እያለ በየጊዜው ይናገራል። ባለፈው ሳምንት የብሄራዊ ባንክ ገዢ ለፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርትም፤ በዋጋ ንረት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው።

የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠርና ለማውረድ ብዙ ስራ እንደተከናወነ የሚዘረዝረው የብሄራዊ ባንክ ሪፖርት፤ ከመስከረም ወዲህ የዋጋ ንረቱ እየቀነሰ መጥቶ በጥር ወር 32 በመቶ እንደደረሰ ገልፀዋል። እንዲህ ነችና መቀነስ? ሁለት ጥያቄዎችን ብቻ እናንሳ። 32 በመቶ ማለት ምን ማለት ይሆን? ከጥር ወር ወዲህስ እንዴት እየሆነ ነው?

የዋጋ ንረት 32 በመቶ ደርሷል ሲባል፤ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር፤ በዘንድሮው ጥር ወር የሸቀጦች ዋጋ በአማካይ በ32 በመቶ ንሯል ማለት ነው። አምና በ1ሺ ብር ስናሟላው የነበረው የወር አስቤዛ፤ ዘንድሮ 1320 ብር ይፈጅብናል። በሌላ አነጋገር፤ በዚያው የወር ገቢ፤ አምና አራት ሰዎችን ለማኖር እንችል ከነበረ፤ ዘንድሮ ከሶስት ሰዎች በላይ የማኖር አቅም አይኖረንም ማለት ነው።

እንደምንም ብለን የቆጠብነውና ያስቀመጥነው ገንዘብ ካለም፤ በዋጋ ንረት ተሸርሽሯል። በአመት ውስጥ ሩብ ያህሉ እንደተቃጠለ ቁጠሩት። የብር የመግዛት አቅም በሩብ ያህል ቀንሷላ። እንግዲህ የዛሬ አመት፤ ባንኮች ውስጠ 100 ቢሊዮን ብር ገደማ የቁጠባ ሂሳብ አልነበር? እንደምንም ተቸግረውም ሆነ ተርበው፤ ገንዘብ ሲቆጥቡና ሲያስቀምጡ የነበሩት ዜጎች፤ በአመት ውስጥ 25 ቢሊዮን ብር ከስረዋል ማለት ነው።

ለመንግስት ድርብ ጥቅም ነው

በዋጋ ንረት ተጠቃሚ የሚሆን ወገን ካለ፤ “ተበዳሪ” ብቻ ነው። የአገራችን ትልቁ ተበዳሪ ደግሞ መንግስት ነው። ከ70 በመቶ በላይ የአገሪቱ ብድር የመንግስት አይደል? መንግስት፤ በዋጋ ንረት ይጠቀማል። እንዴት ብትሉ፤ ...የወጪ እና የእዳ ሸክሙን ያቃልለታላ። የዋጋ ንረት ለመፍጠር የሚጠቀምበት ዘዴ ደግሞ ሌላው ጥቅም ነው - ገንዘብ ማተም።  የዋጋ ንረት መንግስትን ይጠቅማል መባሉ አዲስ እውቀት አይደለም።

የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም በ2011 ሪፖርቱ ላይ እንደገለፀው፤ መንግስታት እዳቸውን ማቃለል የሚችሉት፤ አሁን አሜሪካና አውሮፓ እያደረጉ እንዳሉት ወጪያቸውን ቀንሰው ከታክስ ገቢ ጋር በማመጣጠን፤ አልያም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ እንዳለው በብር ህትመትና በዋጋ ንረት አማካኝነት እንደሆነ ይገልፃል።

ባለፈው ጥር ወር፤ International Journal of Academic Research in Economics and Management Sciences በተሰኘው የምርምር ህትመት ላይ አራት ምሁራን ያቀረቡት የጥናት ፅሁፍም ይህንኑን ሃሳብ ያጠናክራል። በተለይ ድሃ አገራት፤ በታክስና በእርዳታ ከሚያገኙት ገንዘብ የሚበልጥ በጀት እየመደቡ ወጪያቸው ስለሚጨምር,፣ እዳ ውስጥ እንደሚገቡ ጥናቱ ይጠቅሳል። በርካታ የአፍሪካ መንግስታት የበጀት ጉድለት ለመሸፈንና እዳ ለማቃለል የሚጠቀሙበት ዘዴ፤ በአብዛኛው የገንዘብ ህትመትና የዋጋ ንረት እንደሆነ ጥናቱ ያስረዳል። በገንዘብ ህትመትና በዋጋ ንረት አማካኝነት መንግስት የሚያገኘው ጥቅም፤ seigniorage እንደሚባልም ይገልፃሉ ምሁራኑ። የአገራችን የዋጋ ንረትም ከዚህ የተለየ አይደለም።

ከ2000 አ.ም ጀምሮ ስለነበረው የዋጋ ንረት የአፍሪካ ልማት ባንክ ያወጣው የጥናት ፅሁፍ፤ ይህን እውነታ በግልፅ ያሳያል። Inflation Dynamics in selected East African countries: Ethiopia, Kenya, Tanzania and Uganda በሚል ርእስ የሰፈረው ጥናት፤ አራት የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በማነፃፀርና እስካለፈው ጥር ወር ድረስ የአምስት አመታት መረጃዎችን በመመርመር የቀረበ ነው። የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በአመዛኙ ከመጠን ባለፈ የገንዘብ ህትመትና ስርጭት ሳቢያ የተከሰተ እንደሆነ የሚገልፀው የአፍሪካ ልማት ባንክ ጥናት፤ መንግስት ወጪዎቹን ለመሸፈን የገንዘብ ህትመትን እንደሚጠቀም ጠቁሟል።

የአገራችንን የዋጋ ንረት በአለም ገበያ እና በሌሎች ምክንያቶች ላይ ማሳበብ ብዙም አያዋጣም። በአለም ገበያ የሚታየው የነዳጅ እና የእህል ዋጋ ንረት፤ በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትሉት ተፅእኖ ከ15 በመቶ እንደማይበልጥ የአፍሪካ ልማት ባንክ ጥናት የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ በአለም ገበያ አሁን ያለው የእህልና የነዳጅ ዋጋ፤ የዛሬ አራት አመት ከነበረበት ደረጃ በታች እንጂ በላይ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የሸቀጦች ዋጋ የዛሬ አራት አመት ከነበሩበት ደረጃ ከእጥፍ በላይ ሄደዋል።

በጥቅሉ የኢትዮጵያ የአመታት የዋጋ ንረት ሲታይ፤ ግማሽ ያህሉ (52 በመቶው) ከመንግስት የገንዘብ ህትመትና ስርጭት የሚመነጭ እንደሆነ የአፍሪካ ልማት ባንክ ጠቅሶ፤ መፍትሄውም በመንግስት እጅ እንደሆነ ይገልፃል። መንግስት፤ ወጪዎቹን ከቀነሰና ቅጥ ያጣ የገንዘብ ህትመትን ካስወገደ፤ የዋጋ ንረቱ ይቃለላል። መንግስት ግን ፈቃደኛ ባለመሆኑ፤ የዋጋ ንረቱ (በ2002 ረገብ ከማለቱ በስተቀር)፤ ይሄውና አምስት አመቱን እየተባባሰ ነው።

የአለም ባንክ ተወካይ ኢትዮጵያን በሚመለከት ሲናገሩ፤ አምና ብቻ እጅግ ከፍተኛ የብር ህትመት ከመከናወኑ የተነሳ፤ የአገሪቱ የገንዘብ መጠን በ50 በመቶ እንደጨመረ ገልፀዋል። ታዲያ የዋጋ ንረት እየጦዘ ቢመጣ ምኑ ይገርማል? ከ2003 ወዲህ የዋጋ ንረቱ እንዴት እንደባሰበት ተመልከቱ። የብሄራዊ ባንክ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፤ የዋጋ ንረት በጥር ወደ 32 በመቶ እንደቀነሰ ቢገልፅም፤ ይሄ ራሱ በአለም ደረጃ የሚጠቀስ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ነው።

ይህም ብቻ አይደለም። ከጥር ወር ወዲህ ያለውን መረጃ ከስታትስቲክስ ባለስልጣን የየካቲት ወር ሪፖርት ማየት ይቻላል። የዋጋ ንረቱ ወደ 36.3 በመቶ ጨምሯል። የምግብ ሸቀጦች ደግሞ ከአምናው የካቲት ወር ጋር ሲነፃፀሩ፤ ከ47 በመቶ በላይ ዋጋቸው ንሯል። የዛሬ አምስት አመት ከነበረው ዋጋ ጋር ካነፃፀርነውማ፤ የዋጋ ንረቱ ይዘገንናል። የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በ210% ገደማ ጨምሯል። የካቲት 1999 አ.ም፤ በአንድ ሺ ብር የምናሟላው የወር አስቤዛ፤ ዛሬ 3100 ብር ገደማ ይፈጅብናል። በሌላ አነጋገር፤ ያኔ ሶስት ኪሎ ለመግዛት ያስችለን የነበረ ገንዘብ፤ ዛሬ አንድ ኪሎ ለመግዛት እንኳ ያቅተዋል።

እንዲያም ሆኖ፤ መንግስት የዋጋ ንረቱን በሌሎች ምክንያቶች ለማሳበብ ከመሞከር ባይቆጠብም፤ በየአመቱ የዋጋ ንረቱን እንደሚቆጣጠርና ከ10 በመቶ በታች እንደሚያወርደው ሲናገር እንሰማለን። በተለይ ደግሞ፤ የአምስት አመት የትራንስፎርሜሽንና የእድገት እቅድ በ2002 ክረምት ላይ ይፋ ሲደረግ፤ መንግስት የዋጋ ንረቱን እንደሚቆጣጠር ቃል ገብቶ ነበር። የእቅድ ሰነዱ ውስጥም በግልፅ ሰፍሯል።

ቁጥብነትና ጥንቃቄ በተሞላበት የገንዘብ ፖሊሲ አማካኝነት የዋጋ ንረትን መቆጣጠር እንደሚቻል የሚገልፀው ይሄው ሰነድ፤ በአምስቱም አመታት የዋጋ ንረቱ ከ10 በመቶ በታች እንዲሆን ይደረጋል ይላል። ግን አልተደረገም። ከወር ወር ቢታይ፤ ቢታይ... ጭራሽ በ2003 የዋጋ ንረቱ እየባሰበት፤ ነሃሴ ላይ ወደ አርባ በመቶ ደረሰ። የገንዘብ ህትመቱም የዚያኑ ያህል ተጧጥፏላ። የ2004ንም እያየነው ነው። ከአዝመራ ወቅት ጋር፤ እንደ ወትሮው ከጥቅምት እስከ ጥር ድረስ የዋጋ ንረቱ እንዲረጋጋ ቢጠበቅበትም፤ ከሰላሳ በመቶ በታች አልወረደም፤ አሁን ደግሞ እየባሰበት መጥቷል። መንግስት፤ በትራንስፎርሜሽንና በእድገት እቅዱ ላይ የገባውን ቃል ተግባራዊ አላደረገም። ምንድነው ችግሩ?

የብቃት ችግር ነው?

አምስት አመት ሙሉ አገሬውን በዋጋ ንረት ማሰቃየት (የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር አለመቻል) እጅግ ከባድ ጥፋት መሆኑ አያከራክርም። ነገር ግን፤ የብቃት ችግር ነው ለማለት ያስቸግራል። በሌሎች ስራዎች ላይ የብቃት ችግር ሊነሳ ይችላል። የዋጋ ንረት ላይ ግን ...

በእርግጥ፤ ለምሳሌ፤ የዋጋ ንረት ከሶስት በመቶ በላይ እንዳይወጣ የሚከለክል በህግ የታወጀባቸው አገራት ውስጥ፤ የብቃት ጉዳይ ቢነሳ ተገቢ ነው። የዋጋ ንረቱ ከ2.9 ወደ 3.5 በመቶ አለፍ ካለ፤ የገንዘብ ፖሊሲውን እንዲመራ ሃላፊነት የተሰጠው ባለስልጣን፤ ብቃት የለህም ተብሎ ይባረራል። ከአንድ በመቶ በታች የሆኑ አነስተኛ ለውጦችን መቆጣጠር፤ ብቃትን ይጠይቃል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን፤ የዚህን ያህል መራቀቅ አልናፈቀንም። ሌላው ቢቀር እንኳ፤ የዋጋ ንረትን ከአስር በመቶ በታች እንዲሆን የማድረግ ጉዳይ ነው የቸገረን። ይሄ ደግሞ ማንኛውም መንግስት ሊያደርገው ይችላል።

ማንኛውም መንግስት፤ ቢያንስ ቢያንስ ቅጥ ካጣ የብር ህትመትና ስርጭት ከተቆጠበ፤ የአገሪቱን የብድር አቅርቦት ለብቻው ከማግበስበስ ከተቆጠበ ... በቃ የዋጋ ንረትን ማውረድ ይችላል። ያን ያህል ከባድ ጉዳይ አይደለም። ያን ያህልም ብቃት አያስፈልገውም። ታዲያ ምንድነው ችግሩ?

“ዜጎች ምንም አያመጡም”

“መንግስት፤ የዋጋ ንረቱን ለማውረድ ፈቃደኛ የማይሆነው፤ ዜጎቹን ስለማይፈራ ነው” የሚል ምክንያት ሊቀርብ ይችላል። በእርግጥም፤ መንግስት ዜጎቹን እንደማይፈራ ኢህአዴግ ራሱ የሚያምንበት ሳይሆን አይቀርም። ኢህአዴግ፤ አልፎ አልፎ፤ “መንግስት ተነፃፃሪ ነፃነት አለው” የሚል አባባል ይጠቀማል። ምን ማለት መሰላችሁ? አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ፤ መንግስት ከህዝብ ቁጥጥር ውጭ፤ የህዝቡን ተቃውሞ ሳይፈራ እንዳሰኘው ውሳኔዎችን ማሳለፍና ተግባራትን መፈፀም የሚችልበት ሃይል አለው እንደማለት ነው።

ይህን አባባል ተከትለን ከሄድን፤  አብዛኛው ዜጋ በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት ቢማረር እንኳ፤ ምንም አያመጣም ወደሚል ሃሳብ ልናመራ እንችላለን። ግን፤ ዜጎችን ቸል ማለት፤ ለዜጎችን ሃሳብና አቤቱታ ደንታ ቢስ መሆን ይቻላል? ማለቴ... በየአምስት አመቱ ምርጫ ይካሄድ የለም እንዴ? ዜጎች በምርጫ ጊዜ ከስልጣን ቢጥሉትስ?

እውነትም፤ የአገራችን ምርጫ ገና ጉልህ የፖለቲካ ዋጋ ያልተሰጠው ቢሆንም፤ መንግስት በምርጫ ወቅት ዜጎችን በመጠኑ ይፈራል። የ2002ቱን ምርጫ ተመልከቱ። ከ2000 ጀምሮ ሲባባስ የመጣው የዋጋ ንረት፤ በፍጥነት እንዲረጋጋና ከአስር በመቶ በታችን እንዲሆን የተደረገው በ2002 ነው - የግንቦቱ ምርጫ ከመድረሱ በፊት። ታዲያ ምርጫ በማይኖርበት አመትስ? ያው ወደ ቅድሙ ሃሳብ ተመልሰን፤ “ዜጎች በኑሮ ውድነት ቢማረሩ እንኳ፤ ቢበዛ ቢበዛ ወደ አረብ አገራት ይሰደዳሉ እንጂ ምንም አያመጡም” ልንል ነው?

መንግስት እንዲህ የማያስብ ከሆነ፤ ለምን ዜጎችን የሚያማርር የዋጋ ንረትን ይፈጥራል? የዜጎችን እሮሮ ሰምቶስ፤ ለምን የዋጋ ንረቱ እንዲወርድ አያደርግም? መቼም፤ በዋጋ ንረት የዜጎችን ኑሮ እየሸረሸሩ መቀጠል፤ ከእሳት ጋር እንደመጫወት መሆኑን አያጣውም። ታዲያ ለምን? መንግስት፤ በትራንስፎርሜሽንና በእድገት እቅዱ ላይ የገባውን ቃል ተግባራዊ የማያደርገው ለምንድነው? ጥንቃቄና ቁጥብነት በተሞላበት የገንዘብ ፓሊሲ፤ የዋጋ ንረትን ከአስር በመቶ በታች አደርጋለሁ በማለት በእቅዱ ውስጥ ቃል ገብቶ እንደነበር በጋራ የገልፁት አይኤምኤፍ እና ዎርልድ ባንክ፤ በተግባር የሚታየው ግን ተቃራኒው እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች፤ Joint Staff Advisory Note on the Growth and Transformation Plan በሚል ርእስ ባቀረቡት ሰነድ እንደገለፁት፤ በመንግስት የተገባው ቃል እውን ካለመሆኑም በተጨማሪ፤ የዋጋ ንረቱ ወደ አርባ በመቶ እየተጠጋ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። የዋጋ ንረቱ ዋነኛ መንስኤ ምን እንደሆነ ባለሙያዎቹ ሳይጠቅሱ አላለፉም። መንግስት ወጪዎቹንና እዳዎቹን ለመሸፈን፤ አላግባብ የገንዘብ ህትመትን በሰፊው በመጠቀሙ ለዋጋ ንረት መንስኤ እንደሆነ የባለሙያዎቹ ሰነድ ያስረዳል (ገፅ 3)። Ethiopia currently is experiencing acceleration of inflation close to 40 percent largely due to an inappropriate monetary policy, driven by heavy monetary financing by the public sector.

የአይኤምኤፍ እና የዎርልድ ባንክ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ መንግስት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ በትራንስፎርሜሽንና እድገት እቅዱ ውስጥ ቃል ቢገባም፤ ተግባራዊ አልሆነም ከማለት አልፈው፤ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም ብለዋል። እቅዱ ራሱ የዋጋ ንረቱ እንዲቀጥል ያደርጋል ይላሉ ባለሙያዎቹ።

የመንግስት እቅድ፤ የግል ኢንቨስትመንትንና ቢዝነስን ቸል እንደሚል የገለፁት ባለሙያዎች፤ ከእርሻ ውጭ ያለው ኢኮኖሚ በአብዛኛው የመንግስት ድረሻ እንዲሆን የሚያደርግ እቅድ ነው ብለውታል። መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማስፋፋት በርካታ ፕሮጀክቶችን እንደጀመረና እንደወጠነ አያከራክርም። ሚስጥር አይደለም። እናም፤ ለዚህ ሁሉ ተጨማሪ ፕሮጀክት ብዙ ወጪ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎቹ ጠቅሰው፤ መንግስት ከልክ በላይ የሆኑትን ወጪዎችና እዳዎች ለመሸፈን ሲል፤ ለዋጋ ንረት መንስኤ መሆኑን ይቀጥላል ብለዋል።

 

 

Read 3765 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 07:35