Sunday, 28 April 2024 20:57

ለአቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም ዛሬ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 • ገዳሙን ለመታደግ 100 ሚ.ብር ያስፈልጋል


        ለአቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም፣ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 10  ሰዓት ጀምሮ፣ በካፒታል ሆቴል ዓለማቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር የሚካሄድ ሲሆን፤ገቢው በገዳሙ ይዞታ ላይ ለሰፈሩ ነዋሪዎች ካሣ በመክፈል ይዞታውን ለገዳሙ ለማስመለስ ነው ተብሏል፡፡ የገዳሙ ገቢ ማሰባሰቢያ ኮሚቴ እንደገለጸው፤ ገዳሙን ለመታደግና ለማስፋፋት በአጠቃላይ 100 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡
 ገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል የአንድነት ገዳም፣ በ1574 የተመሰረተና የጻዲቁ አባት አቡነ ሐራ ድንግል ገድልና ገቢረ ተዓምራት የሚካሄድበት ገዳም ነው - ይላሉ የገዳሙ መነኮሳት፡፡
ከ400 ዓመት በላይ ታሪክ ያለው ይህ ትልቅ ገዳም በሰሜን ጎጃም፣ ባህርዳር ዙሪያ የሚገኝ ሲሆን፣ ጻዲቁ አቡነ ሐራ ድንግል፣ ከፈጣሪያቸው በተገባላቸው ቃልኪዳን መሠረት፣ ደዌን ሲፈውሱና ተዓምራትን ሲሰሩ የቆዩበትና አሁንም የሚሰሩበት ጥንታዊ ገዳም መሆኑን፣ የገዳሙ ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ባወጣው  መግለጫ ጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ገቢረ ተዓምር የሚሰራበት ታሪካዊ ገዳም፣ ትልቅ ችግር እንደተጋረጠበት መነኮሳቱ ተናግረዋል፡፡
“ለፈውስና ለድህነት ከመላው አገሪቱ ወደ ገዳሙ የሚመጡ ምዕመናን ድህነትና ፈውስ ካገኙ በኋላ፣ ገዳሙን ተጠግተው ቤት በመሥራት እዚያው እየኖሩ፣ ገዳሙ ይዞታውን እየተነጠቀ ከመጣበቡም በላይ፣ የገዳሙን ቅድስና የሚያረክሱ ተግባራት እየተፈጸመበት ይገኛል፡፡”  ይላል፤ የኮሚቴው መግለጫ፡፡
የገዳሙ መነኮሳት የታሪክ ዶሴና ማስረጃ ላይ ተንተርሰው እንደሚናገሩት፤ ዓጼ ዮሐንስ በነቀርሳ ተይዘው በአቡነ ሐራ ድንግል ጸበል በመዳናቸው ነበር ለገዳሙ የአንድ ሰዓት የእግር መንገድ ያህል ስፋት ያለው ቦታ ለገዳሙ የሰጡት፡፡ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ በገዳሙ 800 የሚደርሱ መናንያን እንደነበሩ የሚያስታውሱት መነኮሳቱ፤ በወቅቱ “መሬት ላራሹ” የሚል አዋጅ በመታወጁ የገዳሙን ይዞታ አርሶ አደሮች እየተቆጣጠሩት እንደመጡና መናንያኑ ገዳሙን ጥለው መኮብለላቸውን ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በገዳሙ ይዞታ ላይ ከ250 በላይ አባወራዎች ሰፍረው እንደሚገኙ የሚገልጹት መነኮሳቱ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ለመንግሥት በተደጋጋሚ አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ፣ መንግሥት ነዋሪዎቹን አንስቶ ሌላ ቦታ ለማስፈር ፈቃደኛ ቢሆንም፣ ለነዋሪዎች ካሣ ለመክፈል በጀት እንደሌለው በመግለጽ፣ ገዳሙ ካሣውን እንዲከፍል መወሰኑን ይናገራሉ፡፡
ሆኖም የሚከፈለው ካሣ ከገዳሙ አቅም በላይ በመሆኑ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል የሚለው  የገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም የገቢ ማሰባሰቢያ ኮሚቴ፤ ባለፈው ሐሙስ  በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ፣ ስለ ገዳሙ አሁናዊ ሁኔታና ስለ ገቢ ማሰባሰቢያ   መርሃ ግብሩ  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተነገረው፣ የአማራ ክልል ካቢኔ ለገዳሙ ሁሉንም ይዞታውን ባይሆንም 60 ሄክታር የሚደርስ ቦታ እንዲመለስለት የወሰነ ሲሆን፤ ገዳሙ በበኩሉ ለአርሶ አደሮቹ የሚገባቸውን የመሬት ካሣ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡  ይህን የመሬት ካሣ ለመክፈልና ለገዳሙ የማስፋፊያ ልማት ለማከናወን፣ ዛሬ  ቅዳሜ ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል፣ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት የሚቆይ  ዓለማቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር እንደሚያካሂድ  ኮሚቴው  አስታውቋል፡፡ ለአርሶ አደሮቹ የመሬት ካሣውን ለመክፈልና የገዳሙ ይዞታ ከተለቀቀ በኋላ በሥፍራው ለሚከናወኑ ልማቶች በአጠቃላይ 100 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው የገለጸው የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው፤ በመላው ዓለም የሚገኙ የቤተክርስትያን ልጆችና የጻድቁ አቡነ ሐራ ወዳጆች በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ በንቃትና በትጋት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በገዳሙ የሚገኙ መናንያን ቁጥር 5ሺ እንደሚደርሱና በጾም ወቅት የጸበልተኛው ቁጥር ከ50 ሺ በላይ መሆኑን የጠቆመው  የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው፤ እኒህን ሁሉ በአግባቡ የሚያስተናግድ በቂ መጠለያና የልማት ሥራዎች ማከናወን አስፈላጊ እንደሆነ በአጽንኦት ተናግሯል፡፡


Read 689 times