Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 December 2011 09:17

የኢህአዴግ ወንድም - “የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ”?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአንድ ፓርቲ አገዛዝ እንደ ደርግ ፀረዲሞክራሲ ነው - ኢህአዴግ
የቻይና የአንድ ፓርቲ አገዛዝስ?
ኢህአዴግና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ በካድሬ ስልጠናና ይተባበራሉ
ለተቃዋሚችስ የውጭ ድጋፍ ይፈቀዳል?
የኢህአዴግና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ወዳጅነት አሳሳቢ እንደሆነ የሚጠቅስ ፅሁፍ፤ ባለፈው ሳምንት ጋዜጣ ሳነብ አንድ ሁለት ጥያቄዎችን ጫረብኝ። ከዚያ በፊት ግን፤ “ወዳጅነት” የሚለው ቃል መሻሻል ይኖርበታል።


የቻይና ባለስልጣናት አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት፤ ኢህአዴግና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ከወዳጅነትም በላይ ወንድማማች እንደሆኑ ተገልጿል። የኢዜአ የጥቅምት 29 ቀን ዘገባ ማየት ይቻላል። ወንድማማችነት ብቻም አይደለም። “የሁለቱ ወንድማማች ፓርቲዎች ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል” ይላል ዘገባው።
በእርግጥ፤ ከ2002 ምርጫ በኋላ በኢህአዴግ መፅሄት የታተመውን አቋም ያየ ሰው፤ ኢህአዴግና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ፤ አይንህ ለአፈር የተባባሉ ያመረሩ ፀበኞች ሊመስሉት ይችላሉ። መቼም፤ ቻይና ውስጥ ተፎካካሪ ወይም ተቃዋሚ የሚባል ፓርቲ እንደሌለ ታውቃላችሁ። ኮሙኒስት ፓርቲው ነው፤ በብቸኝነት አገሪቱን የሚገዛት - የአንድ ፓርቲ ስርአት ይሉታል።
በኢህአዴግ የሚታተመው መፅሄት ውስጥ የሰፈረው የኢህአዴግ አቋም የአንድ ፓርቲ ስርአትን ክፉኛ ያወግዛል፤ ለዚያውም እየደጋገመ። ያኔ፤ ኢህአዴግ በምርጫው ከ99 በመቶ በላይ ሲያሸንፍ፤ “የአንድ ፓርቲ ስርአት ወይም አምባገነንነት እየሰፈነ ነው” የሚል ትችት ይቀርብበት እንደነበር ታስታውሱ ይሆናል። እስካሁን ትችቱ አልተቋረጠም። ኢህአዴግ ይህን ትችት በመቃወም፤ አቋሙን በመፅሄቱ ሲገልፅ ምን ምን እንዳለ ተመልከቱ።
አንድ ፓርቲ ለተከታታይ ስልጣን መያዙ በዚያ ላይ ከ99 በመቶ በማሸነፍ የአገሪቱን ስልጣን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩ፤ “የአንድ ፓርቲ ስርአት ሰፈነ” አያስብልም? በጭራሽ አያስብልም በማለት ይከራከራል - የኢህአዴግ መፅሄት።
በኢትዮጵያ ገዢውን ፓርቲ መተቸት በህግ የተረጋገጠ የዜጎች ነፃነት እንደሆነ መፅሄቱ ጠቅሶ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመመስረት በምርጫ መወዳደርም ህጋዊ እውቅና የተሰጠው መብት ነው ይላል። አንድ ፓርቲ ለተወሰነ ጊዜ ገናና ወይም አውራ ሆኖ በስልጣን ሊቆይ ቢችልም፤ በኢትዮጵያ ያለው ስርአት ግን የመድብለ ፓርቲ ስርአት ነው በማለት መፅሄቱ ይከራከራል - ይህንንም “የአውራ ፓርቲ ስርአት” በማለት ሰይሞታል። የገናና ፓርቲ ስርአት እንደማለት ነው። ታዲያ የአንድ ፓርቲ ስርአትስ?
የአንድ ፓርቲ ስርአት በሰፈነበት አገር፤ የዜጎች የመደራጀት መብት እንደሚገደብ መፅሄቱ ጠቅሶ፤ የመንግስት ስልጣን ማን እንደሚይዝ የሚወሰነውና መንግስት የሚሰየመው በህዝብ ምርጫ አይደለም ይላል። ታዲያ እንዴት ነው መንግስት የሚሰየመው? “ኢዴሞክራሲያዊ በሆነ ህገመንግስት የሚሰየምበት ፀረዴሞክራሲያዊ ስርአት ነው” በማለት የአንድ ፓርቲ ስርአትን ያወግዛል - የኢህአዴግ መፅሄት። የነሃሴ 2002 እትም ገፅ 31ን ተመልከቱ። ቀጥሎም እንዲህ ይላል...
“ከገዢው ፓርቲ በስተቀር... ሌላ ፓርቲ እንዲደራጅ ስለማይፈቀድለትና ተደራጅቶ ከተገኘም እንደወንጀለኛ ስለሚቆጠር፤በፓርቲዎች መካከል የሚሄድ የምርጫ ውድድር የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ በህገመንግስት የተሰየመውን ብቸኛውን ፓርቲ ሂስ ማድረግ ራሱ ወንጀል ስለሆነ... የመደራጀት መብት ብቻ ሳይሆን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትም ይታፈናል፡፡ እናም የአንድ ፓርቲ ስርአት ማለት፤ ፍፁም ኢዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርአት ማለት ነው”
ትክክለኛ ሃሳብ ነው፤ “ይበል” ያሰኛል። የኢህአዴግ መፅሄት ግን በዚህ ብቻ አላበቃም። የአንድ ፓርቲ ስርአት ላይ ተጨማሪ ውግዘቶችን አካትቷል። “የአንድ ፓርቲ ስርአት በኢትዮጵያ ተመልሶ ይመጣል ወይም መጥቷል ማለት፤ ዞሮ ዞሮ የደርግ ኢሠፓ ስርአት ተመልሶ መጥቷል ወይም ይመጣል ማለት ነው” ይላል የኢህአዴግ መፅሄት።
እዚህ ላይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ፓርቲ ገናና ሆኖ የሚታይበት ስርአትና የአንድ ፓርቲ ስርአት ዝምድናቸው ምንድነው? ብለን መጠየቅ እንችላለን። “በመሰረታዊ ባህሪያቸው ተፃራሪና የማይመሳሰሉ” ናቸው በማለት ይመልሳል የኢህአዴግ መፅሄት።
በአጭሩ፤ የአንድ ፓርቲ ስርአት፤ የዜጎችን የሃሳብ ነፃነት የሚጥስ፤ የመደራጀት መብትን የሚገድብ፤ ከዚያም አልፎ እንደወንጀል የሚቆጥር፤ ኢዴሞክራሲያዊ ህገመንግስትን የሚጭን፤ ፀረዴሞክራሲያዊ ስርአት ነው... ደርግ ማለት ነው... የዴሞክራሲ ተፃራሪ ማለት ነው... እነዚህ ሁሉ በኢህአዴግ መፅሄት ውስጥ የተዘረዘሩ ናቸው።
ታዲያ ይሄ ሁሉ ውግዘት፤ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲን አይመለከትም? የአንድ ፓርቲ ስርአት ዋነኛ ምሳሌ ነው የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ። ኢህአዴግ በመፅሄቱ በገለፀው አቋም መሰረት፤ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ጋር ፀብ መጀመር አለበት ማለቴ አይደለም። እንዲያው፤ “ተፃራሪያችን ነው” ብሎ ለፀብ መነሳት አላስፈላጊ ቢሆንም፤ ከዚያ ሁሉ ውግዘት በኋላ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ጋር መወዳጀት ምን ይባላል?
ወይስ በመፅሄቱ የተገለፀው አቋምና የቀረበው ውግዘት፤ ለይምሰል ነው? ኢህአዴግ፤ በአጀማመሩ የከረረ ኮሙኒስት እንደነበረ ስናስታውስ፤ አሁንም ስብሰባ ላይ ጓድ... ጓድ ሲባባሉ ስንሰማ፤ “ይሄ ነገር እንዴት ነው?” ብለን ብንጠራጠር አይገርምም። ለማንኛወም፤ “የሁለቱ ፓርቲዎች ወዳጅነት ወይም ወንድማማችነት” ... ይህን ጥያቄ ጭሮብኛል ለማለት ፈልጌ ነው።
ሁለተኛው ጥያቄም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። “የሁለቱ ወንድማማች ፓርቲዎች” የጋራ ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን በመግለፅ ኢዜአ ዘገባውን ሲቀጥል፤ ሁለቱ ፓርቲዎች “የካድሬ ሥልጠና እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ” እንደተስማሙ ይገልፃል። ትብብር፤ የካድሬ ስልጠና ...?
የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ከውጭ አገር በቀጥታ ድጋፍ ማግኘት እንደማይችሉና በህግ እንደተከለከለ በተደጋጋሚ የምንሰማው፤ የምርጫ ጊዜ ሲቃረብ ነው። ከውጭ የሚመጣ ድጋፍ ካለ፤ ለምሳሌ የገንዘብ ድጋፍ ቢኖር፤ የምርጫ ቦርድ ነገርዬውን ይረከብና ለፓርቲዎች እንደሚያከፋፍል ሲገለፅ መስማታችሁ አይቀርም።
የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲና የኢህአዴግ ጉዳይስ? እንግዲህ፤ “የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የካድሬ ስልጠና፤ ከገንዘብ ድጋፍ ይለያል” ካልተባለ በቀር፤ ወይም “ኢህአዴግ ስልጠና የሚቀበል ሳይሆን ስልጠና የሚሰጥ ነው” ካልተባለ በቀር፤ “ህጉ ኢህአዴግ ላይ አይሰራም ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ያጭራል።
ለመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችስ፤ ከውጭ አገር መንግስታት ወይም ተቋማት ድጋፍ ለማግኘት ይፈቀድላቸዋል? አይፈቀድም። የገንዘብና የስልጠና ድጋፍ ይቅርና፤ የንግግር ድጋፍ ራሱ ለፈተና ሲዳርጋቸው አይተናል - “የውጭ ሃይል ተላላኪ”፤ “የውጭ ሃይል ጉዳይ አስፈፃሚ” የሚሉ ውግዘቶችን ያመጣባቸዋል።

 

Read 2178 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 09:19