ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ በቅርቡ ለቅቀዋል ሲባል የነበሩትን የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመተካት፣ ለኩባንያው አዲስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንደተሾመለት አስታወቀ፡፡
ቤልጂየማዊው አዲሱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዊልያም ቫንሀለፑተን፣ የቀድሞውን ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሶሳን በመተካት የተሾሙ መሆናቸውን ኩባንያው በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርጓል፡፡ አዲስ የተሾሙት ሥራ አስፈፃሚ በዘርፉ ትልቅ እውቀትና የ25 ዓመታት ልምድ ያላቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሳፋሪኮም በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከ2 ሺህ በላይ የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች እንዳሉት የተናገሩት አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፤ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ይህንን ወደ 7 ሺህ ለማሳደግ ማቀዱን አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት 35 በመቶ የኢትዮጵያን ክፍል በኔትወርክ መሸፈን መቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ ይህንንም በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ ለማሳደግ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት ትርፍ አግኝቷል ለማለት ከባድ ነው ያሉት ሥራ አስፈፃሚው፤ በቀጣዮቹ ሁለትና ከዛ በቀረቡ ዓመታት ውስጥ ወደ ትርፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው በኢትዮጵያ ከ900 በላይ ሰራተኞች ያሉት መሆኑን የተናገሩት አዲሱ ሥራ አስፈፃሚ፤ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት 500 ለሚሆኑ ሰዎች ቀጥተኛ የስራ እድል እንደሚፈጥርም አመልክተዋል፡፡