Friday, 17 November 2023 19:35

ኢትዮቴሌኮም፤ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለትንና የነዳጅ ኩፖንን ዲጂታል ለማድረግ የሚያስችሉ ሶሉሽኖችን አስተዋወቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

•  የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስን ዲጂታላይዝ የሚያደርጉ መላዎችንም አስጀምሯል


ኢትዮ ቴሌኮም፤ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር በመተባበር፣ የነዳጅ አቅርቦት የአሰራር ስርዓትንና የነዳጅ ኩፖንን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል እንዲሁም ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ከመንገድ ደህንነትና ኢንሹራንስ ፈንድ አገልግሎት ጋር የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አገልግሎትን ዲጂታላይዝ የሚያደርጉ ሶሉሽኖችን በይፋ አስጀምሯል፡፡


ኩባንያው በዛሬው ዕለት የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለትን በተማከለ የዲጂታል ሥርዓት ለማከናወን የሚያስችል የነዳጅ አቅርቦት ትስስር አስተዳደር ሶሉሽን /Fuel Supply Chain Management System/ በማበልጸግ ተግባራዊ ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህም ሶሉሽን በነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ዘልማዳዊ የአሰራር ሂደቶችንና በወረቀት ላይ የተመሰረቱ አሰራሮችን ለማዘመን፣ ግልጽነት ያለው የነዳጅ አቅርቦትና ግብይትን ለማስፈን፣ ትክክለኛ ዳታ በወቅቱ ለማግኘት እንዲሁም በሂደቱ ውስጥ ለሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ግዢ የሚውል የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አመለክቷል፡፡


በተጨማሪም፤ የዘርፉ ተዋናዮች ማለትም የነዳጅ ጣቢያዎችና ቀጥተኛ ተጠቃሚ ደንበኞች፣ የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች፣ የኢትዮጵያ የፔትሮሊየም አቅራቢ ድርጅት እንዲሁም የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አጠቃላይ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል፣ የነዳጅ አቅርቦት ትዕዛዝን በዲጂታል መላ ለመስጠት/ለማቅረብ፣ ትዕዛዝ ለመቀበል እንዲሁም አስፈላጊውን ዳታ በወቅቱ ለማግኘት (real-time data access) ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡


በሌላ በኩል፤ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የማንዋል የነዳጅ ኩፖን ሽያጭ አገልግሎት አሰራርን ወደ ወረቀት-አልባ የዲጂታል ኩፖን በመቀየር አዲሰ አሰራር ያስተዋወቀ ሲሆን፤ ይህም ዘመናዊ አሰራር የነዳጅ ኩባንያዎች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን፣ የነዳጅ ማደያዎችን የአገልግሎት አማራጭ ለማሳደግ፣ ግብይቶችን ለማሳለጥ፣ የገንዘብ ፍሰትን ለማሻሻል፣ የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የተጠቃሚዎችን መጠን ለመጨመርና ሽያጭ ለማሳደግ፣ የዲጂታል ኩፖን ዳታዎችን ለመቆጣጠር እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ ግብይት ለማካሄድ የሚያስችል የዲጂታል ሶሉሽን ማስተዋወቁን በመግለጫው አመልክቷል፡፡   


በተመሳሳይ ሁኔታ፤ ኩባንያው የሦስተኛ ወገን የመድን አገልግሎትን በዲጂታል ስርአት አማካኝነት ለመስጠት የሚያስችል ሶሉሽን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ከመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ ጋር በመተባበር ይፋ አድርጓል። ይህም የኢንሹራንስ አገልግሎት አሰጣጥ ተግዳሮቶችን በማስቀረት በተለይም የተማከለ መረጃ እንዲኖር ለማስቻል፣ ክፍያን በወቅቱና በዲጂታል መንገድ ለማከናወን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል፣ የተሟላ ሪፖርት በወቅቱ ለማግኘትና ወረቀት-አልባ አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል፡፡


በተጨማሪም ይህ የዲጂታል ሶሉሽን ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ ተገልጋዮች የሚያደርጉትን ምልልስና ውጣ ውረድ በማስቀረት ባሉበት ሆነው በቀጥታ (online) እንዲስተናገዱ ለማድረግ፣ በኢንሹራንስ ሂደቶች ውስጥ የሚከሰቱትን ተግዳሮቶች ለመቀነስ እንዲሁም የእድሳትና ባለቤትነት ለውጥ አሰራርን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ኢትዮቴሌኮም ጠቁሟል፡፡

Read 1364 times