Saturday, 19 August 2023 20:29

እውነት ግን… ምን ነካን!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው… እንግዲህ እንደ ቀን መቁጠሪያው ከሆነ ‘አዲሱ ዓመት’ እየተቃረበ ነው፡፡ ይሁን ማለት ደግ ነውና “ይሁን፣” ብለናል፡፡ እናላችሁ… እንደ ነገረ ሥራችንና፣ አኳኋናችን ከሆነ ደግሞ… አለ አይደል… በየዘመናቱ ካሳለፍናቸውና ልናስታውሳቸው እንኳን ከማንፈልጋቸው ቀሺም አሮጌ ዓመታት አንዱ የሆነው በ‘ሪሌፕይ’ እየመጣ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰቡ ስህተት ነው ብሎ ማሰቡ፣ በራሱ ስህተት ነው፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) ስሙኝማ፣ የምር እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምን አለ መሰላችሁ ሌላውን ሰው ግራ ለማጋባት ከተፈለገ እኮ የሆነ ነገርን በአጭሩ እቅጯንና ገብስ ገብሷን ከመናገር ይልቅ ዙሪያ ጥምጥም መሄድን የመሰለ አሪፍ ‘ታክቲክና ስትራቴጂ’ የለም፣ “ስህተት ነው ብሎ ማሰቡ በራሱ ስህተት ነው፣” እንደተባለው አይነት፡፡
እናማ…ግን በርከት ካሉ ዓመታት ወዲህ ‘አዲስ ዓመት’ በመጣ ቁጥር በጨፈገገ ስሜትና ዘፍዝፈው እንደረሱት የአውርዱልኝ ሸሚዝ በተሸበሸበ ፊት መቀበሉን እየለመድነው መጥተናል፡፡ እንደቀድሞው ቢሆን እኮ ነገርዬው ለየት ያለ ይሆን ነበር፡፡ (‘እንደቀድሞው’ የሚለውን ቃል ከቅርብ ወራት እስከ አስራ ምናምነኛው ከፍለ ዘመን መሳብ ይቻላል፡፡ ‘እውነት’ የሚሏት ነገር ግልጽና ነጥራ የወጣች ለማንም የምትታይ መሆኗ ቀርቶ፣ “እንደፈቺዋ” ከሆነች የከረመባት የምድር አካፋይ ውስጥ ነና!)
እውነት ግን…ምን ነካን!
ታዲያላችሁ… “አንተ ሰውዬ አዲስ ዓመት አይደለም እንዴ! ምንድነው እንዲህ ጮርናቄውን እንደነጠቁት ህጻን እንትህነን የጣልከው!” ምናምን ይባል ነበር፡፡ አዲስ ዓመትን በፍሬሽና ፈካ ባለ ገጽታ እንጂ አንደ ‘ዩዝድ’ እቃ ማጨራመት ልክ አልነበረማ!
“እንቁጣጣሽ፣ እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሀል እንምነሽነሽ፤”
ተብሎ የተዘፈነው እኮ አብዛኛው ሰዋችን ምንም ያህል ፈታኝና አስጨናቂ ችግር ውስጥ ቢሆን እንኳን ከዋዜማው ቀናት ጀምሮ ራሱን ዘና አድርጎ፣ ደግ ደጉን እያሰበ ለማሳለፍ ስለሚጥር ነው፡፡ እናማ… ምን ነካን የሚሉ ሰዎች አይደለም አንዴና አስሬ፣ መቶ ጊዜም ግራ ቢገባቸው አይገርምም፣ ብዙ መቶ ግራ የሚገቡ ነገሮች የተፈጠሩብን ወቅት ላይ ነንና! 
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…‘አባየሆሽ’ የሚዘፍኑ ልጆች አሁንም…
ከብረው ይቆዩ፣ ከብረው
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሠላሳ ጥጆች አስረው፤
ምናምን የሚሉትን ስንኞች ይጠቀማሉ እንዴ! አይ የጥጆቹን ነገር እንኳን “ሆድ ይፍጀው፣” እንጂ ሌላ  ምን ይባላል! መጀመሪያ ነገር ‘ጥጃ’ የሚለው ቃል ትርጉም ላይ መስማማት አለብን! አሀ…‘አፕዴትድ’ ሆኖ ለእኛ መረጃው ገና አልደረሰ ይሆናላ! ግን ይሄ “በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው…” የሚለው “የሰው ልጅ ቁጥር በጣም በዝቷል መቀነስ አለበት፣” እያሉ ካሉት፣ ከእነ ቢል ጌትስና ካርል ሽዋብ ከሚባሉት ሰውዬ ጋር ሊያጋጩን ይችላላ! ደግሞ የፀጥታው ምክር ቤት የሚባለውን ቡድን እንደገና በወር አሥራ ምናምን ጊዜ ስብሰባ እንዳይጠሩብን! ባይሆን
ከብረው ይቆዩ፣ ከብረው
የኮንዶ እዳ ከፍለው
ለማኛ እንጀራ በቅተው
ከሹሮ ናፍቆት ወጥተው
ከስድብ ናዳ ተርፈው፣
ምናምን እየተባለ ይስተካከልንማ!
እውነት ግን… ምን ነካን!
ስሙኝማ… አለ አይደል፣ ስለ ራሳችን የፈለግነውን እንበል፣ የፈለግነውን ትርክት እናውራ፣ “ጊዜ ጥሎን እንጂ እንዲህ እኮ አልነበርንም!” ምናምን አንበል፤ ሀቁ ግን ማጅራትንን ጨምድዶ የሚለቀን አልሆነም። እንግዲሀ እውነት፣ እውነቱን እንነጋገር አይደል…. በአሁኑ ጊዝ በአፍሪካም ሆነ በአብዛኛው የተቀረው ዓለም እንደእኛ አይነት ተስፋ በሚያስቆርጡ ብቻ ሳይሆን ሙጥጥ በሚያደርጉ ውስብስብ፣ ጥልፍልፍ ጉዳዮች እግር ተወርች የታሰረ ህዝብ ማግኘት ያስቸግራል። ቤታችን ቁጭ ብለን እኮ ዓለምን በቴሌቪዝን እያየናት ነው፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜያት እኮ…
“አቤት የሩዋንዳውያን አበሳ! እንደው መቼ ይሆን ፈጣሪ ይቅር የሚላቸው!”
“ኮንጎ በቃ እንዲህ ትርምስምሷ እንደወጣ እስከመቼ ልትዘልቀው ነው!” “ሊቢያን የመሰለች ‘ሁሉም ምቹ፣ ሁሉም ዝግጁ’ የሆነባት ዲታ፣ ዶላር የምታስነጥስ ሀገር በዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሱናሚ የተመታች መስላ ትቅር!” …ባዮቹ እኛ ነበርን፡፡ እናማ… ምን ነካን? በነገራችን ላይ “ምን ነካን?” ማለት ደግሞ ምነም ቦተሊካዊ፣ የሴራ ትርክታዊ ቅብጥርሶ ‘አፔንዲክስ’ የሌለውና በዜግታችን ከሁሉም በላይ ደግሞ የእሱ ፍጡራን የሰው ልጆች በመሆናችን ብቻ ልንጠይቀው የሚገባ ነው፡፡
ሌሎቹ ላይ “ጉድ! ጉድ!” እንልባቸው በነበሩ ነገሮች ውስጥ እኛው መሀሉ ዘጭ እያልንባቸው ነው፡፡ ግርም የሚላችሁ ይሄ ሁሉ ችግር በግራና በቀኝ፣ በላይና በታች ቀለበት ውስጥ እየከተተን እያለ ምነው መግባባቱ እንኳን ቢያቅተን እንደው ለሰዓታት እንኳን ቢቀር ለጥቂት ደቂቃዎች “እህ!” እየተባባሉ መደማመጥ ያቃተን ምን አይነቱ አይምሬ ሰፍኖብን ነው ያሰኛል እኮ! የአንዱን ወግን ሃሳብ ማዳመጥ ማለት እኮ ሃሳቡን ማመን፣ መቀበል ማለት አይደልም። ለዚህ ማጠናከሪያ የሚሆን “ለጊዜው ስሙን የረሳሁት…”  ሊባል የሚችል ፈላስፋ ፈልጉልኝማ!) የምር እኮ…  አለ አይደል… እውነተኛ ሃሳቦቻችንና እምነቶቻችን እየተደማመጥን ባልተናገጋርነበት እኮ ነው፣ ‘ብዙዎቻችን ተሳዳቢዎች፣ ብዙዎቻችንም ተሰዳቢዎች!’
እናላችሁ…“ነገሩ ነው እንጂ ጩቤው ሰው አይጎዳም!” ሲባል በተኖረባት ሀገር፣ አሁን ትልቅ የለ ትንሽ የለ፣ ኅጻን የለ አዛውንት የለ፣ ዲታ የለ ቺስታ የለ፣ እውቀት የሰፈረበት የለ ከእውቀት የነጻ የለ! ምን አለፋችሁ…በስድብና በዘለፋ እየታመስንበት ያለ ዘመን ነው፡፡  (ቀደም ሲል ተሳዳቢነት የምንለው ነገር፣ “የእንትን ሰፈር ልጆች እንዴት አይነት ተሳዳቢዎች መሰሉህ! ስድባቸው እኮ አምስት ቀን ተኩል ነው፤ ከሀያ አራቱ ሰዓት አስሩን ወደ እንትን የሚያሯሩጥህ!” ይባል ነበር፡፡ አሁን እንዲህ የስድብ ፋይቭ ስታር ደረጃ ላይ የደረስን ሊመስል!)
እውነት ግን… ምን ነካን!
ብዙዎቻችን ፈራጆች፣ ብዙዎቻችንም ተፈራጆች! (“ሰው ባላወቀው ይፈርዳል፣ እግዜር ባወቀው ይቀጣል!” የምትል አባባል አለች። የእግዜርን ቁጣ በይደር እናቆየውና፣ አንድ ካንሰር ደረጃ የደረሰ የሚመስል ችግራችን ባላወቅነው፣ ብዙዎቻችን ምናልባትም  ማወቅ በማንፈልገው መፍረድና መፈረጅ ነው፡፡
…እኔ የምለው…እነእንትና “እኛ ማንም ላይ አንደርስም፣ ሌሎቹም አይድረሱብን የምትሉት ነገር ‘አግሬድ’ ብታደርጉት መልካም ነው፡፡ አሀ…እንደሱ ብሎ ነገር ኩንታል ጤፍ ወደ ትዌልቭ ታውዘንድ ደረሰባት በሚባልባት ጦቢያችን አይሠራማ! እናላችሁ ይሄኔ ክሬቲቭ በሆነ መንገድ አያንዳንድህ ተፈርጀሀታል! ነገርዬው እኮ “ማን ተፈርጆ ማን ይቀራል!” የተባለ ነው የሚመስለው! ስሙኝማ… ለመረጃ ያህል “አትፍረድ ይፈረድባሀል፣” የሚለው ተረት ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ አልፎበት ይሆን እንዴ! አሀ...የሆነ ጽሑፍ ላይ ተጠቅመንበት ደግሞ “ጥቅስ ናፋቂ!” እንዳንባል ነዋ!)
ብዙዎቻችን አሳዳጆች፤ ብዙዎቻችንም ተሳዳጆች! ብዙዎቻችን ‘ሊቆች’፤ ብዙዎቻችንም ‘ደቂቆች!’  ብዙዎቻችን ቅዱሳን፤ ብዙዎቻችንም እርጉማን! ብዙዎቻችን አንደኞች፤ ብዙዎቻችንም ውራዎች! ነገሩ ሁሉ የሚተረማመሰው ሁሉንም ነገር እየሆንና ለመሆን እየሞከርን ነው እኮ! ሁላችንም ሀቀኞች፤ ሁላችንመ ዋሾዎች! እንዴት ነው ነገሩ…በአንድ ጊዜ አርሴም ማንቼም መሆን ይቻላል እንዴ! “እኛን ግራ ይግባን! የሚሉ አጽናኝ ዘመዶች አጥተን አንጂ ግራ ገብቶናል!
ተነሣ ወንድሜ መንገድ እንቀጥል
እኔም ቅሌን ይዤ አንተም አገልግል፤
የምትል አባባል አለች፡፡ መቼ ይሆን ለጋራ መንገድ፣ ለጋራ ጉዞ፣ ለጋራ ግብ ከልባችን “ተነሣ ወንድሜ…” የምንባባለው!
እውነት ግን…ምን ነካን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 941 times