Saturday, 12 August 2023 00:00

የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ በመንግሥት አመራሮች በተቀሰቀሰ ግጭት ተፈጸመ ያለውን ጥፋትና ውድመት አወገዘ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከነባሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥልጣን መረከቡን ተከትሎ፣ ከክልሉ ዋና ከተሞች አመራረጥ ጋር በተያያዘ በቁጫ የምርጫ ክልል በተቀሰቀሰ አመጽና ረብሻ፣ ከፍተኛ ጉዳትና ውድመት መድረሱን የጠቆመው የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ)፤ ይሄንኑ በመንግሥት አመራሮች የተቀሰቀሰና የተመራ ነው ያለውን አመጽና ረብሻ  በጽኑ አውግዟል፡፡  
ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል አደረጃጀትና ምስረታ ሂደት ጋር ተያይዞ፣ በቁጫ ምርጫ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር አስመልክቶ የቁሕዴፓ አመራሮች፣ ትላንት ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ላይ፣ የኢትዮጵያ  የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ጽ/ቤት አዳራሽ  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
 በየጊዜው ሀገራችን የሚገጥማትን የፀጥታ ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የቁጫ ምርጫ ክልል ሕዝብን እረፍት የሚነሱ ኃይሎች ላይ መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያሰፍን ፓርቲው ጠይቋል፡፡  
ባለፉት ዓመታት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፣ በተለያዩ ዞኖች  ሲነሳ ለቆየው የክልል አደረጃጀት መንግስት ምላሽ እየሰጠ መሆኑን የሚገልጸው ፓርቲው፤ በዚህም  ነባሩ ደቡብ ክልል  ከአራት  በላይ በሆኑ አዳዲስ ክልሎች እንዲዋቀር ተደርጓል ይላል፡፡
”ከእነዚህ አራቱ ክልሎች አንዱ የሆነውና በአሁኑ ወቅት በምስረታ ሂደት ላይ የሚገኘው “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል”፣ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ በተመዘገበው አብላጫ ውጤት፣ 6ቱ ዞኖች እና 5ቱ ልዩ ወረዳዎች በአንድነት በጋራ ክልል ለመተዳደር የወሰኑት ድምፅ በፌዴሬሽን ም/ቤት በመፅደቁ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፣ ክልል ም/ቤት፣ ከሐምሌ 28  እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ የም/ቤት ጉባኤ፣ ለአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል የስልጣን ርክብክብ አድርጓል፡፡” ብሏል፤ ፓርቲው፡፡
 ም/ቤቱ፤አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልልን በ6 ክላስተር ከተሞች የአገልግሎት ተቋማትን ሸንሽኖ በተመረጡ ከተሞች የተደለደሉ የመንግሥት ተቋማትን ዝርዝር ይፋ ማድረጉን ያወሱት የፓርቲው አመራሮች፤ ይሄን  ተከትሎም፣ ሐምሌ 29 ቀን 2015 ዓ.ም፤ “አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል አደረጃጀት የጋሞ ሕዝብን ጥቅም የሚነካ በመሆኑ አንቀበልም” በማለት በቁጫ ምርጫ ክልል፣ በቁጫ ወረዳና በቁጫ ሰላምበር ከተማ አስተዳደር፣ በመንግስት አመራሮች የተመራ የረብሻና አመፅ ቅስቀሳ መደረጉን ይገልጻሉ፡፡
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚና የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የሆኑት የተከበሩ ረ/ፕሮፌሰር ገነነ ገደቡ፣ በአካባቢው የመንግስት አመራሮች የተቀሰቀሰና የተመራ ነው ባሉት አመፅና ረብሻ ስለደረሱት ጥፋቶች ሲያስረዱ፤”የቁጫ ሕዝብን ከወላይታ ዞን፣ ከጎፋ ዞንና ከደቡብ ኦሞ ዞን ሕዝብ ጋር የሚያገናኘውን የፌደራል አስፓልት መንገድ በመዝጋትና የሕዝብን ነፃ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ ወደ ቁጫ ሰላምበር ከተማ ቅዳሜ ገበያ የመጣው ገበያተኛ እንዲበተን፣ የፀጥታ ሃይሎች፣ በገበያተኞች ላይ ወከባና ድብደባ  ፈጽመዋል” ብለዋል፡፡
”በረብሻው ያልተሳተፉ የሰላምበር ከተማ ነዋሪዎች በብሔር እየተለዩ፣ በቁጫ ብሔረሰብ አባላትና በቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች የንግድ ተቋማትና መኖሪያ ቤቶቻቸው ላይ በተፈፀመው የድንጋይ ውርወራ ውድመት ደርሷል” ያሉት የም/ቤት አባሉ፤ ”በረብሻው ከተሳተፉ ወጣቶች መካከልም የአንዱ ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል፤ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰዎች ላይ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎችና በረብሻው በተሳተፉ ወጣቶች እንዲሁም በመንግስት አመራሮች ጥቃት ተፈጽሟል” ብለዋል፡፡
በቁጫ ምርጫ ክልል በመንግሥት ሃላፊዎች የተቀሰቀሰውንና የተመራውን የአመጽና ረብሻ እንቅስቃሴ ፓርቲያችን በፅኑ ያወግዛል ያሉት አመራሮቹ፤በአካባቢው ከፍተኛ ግጭትና ውድመት እንዲደርስ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ከቁጫ ሕዝብና ከፓርቲያችን ለክልሉና ለፌዴራል ፀጥታና ተጠሪ ተቋማት በቀረበው ጥቆማና አቤቱታ፣ የፌዴራል ፀጥታ ኃይል ወደ አካባቢው በፍጥነት ደርሶ ሕዝቡን ታድጎታል ብለዋል፡፡
”የተገኘው አንፃራዊ መረጋጋት አስተማማኝ ደረጃ እስኪደርስና አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል ምስረታ ተካሂዶ በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እስኪሰፍን ድረስ፣ የፌዴራል ፀጥታ ኃይል የሕዝብን ሰላምና ደህንነት እንዲያስጠብቅ በመንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው እንጠይቃለን” ብለዋል፤ አመራሮቹ በመግለጫቸው፡፡
አመፅና ረብሻው በቁጫ ወረዳና በቁጫ ሰላምበር ከተማ አስተዳደር እንዲነሳ የተፈለገው ያለ ምክንያት አይደለም የሚሉት የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሃብታሙ ኃ/ሚካኤል፤ የቁጫን ህዝብ ማህበራዊ ዕረፍት በመንሳት ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል ለመዳረግና አካባቢውን የግጭት ማዕከል በማድረግ፣ የሕዝብን መሰረታዊ  ጥያቄዎች ለመቀልበስ ነው ብለዋል፡፡
የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሌሎች አካባቢዎች ያመጧቸውን ወጣቶች ሳይቀር በዚህ ግጭትና ረብሻ ውስጥ አሳትፈዋቸዋል ያሉት ም/ፕሬዚዳንቱ፤ ግጭቱን በቁጫ የምርጫ ክልል እንዲነሳ ያደረጉትም በቁጫ ብሔረሰብ እንዲሁም በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም በማለም ነው ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
ሐምሌ 29 ቀን 2015 ዓ.ም፣ በቁጫ ወረዳና በቁጫ ሰላምበር ከተማ፣ በመንግሥት አመራሮችና በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም በፖሊስ አባላት በተመራው አመፅና ረብሻ፣ የቁጫ ሕዝብን ከወላይታ፣ ከጎፋና ከደቡብ ኦሞ ዞን ሕዝቦች ጋር የሚያገናኘውን የፌዴራል አስፓልት መንገድ ዘግተውት እንደነበር ያስታወሱት የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት፤ በዚህም ሰላም ወዳዱን የቁጫ ሕዝብ ለዘመናት ጥብቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከፈጠሩ፣ በአንድነትና በፍቅር ከሚኖሩ አጎራባች ሕዝቦች ለመለየትና እነዚህ አካባቢዎች በቁጫ ህዝብ ላይ እንዲነሳሱ በማድረግ፣ ከግጭት ለማትረፍ ታቅዶ የተፈፀመ ነው ብለዋል፡፡
ከክልል በታች ያሉ አደረጃጀቶች፣ ከአዲሱ ክልል ምስረታ በኋላ ምላሽ እንደሚያገኙ በፌዴሬሽን ም/ቤት አቅጣጫ መቀመጡን ያመለከተው ቁሕዴፓ፤ የቁጫ ሕዝብ ብሔር ማንነትና ራሱን በራሱ የማስተዳደር ህገመንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄው ለዘመናት የቆየና ጥያቄው ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ በክልል ደረጃ ምላሽ ማግኘት የሚገባው ጊዜ በማለፉ በይግባኝ ለፌደሬሽን ም/ቤት ቀርቦ ለምላሽ የተለያዩ ጥናቶች ሲደረጉ የቆየበት ከመሆኑ አንጻር፣ ከክልል አደረጃጀት ጥያቄ አስቀድሞ ምላሽ ሊሰጠው ይገባ ነበር ብሏል፤ ፓርቲው፡፡
 በአጠቃላይ በቁጫ ሕዝብ ላይ ተጭነው ለቆዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የፌዴሬሽን ም/ቤት በራሱ ሥልጣንናና ተግባር ስር የነበረውን ኃላፊነት፣ በህግ አግባብም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መመለስ አለመቻሉ በፈጠረው አጋጣሚ የቁጫ ሕዝብ ህገመንግስታዊ መብቶች ተጥሰው፣ በሌላው ወገን ፈላጭ ቆራጭነት፣ ህዝብን ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መጎሳቆል ከመዳረጉም በላይ፣ በራሱ መልክዓ ምድር ሠርቶ፣ ነግዶ፣ አርሶና አርብቶ እንዳይኖር ለተለያዩ ችግሮችና መከራዎች አጋልጦታል፤ ብሏል በመግለጫው፡፡
 ፓርቲው በመግለጫው ለፌዴሬሽን ም/ቤት ባስተላለፈው መልዕክት፤የቁጫ ብሔረሰብ ማንነትና የራስ አስተዳደር የዞን መዋቅር ህገመንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች፣ በህገመንግስቱ በተቀመጠው አግባብ፣ መሰረት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጠው አበክሮ ጠይቋል፡፡
 በሌላ በኩል፤የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል ምስረታን ተከትሎ፣ በቁጫ የምርጫ ክልል በመንግሥት አመራሮች በተነሳው ረብሻና አመፅ፣ ለሰው ህይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ተጠያቂ የሆኑና የቁጫ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር እንዳይገናኙ በማድረግ ጥቃት ፈጽመውባቸዋል የተባሉ አካላት ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡ ቁሕዴፓ በመግለጫው ጠይቋል፡፡
ፓርቲው አክሎም፤ የመንግሥት አካላት በመሩት ሁከት፣ የሰው ሕይወት ለጠፋበት የሟች ቤተሰብና በብጥብጡ  የአካልና የንብረት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች፣ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ፣ ተገቢው ካሣ እንዲከፈልና የወንጀሉ ፈፃሚዎችም በቁጥጥር ሥር ውለው ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡

Read 627 times