Saturday, 29 July 2023 12:20

የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነትና የስበት ሥነ ልቦናዊ ሕግ፦ ተቃርኖ

Written by  በቴዎድሮስ ታደሰ
Rate this item
(3 votes)

ብዙውን  ጊዜ ራስን የማሳደጊያና ሰብዕናን የማበልጸጊያ  መሣሪያ  ተደርጎ የሚወደሰው የስበት ሥነ ልቦናዊ  ሕግ፤ (The psychological law of attraction) አዎንታዊ አስተሳሰቦችና  እምነቶች፣ የገንዘብ ስኬትንና የስራ እድሎችን ጨምሮ፣ በተለያዩ የህይወት ዘርፎች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይጠቅሳል። ይሁን እንጂ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነትን በተመለከተ ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮችን ከማብራራት አንጻር፣  ይህ አመለካከት ጠንከር ያለ የኢኮኖሚ ትንተና አስፈላጊነትን  የሚቃረን ይመስላል። በዚህ ጽሁፍ፣ የኑሮ ውድነትንና ሥራ አጥነትን ከመረዳት አንጻር፣በስበት  ሥነ-ልቦናዊ ሕግና በኢኮኖሚ ትንተና  መካከል ያሉትን  ልዩነቶች ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡  
በአስተሳሰብ (mindset) እና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች መካከል ያለው  ልዩነት፡-
 የስበት ሥነ ልቦናዊ ሕግ አቀንቃኞች፤ አዎንታዊ  አመለካከት መያዝ፣ የገንዘብ መትረፍረፍና  የሥራ ዕድሎችን  ሊስብ ወይም ሊያመጣ ይችላል ብለው ይሞግታሉ፡፡  ይህ አመለካከት ግን በኑሮ ውድነትና በሥራ ዕድል ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ይዘነጋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ፤ ውጫዊ  ኃይሎች የኑሮ ውድነትና የሥራ ገበያ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ለመረዳት ጥቅል አገራዊ ምርት (GDP)፣ የዋጋ ግሽበትና የሥራ ገበያ ሁኔታዎችን የመሳሰሉ ጠቋሚዎችን ማጥናትን ያካትታል፡፡ እነዚህን ውስብስብ ነገሮች ከግል እምነቶችና አመለካከቶች ጋር ብቻ የሚያገናኛቸው መሆኑ፣ የስበት ህግ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ፣ ያለውን ተግባራዊነትና ውጤታማነት  ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡   
የኢኮኖሚ  ተፅኖዎች እና ሥራ አጥነት-
  በቴክኖሎጂ እድገት፣ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ በሥራ ገበያ አዝማሚያዎችና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሳቢያ  ሥራ አጥነት በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የስበት ሥነ ልቦናዊ ሕግ፣ ግለሰቦች የሚፈልጉትን ሥራ በዓይነ ሕሊናቸው እንዲስሉና እንዲስቡ  ሊያበረታታቸው ቢችልም ቅሉ፣ በኢንዱስትሪ ለውጥ ወይም በኢኮኖሚ ውድቀት ሳቢያ የሚከሰተውን ሥራ አጥነት ሊቀርፍ ግን አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ፣ ሥራ አጥነትን በስፋት ለመፍታት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና የመፍትሄ እርምጃዎችን ለመቅረጽ  እነዚህን ማክሮ-ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎች ይመረምራል።
ማህበረ - ኢኮኖሚያዊ እንቅፋቶች፦
 የስበት  ሥነ ልቦናዊ ሕግ ብዙውን ጊዜ የግል እምነቶች ብቻ ለስኬት እንቅፋት የሚሆኑ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እንቅፋቶችን ሊያሸንፉ ይችላሉ የሚል አስተሳሰብ ያቀነቅናል፡፡ ይሁን እንጂ የተደላደለ አስተዳደግ የሌላቸው ግለሰቦች ጥራት ያለው ትምህርት፣ የጤናና የሥራ ዕድል እንዳያገኙ እንቅፋት ሊሆኑባቸው እንደሚችሉ የኢኮኖሚ ጥናት ያመለክታል፡፡ ማኅበረ- ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በኑሮ ውድነትና በሥራ አጥነት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ችላ ማለት፣ ለሁሉም እኩል እድል ለመፍጠር የታቀደውን ማኅበራዊ ፖሊሲ አስፈላጊነት ያዳክማል።
የኢኮኖሚ መረጃና ግላዊ ተመክሮ -
 የኢኮኖሚ ትንተና፣ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ በተጨባጭ መረጃና  አኃዛዊ ማስረጃ  ላይ ይመሰረታል። የስበት  ሥነ ልቦናዊ ሕግ በተቃራኒው፣ በግላዊ  ተመክሮዎችና በግል ገጠመኞች ላይ የተመሰረተ ነው። አዎንታዊ አስተሳሰብና አመለካከት ለግለሰቦች አቅም የሚያጎናጽፍ ሊሆን ቢችልም፣ ትልልቅ ማህበረሰባዊ ችግሮችን  ለመረዳትና ለመፍታት የሚያስችሉ ተጨባጭ ማስረጃዎችንና የተሟላ የኢኮኖሚ ጥናቶችን ፋይዳ ጨርሶ  ሊተካ አይችልም።
 የስበት ስነ-ልቦናዊ  ሕግ፤ አዎንታዊ አስተሳሰብንና በራስ ማማመንን የሚያበረታታ ቢሆንም፣ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ውስብስብነትን በተመለከተ ግን ሰፋ ያለ ማብራሪያ መስጠት  ይሳነዋል። ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ፤ በተጨባጭ መረጃና የገበያ አዝማሚያዎች ላይ ተመስርቶ እነዚህን ኢኮኖሚያዊ ክስተቶች የሚቀርጹ ኃይሎችን ለመረዳት ይበልጥ ተግባራዊ የሆነ አቀራረብ ይሰጣል፡፡  
ሰዎች  የአእምሮንም ሆነ የኢኮኖሚ ትንተናን ጠቀሜታ በመገንዘብ፣ አዎንታዊ አስተሳሰብን እንደ ግለሰብ የአቅም  ማጎልበቻ መሣሪያ አድርገው መጠቀም ይችላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰፋ ያሉ ማህበረሰባዊ ችግሮችን ለመፍታት በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ፖሊሲዎችና የኢኮኖሚ ስትራቴጂዎች አስፈላጊነትን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህን አመለካከቶች አንድ ላይ ማጣመር የኑሮ ውድነትና  የሥራ አጥነት ችግሮችን  የሚመለከቱ ውስብስብ  ጉዳዮችን ለመፍታት ይበልጥ ሁሉን አቀፍ  አቀራረብ  ይፈጥራል፡፡
Read 1500 times Last modified on Saturday, 29 July 2023 19:36