Saturday, 29 July 2023 12:13

“ያ ሣር አይደለም ወይ የምናየው ሁሉ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  ”ከ‘ሰፊው’ ተገልጋይ ይልቅ (‘ሰፊው’ ሕዝብ ከሚለው በውሰት የተወሰደ!) ወይ ራሳቸውን ብቻ፣ ወይ አ ለቆቻቸውን ብቻ፣ ወይ ዘመድ አዝማዶቻቸውን ብቻ፣ ወይ አማት ምራቶቻቸውን ብቻ አይነት አገልግሎት አሰጣጥ ስናይ ብዙም ምቾት አይሰጠንም፡፡--”
     

           እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይኸው ሐምሌም ሽው ብሎ ሊሄድ ነው...ሲያንሸወሽወን ከርሞ ማለት ነው፡፡ (‘ሲያንሸወሽወን’ የሚለው ቃል ከስምንቱ የንግግር ክፍሎች በየትኛው እንደሚደገፍ ገና አልታወቀም፡፡ አሁንም ‘ስምንት’ ናቸው አይደል! ብዙ ነገር “ለምን?” “እንዴት?” “በምን ምክንያት?” “በማን ወይም በእነማን ውሳኔ?” የመሳሰሉት አይነት ጣጣዎች ሳይገጥሟቸው “ሆነ፣” “ተደረገ፣” ሲባል መስማት ስለለመደብን ለድንገቱ ብለን መጠየቃችን ነው፡፡)
አንድ የሀገራችን እውቅ ጸሀፊ በአንድ መጽሐፋቸው ላይ ያሠፈሯትን ስንኝ እዩልኝማ...
ሐምሌ ወንዱ መጣ
ለጎኔ መኝታ ሳልፈለግለት
ሐምሌ ወንዱ መጣ ጉሙን ደረደረ
የወር ቀለብ የለኝ ቤቴ አልተከደነ
ኧረ ተወኝ ሐምሌ ጉምህን አትደርድር
ቀለቤን ልሸምት ቤቴንም ላስከድን፡፡
እኔ የምለው... እነኚህ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከሀገር ሀገር፣ ከሕዝብ ሕዝብ  ‘ዲስክሪሚኔት’ ያደርጋሉ እንዴ! አሀ...እኛ ላይ የሌለውን ጡንቻ ሁሉ ለማሳየት የሚሞክር መአት ነዋ! ነው ወይስ “እነሱ ፌስቡክና ቲክቶክ እስካሉላቸው ድረስ ከዛ በላይ ምንም ነገር አይፈልጉም!” ብሎ ሹክ ያለብን አለ እንዴ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አንቺ እንትና፣ ስንትና ስንት ጊዜ ጠፍተሽ ከርመሽ...አለ አይደል... ወይ አምረሽ ደምቀሽ በራስሽ ሠርግ ላይ፣ ወይ ደግሞ የሆነ ተአምራዊ የሚባል አይነት አድናቆት ሊገልጸው በማይችል ፍጥነት ዛሬ እግረኛ ሆነሽ ሀይገር ላይ እኩል ስንጋፋ እንዳልነበርነው ሁሉ፣ ከነገ ወዲያ ወይ በቪ ኤይትሽ እሱም ባይሆን በሆነች ‘ራቭ ፎር’ ምናምን ውሀ እየረጨሽን ታልፊያለሽ ስንል ጭራሽ ቲክቶክ ላይ ተከሰትሽና አረፍሽው!
እሱማ ቲክቶክ ላይ መሆኑ ችግር አለው ለማለት ሳይሆን ምን አስበሽ ነው ለማለት ያህል ነው፡፡ አሀ... እዛ ሚዲያ ላይ እኮ ባዮሎጂ... አለ አይደል... ‘የሰው ልጅ አፈጣጠር’ ምናምን አይነት ‘ሲኒማዎች’ ላይ ኦፊሴላዊ ብቻ ሳይሆን ኦፊሴላዊ ያልሆኑ ነገሮች ብልጭ እያሉብን ተቸገርና!  አይ ምነው፣ ምን አስበሽ ነው፣ ለማለት ያህል ነው።
ስሙኝማ...ፊልም የምትሠሩ ሰዎች እስቲ እናንተ እንኳን ፊልሞቻችሁ ውስጥ... አለ አይደል...የፊልም ጽሁፎቻችሁ ውስጥ “ደንበኛ ንጉሥ ነው፣” የሚል ሲን ነው ምናምን የምትሉትን ጨምሩልንማ! ፈረንጅ ‘ዘ ከስተመር ኢዝ ዘ ኪንግ’ ሲል እኮ ቲራቲር ማሳመሪያ ብሎ  አይደለም፣ በአብዛኛው ከአንጀቱ ነው፡፡ የእኛ ነገር መፈክር ብቻ! ልክ ነዋ...እኛ ዘንድ እኮ አይደለም እንደ ኪንግ ልንቆጠር ቀርቶ በዓይናቸው ሙሉ ሊያዩን እንኳን  የማይፈልጉ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነበት ዘመን ውስጥ ነው ያለነው፡፡
”አንተ ወዳጄ... ወርሀዊ የቤት በጀትህን አናግተህ የአንድ ሺህ ብር ጫማ ለመግዛት፣ እርካሹ የጫማ ዋጋ ሀያ ሺህ ብር ምናምን የሆነበት ቡቲክ ምናምን ዘው ብለህ ስትገባ አበባ ይዘው ሊቀበሉህ ነበር!” የልብ ወዳጅ በጠፋበት በዚህ ዘመን ወዳጅነታችንን በብልሀት መያዝ ስለሚያስፈልግ ልክ ነህ እንበል፡፡ ግን እኮ ወዳጄ፣  የሀያ ሺህ ብር ጫማ መግዛት የምትችል ከሆነ ለንጉሥነትህ የሌሎች መፈክር፣ መወድስ ቅኔ ምናምን አያስፈለግህም፡፡ አሀ...በእውቅ የተሠራ  ዘውድህን አንተው በራስህ ላይ መጫን ትችላለህ! ደግሞልህ እኛ እግርህ ላይ ያለውን የትዌንቲ ታውዘንድ ጫማዎች እያየን “ታያለህ እኛ ‘ማዳበሪያ’ የምንለው ጆንያ ውስጥ ያለው ጤፍ እንዲበረከት አንዲቷን እንጀራ ‘ለሁለት ሚል’ እያደረገን እሱ ሁለት ኩንታል ማኛ ጤፍ እግሩ ላይ አድርጎ ክንፍ ግጠሙልኝ ሊል ምንም አልቀረው እኮ! (እግረ መንገድ ጠቆም ለማድረግ ያህል... በኦቨርናይት ሚሊየነርነት ምናምን፣ በቦተሊከኝነት፣ በሚለየነሮችና በቦተሊከኞች የቅርብ ሰውነት ክንፍ ካልገጠማችሁልኝ የምንል በርከት እያልን የሄድን ነው የሚመስለው፡፡)
እናልህ ወዳጄ፣ የሃያ ሺህዋን ግጥም ካደረግህ እንደዚህ እያልን እንንሾካሾክብሀለን ለማለት ነው፡፡ “ድሮስ እናንተ ከመንሾካሾከ ሌላ ምን ታውቁና!” ካልከን የሚቀጥለው ጊዜ ወይ ከትዌንቲ ታውዘንዷ ሰፈር ወደ ፎርቲ ታውዘንዷ ፈጣኑን ሚሳይል ቀድመሃት ትወነጨፍና ከእኛ ዓይንም ትትርፋለህ፣  ወይ ደግሞ ከትዌንቲ ታውዘንዷ ወደ እኛ ሰፈር ዋን ታውዘንዷ እዘጭ እንቦጭ ትልና በየባሱ እንጋፋታለን!
ስለ ደንበኛ ነበር ማውራት የጀመርነው አይደል!... እናላችሁ አሪፍ መስተንግዶ የሚሰጡትን ያህል አገልግሎት ፈልጋችሁ ሳይሆን፣ እነሱን ጎትታችሁ የሄዳችሁ ይመስል ፊት የሚነሷችሁ መአት አሉላችሁ! ስሙኛማ...እግረ መንገዴን...አንዳንድ ሰው በብዛት የሚገለገልባቸው ተቋማት ውስጥ ያላችሁ ወጣት የተቋማቱ አባላት ተረጋጉማ! አልፎ፣ አለፎ የምናያቸውና የምንሰማቸው ነገሮች ደስ አይደሉም ብቻ ሳይሆን ልናስባቸው የማንፈልጋቸውን ሀሳቦች እያመጡብን እንቸገራለና! እናማ ወጣቶቹ እዛ ስፍራ በሙያችሁ ልታገለግሉ ስትቀጠሩ፣ የግል ጓዝ ጉዝጓዛችሁን እዛው ከቢሮ ውጭ ትታችሁ ኑማ! የሥራ ሰዓቱ ሲያበቃ ትደርሱበት የለ! ማን ይወስድባችኋልና ነው! እንደዚህ ለማለት የምንገደደው ነገሮቹ ጥሩ ሆነው ሳይሆን በራሳችሁ ሰዓት የምታደርጓቸው ነገሮች የራሳችሁ ጉዳዮች ብቻ ስለሆኑ ጦስም ቢያመጡ ጦሱን ተሸካሚ እናንተው ናችሁ!
እናማ... እየገጠመን ያለው ችግር ምን መሰላችሁ... አሁን አሁን ምንም አይነት ነገር አዲስ፣ የሚያስገርምና ጉድ የሚያሰኝ መሆን ባቆመባት ሀገር፣ የግለሰቦችና የቡድኖች የሚመስሉ ነገሮች ሙያና ሙያ ብቻ ሊሆኑ በሚገባቸው ነገሮች ውስጥ ዘው እያሉ እየገቡ፣ የዜጎችን ስሜት መጉዳታቸው ስለማይቀር ነው፡፡ እናማ ምናልባት ከትምህርት ቤቶችም፣ ምናልባት ከሆኑ ቦታዎችም ወደተለያዩ ሙያዎች በህዝብ አገልጋይነት የሚገቡ በተለይም ፈረንጅ “ግሪን ቢሀይንድ ዘ ኢርስ” እንደሚለው አይነት ብዙም የሥራ ዓለም ተሞክሮ ለሌላቸው ወጣቶች፣ በተለይ በሚሰማሩባቸው ሙያዎችና በዛም ተገቢ አገልግሎት መስጠት ላይ ብቻ የሚያተኩሩ መመሪያዎች፣ ስልጠናዎች ምናምን ቢያገኙ አሪፍ አይመስላችሁም! ታዲያ አደራ...ስልጠና በሚጀመርበት ጊዜ “የዛሬውን ስልጠና ልዩ የሚያደርገው...” ምናምን አይነት ዲስኩሮች በህግ ባይሆንም፣ በውስጥ ‘ሰርኩላርም’ ቢሆን ይታገዱልንማ!
ከ‘ሰፊው’ ተገልጋይ ይልቅ (‘ሰፊው’ ሕዝብ ከሚለው በውሰት የተወሰደ!) ወይ ራሳቸውን ብቻ፣ ወይ አለቆቻቸውን ብቻ፣ ወይ ዘመድ አዝማዶቻቸውን ብቻ፣ ወይ አማት ምራቶቻቸውን ብቻ አይነት አገልግሎት አሰጣጥ ስናይ ብዙም ምቾት አይሰጠንም፡፡
የሆነ የአለቃ ወይም ቢለቦርድ በሚያክል የሆነ ማቴሪያል ስሙ በግልጽ፣ የሥራ ኃላፊነቱ  ደግሞ በመአት ምህጻረ ቃል ተዥጎርጉሮ ጠረዼዛው ላይ የለ ሰው ቢሮ አንገታችሁን በበሩ ሾከክ ታደርጋላችሁ፡፡ ያው ምንም ቃላት ሳያወጣ  ግንባሩን አርባ ስምንት ተኩል ቦታ ከስክሶ “ምነ ፈህ ነው?” አይነት ነገር ያሳያችኋል፡፡
“ጠዋት አሥራ ሁለት ሰዓት መጥተን ነው እኮ ተራ የያዝነው፡፡”
“እና...!”
“አይ እዚሁ እንደተገተርን የምሳ ሰዓት ደረሰ እኮ!”
“ለምን የእራት ሰዓት አይደርስም...እኛ ምን እናድርጋችሁ!”
“እ...እ..እኛ እዚህ ቆመን ከኋላችን ብዙ አርፍደው የመጡ ሰዎች እየተስተናደጉ ነው፡፡ ጌታዬ መብታችን እኮ ነው የተገፈፈው!”
(ልቡ ጦሽ ልትል አፋፉ ላይ እስከምትደርስ ይንከተከታል፡፡) “እውነት! መብታችሁ ተገፈፈ? እሱን ከፈለጋችሁ የበላይ አለቃ ለምትሉት አመልክቱ!”
እናላችሁ... በአገልግሎት አሰጣጥና በመሳሰሉት የምንሰማቸው (አልፎ፣ አልፎም እራሳችን የምናያቸው) ነገሮች ደስ አይሉም፤ ምቾትም አይሰጡም፡፡ አሉታዊ እየሆኑብነ ተቸግረናል፡፡
የሀገራችን ሰው የሚጠቀምባት የጥንት ስንኝ አለች፡፡
አሰምራቸውን ከብቶቻችን ይብሉ፣
አሰምራቸውን በጎቻችን ይብሉ፣
አሰምራቸውን ፍየሎቹ ይብሉ፣
ያ ሣር አይደለም ወይ የምናየው ሁሉ፡፡
እና ያለማጋነን፣ ያለ ቅጥያና የነገር ‘አፔንዲክስ’ (ቂ...ቂ...ቂ...) ዘንድሮ በበርካታ መስኮች የምንሰማቸውና የምናያቸው ነገሮች ሁሉ...አለ አይደል...“ያ ሣር አይደለም ወይ የምናየው ሁሉ! የሚያሰኙ ናቸው፡፡
አንድዬ በተስፋ የምንጠብቀውንና ብዙዎች እየጸለዩለት ያለውን  በጎውን ዘማን ያፍጥንልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1088 times