Saturday, 03 June 2023 20:20

የራሱን መጻሐፍ እንዲያነብ የታዘዘው ዝነኛ ደራሲ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጨረፍታ

 ማርዮ ፑዞ በጠባብ መኖሪያ ክፍሉ ውስጥ ተመስጦ በታይፕ ራይተር እየጻፈ ነው። ነገር ግን ብዙም ሳይርቁ እየተጫወቱ የነበሩት የአምስት ልጆቹ ድምፅ ከተመስጦው እያወጣው ሲቸገር. ..ወደ ልጆቹ ዞሮ እስኪ አንድ ጊዜ ዝም በሉ  አላቸው።
”በአለም ዝነኛ የሆነ፡ በብዙ ሺህ ኮፒ ሊሸጥ የሚችል የሚገርም መፅሀፍ እየጻፍኩ ነው። ድምጻችሁን  ቀንሱ ወይም ራቅ ብላችሁ ተጫወቱ”
ማርዮ ፑዞ ልጆቹን እንዲህ ብሎ ሲናገራቸው፤. . .. በተለይ ወንድ ልጁ ቶኒ በአባቱ ንግግር ተገረመ ። ምክንያቱም አባቱ ይህን በሚናገርበት ወቅት. ..  ዝነኛ መፅሐፍ ፅፈው በብዙ ሺህ ኮፒ ከሚሸጥላቸው ታዋቂ  ደራሲያን ተርታ የሚመደብ ሰው አልነበረም።ማርዮ ፑዞም ይህን እውነት ያውቃል። የመጀመሪያ ስራው ከሆነው The Dark Arena ጀምሮ እስካሁን የጻፋቸው መፅሐፍት. . ስምም ሆነ ብዙ ብር እንዳላስገኙለት፣ ሌላው ቢቀር የተሻለ ኑሮ እንኳን እንዲኖር እንዳላስቻሉት ያውቃል። ይህ ያለፈ ታሪኩ ነው። አሁን ግን ይህን ነገር ለመለወጥ ቆርጦ ተነስቶአል ። ለዛም ነው ለልጆቹ  ”በአለም የታወቀ ዝነኛ መፅሐፍ እየጻፍኩ ስለሆነ አትረብሹኝ” ያላቸው ።
ማርዮ ፑዞ ይህን ካለ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ያንን ታሪኬን ይለውጠዋል ብሎ ወስኖ የጻፈውን መፅሐፍ አሳተመ።ይህ መፅሀፍ እንደታተመም ፡ የጋዜጦች የፊት ገፅ በሱ ፎቶዎች ተጥለቀለቁ። አለም ቆሞ አጨበጨበለት ። ይህ ብቻ አይደለም፡
ባልተስተካከለ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ፣ ነገን አሻግሮ በማየት የጻፈው መፅሐፍ፣ በአለም ዙሪያ ከ21 ሚሊዮን በላይ ኮፒዎች ተሸጠ። በአለማችን ካሉት የምንጊዜም ምርጥ ልቦለድ ስራዎች መሀከልም The Godfather ዋንኛው ሆኖ ተመዘገበ።
ስሙ ከዝነኛ ደራሲያን ተርታ እጅግ ርቆ ባለበት ወቅት ማርዮ ያስብ የነበረው የነገውን ስኬታማነቱን ነበር። ያ ራእይ ወዳላሰበው ከፍታ ገፋው ።
The Godfather መፅሐፍ  አማርኛን ጨምሮ ፡ በብዙ የአለም ሀገራት ቋንቋዎች ተተረጎመ። የማርዮ ፑዞ ይህ ዝነኛ ስራው ወደ ፊልም ተለውጦም ፡ ከምንጊዜም ምርጥ ፊልሞች መሀከል አንዱ ከመሆኑም ሌላ፣ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝቷል። ለመደምደሚያ ያህል. .. ማርዮ ፑዞ ይህ መፅሐፉ  ወደፊልም ሲለወጥ ፡  ስክሪፕት የመጻፍ ብዙም ልምድ ስለሌለው ፡ ከሌሎች ሁለት የስክሪፕት ፀሃፊዎች ጋር በመሆን ነበር የጻፈው። ፊልሙ ዝነኛ ሆነ። እና ግን ማርዮ ፑዞ የፊልም ስክሪፕት ራሱን ችሎ ለመጻፍ ሲል፡ የፊልም ፅሑፍ አጻጻፍን ለመማር የሚያግዘው አንድ መፅሐፍ ገዛ ። እና መፅሐፉን ማንበብ ሲጀምር. ..በመጀመሪያ ገፁ ላይ፤ ”የፊልም ስክሪፕት አጻጻፍ መማር የሚፈልግ ሰው በቅድሚያ The Godfather ን ደጋግሞ  ማንበብ አለበት” የሚል ፅሁፍ ነበር ያገኘው።
(ዋስይሁን ተስፋዬ)




Read 1023 times