Saturday, 03 June 2023 20:07

”አንቺን ባላገባ ሱሪ አላጠለኩም”1

Written by  ዮናስ ታምሩ
Rate this item
(6 votes)

‹1› የበቅሎ ኮቴ፣ ይላል ትኩም፣ ትኩም፣
        አንቺን ባላገባ፣ ሱሪ አላጠለኩም።
    - ካፒቴን አፈወርቅ ዮሐንስ በ15 ዓመታቸው ላፈቀሯት ኮረዳ የገጠሙት ነው። የመጀመሪያ ግጥማቸው እንደሆነ ይነገራል።
          

        የእድር ክፍያ እንድከፍል ማለዳ ተቀሰቀስኩ። ተነጫነጭኩ። ገና አልነጋም፤ ድንግዝግዝ ያለና ጭፍና የጨፈነ። ልክ እንደ መጋኛ ጅስም የሚሰቅዝ ብርድ ምድርን አወራክቧታል፤ ነፍራቃ ሰንበት….
§
…የእንኮይዘንግ ደኅና መሰንበቷን እንጃ… ጠል የጠቀሙ ከንፈሮቿን እያማመሰች ደጃፍ ትቆረቁራለች፡፡
‹‹ማነው?››
ገመምተኛ ድምጽ ከውስጥ ወጣ፡፡
‹‹ገነት ነኝ›› አያቷ ያወጡላት ሥም ነው
‹‹ጋኔን ይነቅሽ››
በውስጡ አግተመተመ፡፡
ጣቶቿን እየፈተለች ትጠባበቅ ያዘች። ቁሩ ነው መሰል ትናጣለች። የዳንግ ኳስ ዓይኖቿን በእርጋታ ታንቦላፋለች። ክርትት፣ ክርትት። መንፈስዋ ወብርቷል። ብርድና ሃፍረት ዕኩሌታ ተጠናውቷታል፡፡        
§
በሩ የሲቃ ድምጽ አስተጋብቶ ተከፈተ። ተከተተች። እውስጥ ያደባው ቀረሮ በሲቃ ስልት ሠላምታ አቀረበላት። በሩን ገርበብ አድርጎ ከተወው በኋላ ትዋጋውን አለዘበው፤ እዚህ ቤት አንዳችም ጤነኛ የለም ማለት ነው…
…እንደ ምላጭ በተቆነጸለች ፍራሽ ላይ ጎኑን ታክካ ተቀመጠች። ጎኑን በእሾህ ስልት ለግሷት ወደ ዕንቅልፍ ዓለሙ ተመመ። ዓይኖቿ ይማጠናሉ፤ አንዲያ ነፍሷ ብርክ ሆናለች። ሁለመናዋ እንደ ባቄላ እንጀራ ድቅቅ ብሏል። ቀረሮ ለምን እንደሚጠየፋት ባይገባኝም ሆደ ቡቡ እንደሆነች አውቃለሁ። ብሩስሊ ሲሞት ጸጉሯን ተላጭታ፣ ማቅ አገልድማ ለቅሶ መቀመጥዋን አውቃለሁ፤ ቀረሮ ግን ሁሉ ነገሩ የብሳና ነው፤ ሥሩ በተዐብዮ ምስጥ ተበልቶ መጽኛ ያጣ ተንከላዋሽ…
…እዚያ መንገድ ተሻግሮ ካለው እንጨት ቤት ቁሩንጮና ቁርጥራጭ ጣውላ ሲፈገፍግ ይውላል፤ ሁል ጊዜ ሳገኘው ታዲያ ቡናኝ ብቻ ነው ልብሱ። የአካባቢውን ሰው አስም ካላስያዝኩ እያለ እንጂ ልብሱን ቀይሮ መምጣት ይችል ነበር፤ ቀረሮ ግን ከይሲ ነው። ተንኮል መቀመም ሲወድ፤ ግብታዊ ነው። በግብታዊነት ስለሚያውቅ ደንደሳም ጥላቻ ልቤ ገባ። እንዲያ እንዳሰለቸኝ ቢያውቅ። ገለባ ትከሻው ላይሸከም ዕውቀት ያከናነበውን እግዝሔርንም ጠላሁት፤ ለሁለቱ ያለኝ መታከት እንደ ሊከርት እርከን ከቀን ወደ ቀን ከፍ እያለ ይሄዳል፤ ከመጥላት ወደ በጣም መጥላት፤ ወላ በጣም ከመጥላት ወደ እጅግ በጣም መጥላት።
እግዚሔር ደግሞ የምንጠላቸውን ሰዎች በጉያችን ሲያንዣብቡ እንዲከርሙ ይፈርድብናልና (ለዚህም ጠልቼአለሁ) ሞጣጣ ፊቱን ወደ እኔ አስግጎ ይስቅልኛል፤ ሁልጊዜ ነበር ታዲያ። እንደደበተኝ። ሰዎች በምድር ላይ ሲኖሩ እንደተጠሉ የማይገባቸው ነገር ያበሽቀኛል፤ ቀረሮ የዓለማችንን የእንጨት ሥራ ዕውቀቶች መጦ የሚያስቀር ነቃቃ አንጎል ያለው ይመስለኛል። አንጎሉ ገብጋባ ወይ ሆዳም...
…የተገለጠ መጻሕፍ የሚመስል (ወይም እየተነበበ ያለ መጻሕፍ መሳይ) መደገፊያ ያለው ሶፋ ሠርቶ ሲያስረክብ አይቼአለሁ፤ ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ሶፋ አይቼ አላውቅም ነበር። በጣም ደነቀኝ። ከሶፋው ግራ መደገፊያ በኩል ላይ ደግሞ ‹‹ወሪሳ››፣ ከዚህ ርዕስ ሥር ‹‹ዓለማየሁ ገላጋይ›› የሚል መጻሕፍ መሳይ ነገር፤ በቀኝ በኩል ‹‹ግራጫ ቃጭሎች››፣ አሁንም ከዚህኛው ሥር ‹‹አዳም ረታ›› ተብሎ በጥልፍ ተውቧል። ግራ ተጋባሁ፤ እንዲያ ያሉ ሥሞችን ሰምቼ አላውቅም ነበር። ወይ ቀረሮ ላንቲከኛ ነበርን?  
የራሱ ጉዳይ ነው ግን፤ እንኮይዬ ግን እንደ ጣኦስ ታስደነግጻለች፤ ሁለመናዋ ውብ ነው። ስለ ዚያድ ባሬ ወረራ ሲነሳ ሀገር ምድሩ አንቀላፍቶ ሲያበቃ አባቷ ብቻቸውን ዘምተው ሶማሌን ያቸነፉ ይመስል ኩራት ይሰማቸዋል። በኋላ ‹ሶማሌ› የሚል ሥም ሰጥተዋት አረፉ፡፡                
§
አንድ አረፋድ እዚያች ጠፍ መሬት ላይ ከማቲዎች ጋር የነበረኝን ጨዋታ ገትቼ እየተከታለፍኩ ቤት ደረስኩ…
…እናቴ የአጃ ሊጥ የመሰለ ጠጉሯን ሦስት ቦታ እያሸመች ነበር። እንደ ከል የጠቆረ አዳፋ ሻሽዋን ባቶቿ ላይ አንጥፋለች። ቅርናቱ የሚያጥወለውል ቅቤ ከኮባ ላይ ወዝፋ በጣቷ እየጠነቆለች አናቷ ላይ ትመርጋለች፡፡
አክክክ… እንትፍፍፍፍ… ማለት ቃትቶኝ ተውኩት። ‹ብስባሽ› የመልስ ምቷ ነው
ዳናዬን ስትሰማ ቀና እንደማለት ሆነች…
‹‹ዝላይ በቅቶህ ነው?››
‹‹አዪ…›› ራሴን አናጠብኩ
‹‹እና ምን እፊቴ ይጋርጥሃል?››
ቅቤውን በአናቷ ልክ ትለስናለች፤ የዚህ ወር ቀለባችን ቅቤ የሌለው እንደሚሆን ገመትኩ፡፡  
‹‹እቴሜቴ…››
‹‹ምነው ቀልማዳዬ!›› በስስት ዓይኖቿን እያንከላወሰች
ጥቂት አሰብ አድርጌ...
‹‹እንኮይዬና ያ-ጅብራ ለምንድነው የሚጣሉት?››
ጅብራ አባባሌ አስደነቃት መሰል ፋታ ወሰደች። ከመደነቋ ዕኩል፣ ባይሆንላትም ጸጉሯን ማሽሞንሞኗንና ቅቤ መደንባቷን አላስተጓጎለችም ነበር
አንገቷን ወደ እኔ አስግጋ…
‹‹ሕጣናት አይደለህ፣ ምን ዶለህ?›› ብላ አዳፈነች
ትከሻዬን ስሰብቅ ስላየች…
‹‹እነሱ የሚጣሉት መርከስ ስለተጎነጩ ነው!››
‹‹እህህህህ…?››
‹‹ኋላስ ቀልማዳዬ! እርኩሶች ናቸው፤ ስዶችም ጭምር… የእነሱ እህል ውኃ ተራክሷል። እንግዲህ ልብ በል፣ እህል ውኃ እንደ አያያዛችን ነው የሚዘልቅ፤ እንኮይ ራሷ ረክሳ ፍቅርን አርክሳለች፤ ራሷ ተካልባ ፍቅርን አካልባለች›› ንግግሯ አልገባኝም፤ ግን ልብ ብዬ እያየኋት አደምጣለሁ፤ መለስ ብላ አይታኝ ቀጠለች ‹‹እህል ውኃ ዘለ-ዓለማዊ የሚሆነው እንደ አሰፋፈራችን ነው። ለዘለ-ዓለም ብለን የሰፈርን እንደሆን ዘለ-ዓለማዊነቱ ዕሙን ነው፤ ኋላ በስድነት፣ በውርክባና በግብታዊነት የሰፈርነው ከሆነ ይረክሳል፣ ይጠነዛል…››
ይኼን ብላኝ ገረመመቺኝ፣ ‹‹እኒያ ጉምቱ ፈላስፋ ማናቸው በለኝ? የአውሮፓ ሰው ናቸው›› ጠቋሚ ጣቷን አገጭዋ ላይ አኑራ ጥቂት ተብሰለሰለች…
…መለስ ብላ፡-
‹‹ታዲያ እኒህ ሰው ምን ይላሉ መሰለህ?...›› ደግማ ፈተሸቺኝ ‹‹እህል ውኃ የሚጠናው ፍቅረኛማቾች መሀል ጽናት ሲኖር ነው ብለዋል፤ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?››
ራሴን እያማታሁ…
‹‹እቴሜቴ ፍቺውን ታውቂያለሽ?›› ጠየኩ
‹‹እንግዲያስ… የእንግሊዝ አፍ ያደግንበት ነው! እንግሊዝኛ አቀላጥፌ አወራ ነበር››
‹‹እንዴት?››
‹‹የዛሬውን አይበለውና ቋንቋውን ከግቱ ነበር የጠባሁት!››
የስላቅ ሳቀቺብኝ፡፡
እናቴ እየተጫወተቺብኝ እንደሆነ ለማጣራት ትክ ብዬ ፈተሽኳት። ከሁኔታዋ ፍጹም አልረገበችም፤ ልቃወማት አልደፈርኩም፤ ያጋተችኝን መጋት አለብኝ፤ ዝም፣ ጽልም…      
‹‹እውነት እልሃለው… እንኮይ የታሪክ አተላ ነች። እውነት ላይ የተመሠረተ ማፍቀርንና መውደድን አታውቅም። የዋህና ግልብ። አንድ ነገር ልትፈጥም ስትነሳሳ ከራሷ አትመክርም። ሀሳቧ እንደ ጥሬ የተበታተነ ነው። አበክሮዋ የተመጣጠነ አይደለም። ነገር ግን ሁሉም ነገር መጠንና ቦታ አለው፤ ያለ ቦታው የዶሉት ነገር ከንቱ ድካምን ያስከትላል። ጉሮሮ የሚውጠውን እጅ ይመጥናል። ቀድሞ ሲፈጥራት ጠዋት የጠነሰሰቺውን ከሰዓት የምታደባይ ዓይነት ሴት አድርጎ ነው። ፍጥንጥን ማለት ግብሯ ነው። ቸኳላ! የሴት ቸኳላ ደግሞ ውላ አድራ ራሷ ላይ መዘዝ መምዘዟ አይቀርም። ይኼዋ ‹ሰከን በይ… መሬት ያዥ› ብትባል አልሰማ ስላለች ቅጣቷን ተከናነበች፤ መከርናት ዘከርናት እሷ እቴ ከቁብም አትጥፈው! ብስባሽ…››
ሁሉ ነገር ተሳከረብኝ…
…እውነት፣ እውቀት፣ ቦታ፣ አበክሮ፣ ምትና ምጣኔ ምንድናቸው? የእኛ እውነት በአንጃ-ግራንጃ፣ በአፈ-ታሪክ፣ በተረት፣ በተውላጠ-ሥም በምሳሌ፣ በፈሊጥና በጅኒ-ቁልቋል የተከበበ አይደለምን? በተረት-ተረት የሚተዳደር ሕዝብ ፍጻሜው ተረት አይሆንም?
ሕጋችን፣ ደንባችንና ይትባሕላችን ባለ ቅቤ አንደበት ባበጃጀው ምሳሌና ታሪክ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ተገቢ ነውን? የእውቀታችን ምንጭ ልምድ፣ አዋዋል፣ አኗኗር ቅብርጥስ… አይደሉምን? ከልምዳችን፣ ከአዋዋላችንና ከአኗኗራችን አንጻር የሚጠራቀም እውቀት በሌላ፣ ወይም በአዲስ ልምድ፣ አዋዋልና አኗኗር ሲተካ አይምታታም? አይዛነቅም?
§
ቆይ ያ ቡናኛም ቀረሮ ምን አጣሁ ነው የሚለው? የእንኮይዘንግ ነገር ፋታ ስለነሳኝ ጓደኞቼን አስተባብሬ በሽምቅ ድንጋይ ወረወርንበት፤ ተደብቀን። ምዝምዝ ሰገቱራ የተጎነጎነበት ጭንቅላቱ ቢበረቀስ መዘዝ እንደሆነ ባውቅም ያቅሜን እያነሳሁ እሰነዝራለሁ፤ ስንዘራ አሰለጥናለሁ፡፡
‹‹ቀረሮ፣ ጅብራ›› እያልን
ቆሞ ይፈትሻል ማን እንደሆንን፤ ድምጼን ስለለየ ለእናቴ አቃጠረ፤
ጋደድ ብላ አይታኝ ስታበቃ ቂጤን በሳማ ሳመቺኝ፤ እልህ ይዞኝ አላለቀስኩም ነበር፤ ቀረሮን የተበቀልኩ የጎዳሁ እየመሰለኝ በሚጎበኘኝ አረንጓዴ እሣት ብለበለብም አንዲት ጥሪኝ እንባ ላለማውረድ ለራሴ ቃል ገባሁ፤ ጥርሴን ነክሼ በውስጤ ‹ይኼ ጅብራ› እያልኩ…
…አንድ ቀን እናቴ ሽልንግ ዘይራኝ ፓስቲ ገዝቼ በልጆች አዩኝ/አላዩኝ እየተገላመጥኩ በሠፈራችን ጉራንጉር ውስጥ ሸርተት ብዬ ሳልፍ፣ ‹እንኮይዬ›ን በቁሟ ተክዛ - እየሄደች ናውዛ አገኘኋት፤ እጠባብ ምንገድ ላይ አስቁማኝ ቁንጮዬ ላይ ያረፈውን ቡናኝ እያራገፈች ሠላምታ ሰጠቺኝ፤ ድምጽዋ ተኮናኩኗል፤
ቀና ብዬ ሳያት ዓይኖቿ እንባ አርግዘዋል፤ ሽንጣም የእንባ ዘለላ ጉልበት ባጣ ስልት በጉንጮቿ ተንከላውሶ ወርዶ ከከንፈሮችዋ ሰጠመ። ቁመቴ ቢያኽላትና ባብስላት በወደድኩ…
…ድክም ብዬ አየኋት
‹‹ምን ሆነሻል?››     
የሆነቺውን አውቃለሁ፡፡
‹‹ምንም››
ብላኝ ተሰናበተች
‹‹እንኮይዬ…››
ዘወር አለች
‹‹አታልቅሺ፣ ሳድግ አገባሻለሁ!››
ሕያው፣ አካል የተላበሰ፣ የሚዳብስ፣ ብርሃን አሳባቂ፣ ሚንት ጠረን የታደለ፣ ጽጌ ዓይነት፣ ነፍስ ያለው ፈገግታ ለግሳኝ እመንገድዋ ገባች፤ አልባብ ጠረንዋን እየተፋች ብዙ በዓይኖቼ እየተከተልኩዋት….     


Read 803 times