Saturday, 03 June 2023 13:49

ኅሩይና ሥራዎቻቸው…ለትውልድ

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

   [አሁን የአዳም ልጆችን ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ፣ በአገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ፣ ከኢትዮጵያ ከፍ ካሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው፡፡ ብልሃቱንና ትጋቱንም ለመልካም ስራ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ስላደረጋቸው በመንግስታችን ስራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ በቃ፡፡ በየጊዜውም የጻፋቸው ከፍተኛ ባህርዩን የሚገልጡ መጻሕፍት፣ ይልቁንም በቤተ-ክህነትና  በታሪክ ዕውቀት በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት፡፡ ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈልግ አልመሰለኝም፡፡ በአጭሩ ከጠባዩ ትልቅነት የሚሰማኝን ለመናገር ሳስብ፣ ጊዜውን ሁሉ ቁም ነገር በመስራት ማሳለፉ፣ ከራሱ ይልቅ የተቸገሩትን  ለመርዳት መጣሩ፣ ዕውነትን፣ ፍርድንም ማክበሩና በአገር ፍቅር መቃጠሉ ትዝ ይሉኛል፡፡ አገልጋዬና ወዳጄ ኅሩይ! በተቻለህ ስለ አገርህ ስራህን በሚገባ ፈጽመህ በምትሰናበትበት ጊዜ ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር፣ ስራዎችህ የሚገፋ የአለምን ጸጥታ የሚያናውጥ ነፋስ ምንም ቢያንገላታህና በታላቅ ፈተና ላይ ቢጥልህም ሊያሸንፍህ አልቻለም፡፡ ታላቅና ቸር በሆነው ጌታ ለተመደበው ሕግ ግን መታዘዝ ግድ ሆነብህ፡፡ ይህም ለእያንዳንዳችን በተራ የሚደርሰን ዕድል ነው፡፡ አንተም እስከ መጨረሻ ከታገልክ በኋላ ዛሬ ደከመህ፤ አንቀላፋህም፡፡ በስጋ ብትለየንም ስምህና ስራህ በመካከላችን ይኖራሉ፡፡ ኅሩይ! እግዚአብሔር ሲያስበን አጥንቶችህ መንፈስህ  በእንግድነት በመጣህበት በዚህ ስፍራ በሰላም ዕረፍ፡፡] (ቀዳሚዊ ኃይለ ስላሴ-ለንደን መስከረም 7 ቀን)
ይህ የንጉሰ ነገስቱ መሪር ኃዘን፣ ታላቁ ደራሲ ክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሞትን ተከትሎ፣ በስርዓተ-ቀብራቸው ላይ ባሰሙት የመጨረሻ መሰናበቻ ንግግር ነው፡፡ ቀብሩም የተካሄደው በመስከረም ወር በአስራ ዘጠኝ ሃያ ዘጠኝ ዓ.ም በእንግሊዝ አገር ለንደን ከተማ አጠገብ ባዝ በተባለ ስፍራ  ነበር፡፡ በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ በወረደው መከራ ምክንያት ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ተሰደው፣ የአገራቸው ጥፋት ያሳደረባቸው ጽኑ ምሬትና የሱም ጠንቅ ያስከተለው ህመም አንድ ላይ ተደምሮ ለህይወታቸው ማለፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ በርግጥ ወቅቱ አገራችን ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ፋሽስቶች ተወርራ ነጻነቷን በመገፈፍዋ ንጉሱና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኅሩይ፣ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሁሉ በእንግሊዝና በሌሎች አገሮች ተሰደው በኃዘንና በመከራ፣ በችግር በስጋና በመንፈስ ስቃይ ውስጥ በነበሩት ጊዜ ስለነበር የኅሩይ ህልፈት ሀዘናቸውን እጥፍ ድርብ አድርጎባቸው ነበር፡፡ ከፍ ሲል በንጉሱ የተነገረው ምስክርነትን ያዘለ ቃል ኅሩይ በህይወት በነበሩበት ጊዜ የጻፉትና ከሰባ ዓመታት በኋላ ዳግም ለመታተም የበቃው “የኢትዮጵያ ታሪክ” መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ሰፍሯል፡፡ በእርግጥ የመጽሐፉ አዘጋጆች በአጽንኦት ቃሉን ከፊት ማኖራቸው ስለደራሲው ስራዎችና ታላቅነትም ከንጉሰ ነገስቱ የበለጠ  ምስክር  የማይገኝለት አድርጎታል፡፡ይህ ጊዜን፣ ስፍራንና ሁኔታን አጣምሮ እጅግ  ጥልቅ ከሆነ የግል ውስጣዊ ስሜት ፈንቅሎ የወጣው ቃል፣ እውነተኛ ስሜትን ገላጭ ንግግር፣ ከዚያን በፊትም ሆነ ከዚያን በኋላ ብዙውን ጊዜ  ከንጉሰ ነገስቱ አፍ ሲነገር ያልተሰማ አይነት ነው፡፡
ምክንያቱም ስለ ሁሉም ነገር “እኛ” በሚል  የፕሮቶኮል ስርዓት እንጂ፣ “እኔ” በሚል ግላዊና ስሜታዊ ቃል መናገራቸው ያልተለመደ  በመሆኑ ነው፡፡
ጃንሆይ በ1932 ዓ.ም ኢትዮጵያ ነጻነቷን መልሳ ከተጎናፀፈች፣ በድል አድራጊነት ከስደት አለም ተመልሰው ከገቡ በኋላ በእንግሊዝ አገር አርፎ የነበረው አስክሬናቸው፣ ከነበረበት ከለንደን አስመጥተው በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ  ካቴድራል እንዲያርፍ አድርገዋል፡፡
ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩም የስድሳ ዘመን አዛውንት እንደነበሩ ታሪክ ዘግቦታል፡፡ ኅሩይን ይሄ ትውልድም ሆነ መጪው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ሊያውቃቸውም-ሊያስታውሳቸውም የሚገባ ታላቅ ኢትዮጵያዊና ስመ-ጥሩ ደራሲ እንደነበሩ አያሌ ስራዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡…ታሪክ በታሪክነቱ፣ ነባር ኢትዮጵያዊ ደራሲያን ደግሞ ህይወታቸውንና ስራዎቻቸው ለተከታዩ ህብረተሰብ መተላለፍ ያለበት መሆኑን እያሳሰብኩ፣ በሁለት ክፍል ያሰናዳሁትን ጽሁፌን እንዲሁ እያዋዛሁም፣ እያሰናሰልኩም ለማቅረብ እሞክራሁ፡፡
ብላቴን ጌታ ኅሩይ በትልቁ የታሪክ ድርሰታቸው በሆነው በዚህ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፣ ከንግስተ ሳባ ይነሱና እስከ ድል ነግድ፣ ቀጥሎ የዛጉዌን ዘመን፣ ከዚያም ከይኩኖ አምላክ እስከ ልብነ ድንግል የነበረውን ክፍል በመጠኑ ከዳሰሱ በኋላ፣ ከነጋሲ እስከ ኃይለ መለኮት ድረስ ያለውን የሸዋን ታሪክ በዝርዝር አቅርበውታል፡፡ ኅሩይ የማናውቀውንና ያልደረስንበትን የአገራችንን የሩቅ ዘመናት ታሪክ ሁለገብ በሆነ መልኩ በስፋትም-በጥልቀትም እንዳሻን ገልጠን ለማየት የሚረዳንን ይህን መጽሐፋቸውን ስናነብ፣ ወደ ኋላ አስጉዘው መለስ ብለው ደግሞ ኢትዮጵያ በታሪኳ ምን አይነት አስተዳደርና ነገስታት እንደነበሯት ለመመራመርና ህይወታቸውን ለማቃኘት ብዙ እድሎችን ይሰጠናል፡፡
ደራሲው ወደ ቅርቡ በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በኢትዮጵያ መድረክ ላይ በተለያየ ደረጃ ገነው በነበሩበት የዘመነ መሳፍንቱ አጼ ቴዎድሮስና የሸዋው ሚኒሊክ…በእነዚህ ሁለት ታላላቅ ሰዎች መካከል የተፈጠረውን የሻከረ ስውር ሁኔታ ከነ-ምክንያቱ በጥልቀት ለማወቅ የሚረዱትን መረጃዎችና ሰነዶች ከታሪኩ ሂደት ጋር አያይዘው፣ በመጽሐፋቸው ውስጥ ለትውልድ በማስተላላፍ በአጠቃላይ ለታሪክ አንባቢያን ብቻ ሳይሆን በተለይ ለታሪክ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ ግምቱ እጅግ ከፍ ያለ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ታላቅ የታሪክ ጽሑፍ ሰንደውልናል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ታሪክ ከመታተሙ በፊት ብዙ ተግዳሮቶች ገጥመውታል፡፡ ኅሩይ ይህን ለመጻፍ ያቀዱትን የኢትዮጵያ ነገስታት ታሪክ መጻፍ ጀምረውት ሳለ፣ ከጻፉት ውስጥ መቶ አስራ ሶስት ገፆች ለህትመት  በቅተው፣ ሌሎች ከመቶ ያላነሱ ገፆች በእጅ ጽሁፍ ላይ እንዳሉ በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ በደረሰው የኢጣሊያ ፋሽስት ወረራ ምክንያት ደራሲው ስራቸውን በማቋረጥ፣ ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ወደ ውጭ  አገር ለመሰደድ በመገደዳቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ  የመጨረሻ ጽሁፋቸው የሚቆመው ከአፄ ዮሐንስ ዕረፍት በኋላ ንጉሰ ነገስት የሆኑትን የዳግማዊ ምኒሊክን ዘመነ መንግስት የመጀመሪያውን ክፍል፣ ማለትም ከውጫሌ ውል እስከ የአድዋ ጦርነትና ታላቅ ድል ድረስ ያለውን (1981-1988) የታሪክ  ክስተት በመተረክ ለማገባደድ ሲሞክሩ ነው፡፡ ኅሩይ የአፄ ሚኒሊክን ዘመን በዳሰሱበት ምዕራፍ ውስጥ የሚያወጉን አንድ የታሪክ ሁነትን ቀጥሎ እንመልከት፡፡…ንጉስ ሳህለ ስላሴ ለጊዜው ለሸዋ ለኋላው ለሙሉ ኢትዮጵያ ጥቅም የሚሆን ስራ ለመስራት ከማሰባቸው በፊትም የውጭ አገር ነጋዴዎችና የወንጌል መልእክተኞች በከተማቸው እንዲኖሩ አድርገው ነበር፡፡
 በኋላም የእንግሊዝ ንግስት የቪክቶሪያ መላእክተኛና ቀጥሎም የፈረንሳይ ንጉስ የትልቁ ሉዊ ፊሊፕና መልዕክተኛ እንዲመጡ ፈቀዱ፡፡ ከመጡም በኋላ በአንኮበርና በደብረብርሃን በአንጎለላም ከተሞቻቸው በየኦሮሞም አገር ሲሄዱ እያስከተሏቸው ይሄዱ ነበር፡፡ ሰፈርም በሆነ ጊዜ እነዚህ የውጭ አገር ሰዎች እንደ አገራቸው ልማድ የማደኛ ጠመንጃቸውን እየያዙ ወደ ዱር እየገቡና ቆቅና ዳክዬ ዝይም…እነዚህንም የመሳሰሉትን የባህር አሞሮች ሁሉ እየገደሉ በግልጥ በህዝቡ ሁሉ ፊት ይበሉ ነበርና፣ በዚህ ዘመን የነበረች ግጥም አዋቂ ሴት እንደዚህ ብላ ገጠመችባቸው፡-
አረ አይገባም ነበር በነጋሲ ፊት
አረ አይገባም ነበር በወይዘሮ ፊት
የሚበላ ሰው ቁራና  ጭልፊት
ምታተኛ ነው ጥበበኛ ነው ብለው ይሉታል፡፡
ይህ ሲሰነብት ጥሉም ያቅታል
የርስዎስ ጋሻ ከቶ አይደፈርም
እንዲህ ያለ ወዳጅ ለልጅም አይሆንም፡፡
ኅሩይ እንኳን ያኔ ዛሬም ለሰው ዘር በሙሉ ጠቃሚ የሚሆን የመንፈስም ሆነ የስጋን የተቃና መንገድ የሚያመላክቱ፣ ቀጥተኛ ህይወትንም በመልካም አላማ የሚያንጹ፣ ከፍ ያለ ሀሳብ ማፍለቅ የሚችሉ፣ እጅግ የላቁ ምርምሮችን በማድረግ ከሰው ልጆች የላቁ ተግባራት መካከል የተወደደውን ሲከውኑ የኖሩ ምሁር ናቸው፡፡
 በትውልዶች ሁሉ እንዲህ ለመታወስ ያስቻላቸውም ይኸው ድንቅ ግብራቸው ነው፡፡ ለብላቴን ጌታ በይበልጥ ቦታ እንድንሰጣቸው የሚያደርገን ደግሞ በቤተ-መንግስት የነበራቸውን ከባድና ፋታ የማይሰጥ ስራ በድለው፣ ለሚጽፉት መጽሐፍ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ለአገራቸው ህዝብ በነበራቸው ፍቅር ምክንያት፣ ካወቁት ከብዙው ጥቂቱን ሳያሳውቁ ቢቀሩ ለትውልድ እሚተርፈውን ኪሳራ በማመዛዘን ሸጋ አበርክቶዋቸውን አኑረውልናል፡፡ ለዚህ ጽሁፌ ለመውጫነት እንዲሆነኝ ከዚሁ  የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንድ ተረክ መዝዤ ላብቃ፡፡
በአጼ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግስት  በቆላው አገር የሚኖሩ ባላባቶች አንድም ኃይላቸው እየደከመ፣ አንድም በሞት እያነሱ መሄዳቸውን ተከትሎ ይሉናል ኅሩይ…. ሸዋን ደግሞ መሐመድ ግራኝ ካጠፋው ወዲህ አገሩ ተከፋፍሎ በየባላባቶች ይገዛ  ነበርና አስፋ ወሰን እነዚህን የተከፋፈሉትን አገሮች አንድ አድርጎ  ጠቅሎ ለመግዛት ስላሰበ፣ ወደ ቆላ አገር ይዘምት ነበርና ስለዚህ የሞረት ጥዱ ለመርድ አዝማች አስፋ ወሰን ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ግጥም ልኮበት ነበር፡-
”አስፋ ወሰን ይፋት ጠንክረው ይረሱ
ሞረት ጥዷል /ጥዱ አለ/
ብለው ከመመላለሱ
አስፋ ወሰንም ሲመልስ
ለሞፈር ለቀንበር ለመቃን
 ለጉበን የሚሆነኝን
ሳልቆርጠው አልቀርም ዘንድሮ ጥዱን
ጥዱም ሲመልስ
“ያባቴ አገር ሞረት ሴቱን ያሳምራል፣
ወንዱን ያደረጃል
ምንጩን ያመነጫል
ጠበሉን ያፈልቃል
ቢለመልም እንጂ ጥዱ መቼ ይደርቃል?›› አለ፡፡


Read 1708 times