Saturday, 03 June 2023 13:23

“መሬቱ ቢገለበጥ ኩንቲ እጠግብ ነበር፤ ግን የት ላይ ሆኜ?” አለች ዝንጀሮ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 አንድ የህንዶች ተረት አለ፡፡
አንድ ሽማግሌ አባት የመሞቻቸው ጊዜ ሲቃረብ፣ አምስት ልጆቹን ይጠራል፡፡ “ስሙ ልጆቼ፤ የመሞቻዬ ጊዜ እንደተቃረበ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ በህይወታችሁ ሳላችሁ በጭራሽ ባታደርጓቸው ደስ የሚሉኝን ልንገራችሁ፡፡”
ሁሉም በፀጥታና በሃዘን ድባብ ውስጥ ሆነው ያዳምጣሉ፡፡
በተቻለ መጠን ሃገር ከድታችሁ ወደ ውጭ ለመሄድ አታስቡ፡፡
ከሄዳችሁም ያለ በቂ ምክንያት አትመለሱ፡፡
ካልተመለሳችሁም እዛው ጠንክሩ እንጂ፣ ባልጠና አካልና ባልጠና ልቦና፣ ጊዜያችሁን በዋልጌነት አትጫወቱበት፡፡
ከተሳካላችሁ በኋላ ግን በጭራሽ አገራችሁን አትርሱ፡፡
ይህን ካለ በኋላ ለአንዴም ለሁሌም ፀጥ አለ፡፡
ከጊዜ በኋላ ከአምስቱ አራቱ ልጆች ወደ ውጭ ሀገር ሄዱ፤ አንዱ አገር ውስጥ ቀረ፡፡
አገር ውስጥ የቀረው የአባቱን ቤት ሸጦ እየመነዘረ መኖር ጀመረ፡፡
ውጭ ከሄዱት አንደኛው ደግሞ ጨርሶ ዋልጌ ሆነ፤ገንዘብ መዝራት፣ መስከር፣ መጨፈር ሆነ ስራው፡፡ ግን ገንዘብ አፈራ፡፡
ሌላኛው እጅግ ሀብታም ሆኖ መቼ ሀገሬ ተመልሼ በገንዘቤ ተምነሽንሼበት ይል ጀመር፤ ሶስተኛው ግን በቶሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰና የራሱን ኑሮ ይኖር ጀመር፡፡
አራተኛውና የመጨረሻው ትንሹ ልጅ ግን ውጭ ሀገር ሆኖ፣ የአባቱን ቤት መልሶ ለመግዛት የሚችልበትን መንገድ ሲፈልግና ጊዜ ሲጠብቅ ቆየ፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ሀገራቸው ተገናኙ፡፡ ስለ ትላንትና ውሏቸው መወያየት ጀመሩ። የመጨረሻው ልጅ አንድ ጥያቄ ያነሳል፡፡ “ለመሆኑ ከመካከላችን የአባቱን ቃል ያከበረ ማን ነው?” በተራ በተራ ይመልሱለት ጀመር፡፡
በመጀመሪያ አገር ውስጥ የቀረው መለሰ፡- “የአባቴን ቃል ያከበርኩ እኔ ነኝ፤ አባቴ አገራችሁን አትክዱ በሎ ነበር፤ እሱን ፈፅሜያለሁ ዛሬም ለአባቴ ቃል ታማኝ ነኝ፡፡”
ሁለተኛው የመለሰው ወደ አገሩ ቶሎ የተመለሰው ነበር፡፡ “የአባቴን ቃል ያከበርኩ እኔ ነኝ፡፡ በሁኔታዎች ተገድጄ ከሀገር ብወጣም ተመልሻለሁ” አለ፡፡
ሶስተኛው፡- “እኔ በበኩሌ ውጭ ከኖራችሁ ጊዜያችሁን በዋልጌነት አታሳልፉ ያለንን ቃል ለማክበር ሞክሬያለሁ፡፡ ነገር ግን ውጭ ሀገር አባባ እንዳሰበው አደለም፤ ገንዘብ ለማግኘት ገንዘብ መመንዘር ግድ ነበር፡፡ ያንን አድርጌ ገንዘብ አፍርቼ መጣሁ”
አራተኛው፡- “እኔም አገር እንደከዳሁ አይቆጠርም፤ ምክንያቱም የናጠጥኩ ሀብታም ሆኜ ተመልሻለሁ፤ ጊዜዬን በከንቱ አላሳለፍኩም” አለ፡፡
አምስተኛው፡- “በበኩሌ የአባቴን ቃል ያከበርኩ እኔ ነኝ እላለሁ፤ ምክንያቱም አባታችን በታቻለ መጠን አገር ከድታችሁ አትሂዱ ሲል ከቻላችሁ ማለቱ ነው፡፡  ከመሬት ተነስታችሁ ውጪ እንሂድ አትበሉ ማለቱ ነው፤ ከሄዳችሁ ያለ በቂ ምክንያት አትመለሱ ሲልም፣ በመጀመሪያ ከሀገር ያስወጣችሁ ጥያቄ ተመልሶልኛል ወይ? በሉ ማለቱ ነው፡፡
 ጊዜያችሁን አትጫወቱበት ሲልም አካልና መንፈሳችሁን ለውጭ ሀገር አሸሼ ገዳሜ አታስገዙ፣ ሰብእናችሁን አትሽጡ ማለቱ ነው፣ በንዋይ አትደለሉ ማለቱ ነው፡፡”
የቀሩት ወንድሞቹም በጥሞና አዳመጡት፡፡ ግን ልባቸው አልተቀበለውምና በአፋቸው ተቃወሙት፡፡ ተከራከሩት፡፡ ክርክሩ እጅግ ተጋጋለና አንደኛው በስለት ሊወጋው ተነሳ፡፡
 ሆኖም አንድ ድምፅ በድንገት በቤት ውስጥ ተሰማ፡፡
“ልጆች” አለ፤ የአባታቸው የሙት መንፈስ ነው፡፡
ሁሉም ፀጥ አሉ፡፡ “በህይወት እያለሁ ትጨቃጨቁ ነበር፤ ዛሬም እየተጨቃጨቃችሁ ነው፡፡ ሁላችሁም እራሳችሁን ከጥፋተኝነት ነፃ ለማድረግ እየሞከራችሁ መሆኑ ገብቶኛል፡፡ ይህን ትታችሁ የሁላችንም አስተዋፅኦ ቢደማመር ምን ይፈጥራል ብላችሁ ጠይቁ፡፡ እኔን አያድነኝም-አይመልሰኝም፡፡
 ሆኖም ቀሪው ትውልድ መዳን አለበት፤ መኖር አለበት፡፡ የሚያድናችሁ ስለ ነገ ማሰብ ብቻ ነው፡፡ እኔም ሞትኩ፤ እናንተ ከእንግዲህ ዳኑ፡፡ መዳን የምትችሉት ዛሬ ላይ ቆማችሁ ስለ ነገ በማሰብ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም አእምሮአችሁን ከትላንት ነፃ አድርጋችሁ ጀምሩ፡፡” ድምፁ ተሰወረ፡፡ ልጆቹም ከድንጋጤያቸው ሲነቁ አባታቸው ያለውን ፈፅመው ለመዳን ወሰኑ፡፡
***
አዕምሮን ከትላንት የፀዳ ማድረግ መታደል ነው፡፡ በደልና ግፍ እንደ ጥቁር ጥላ በተከተለን ቁጥር ከመሳቀቅ ንስሃ ገብቶ ወደ ፊት መራመድ ይመረጣል፡፡
በአገራችን አያሌ የፖለቲካ ድርጅቶች በቅለዋል፡፡ ጥቂቶቹ ገና በችግርና በቡቃያ ደረጃ ተቀጭተዋል፡፡
ከፊሎቹም ግማሽ መንገድ ተጉዘው ጠውልገዋል፡፡ ከፊሎቹ በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ጨምሮ አሁንም አሉ፡፡ ገና ጉዞ ላይ ናቸው፡፡
በየዘመኑ ከመጡ መንግስቶች ጋር ያበሩ ነበሩ፡፡
ገና የሚያብሩም አሉ፡፡ ሁሉም የየበኩላቸውን የህሊና ፅዳት ፍለጋ እጃቸውን መታጠቡን ተያይዘዋል፡፡
 ሆኖም ዛሬም ከየራሳቸው የፖለቲካ ንፍቀ-ክበብ ባለመውጣታቸው ከትልቁ የአገር ስእል፣ ከህዝቡ ጥቅም አንፃር ጉዳዩን ያዩት አይመስለኝም፡፡
ስለ ነገ በቅጡ የማሰብን ነገር ፕሮግራማቸውም ሆነ የኢላማ መነፅራቸው ከልብ አላስተናገደም፡፡
አንዳንዶቹ “መጫኑንስ ጫኑ ግን ገብስ ይሁንልኝ” እንዳለችው አህያ፣ ለእነሱ የሚቀላቸውን ሸክም በመሸከም ብቻ ሊገላገሉት ይሻሉ፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ “ሞት አለና ድንገት ለስንቃችሁ ደግ ስሩ” ቢባሉም እኔ ያልኩት ምን ሆነና ብለው በግትርነት ጎዳና ላይ ናቸው፡፡ ሌሎቹ “የእንጨት ምንቸት እራሱ አይድን ሰው አያድን” አይነት ብቻ ሆነዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የምንጓዘው የት ድረስ ነው፣ ግባችን ምንድን ነው፣ ህዝባችን የት ላይ ይጠቀማል? የሚለው ነው፡፡
ስብሰባዎች ቢደጋገሙ፣ ኮንፈረንሶች ቢሟሟቁ፣ ዱለታዎች በየማታው ቢጋጋሉ በመካያው “ማረፊያችን ለሀገራችን መሻሻል ምን ያህል ፍሬ ይሆናል?” ካላሉ በየራስ አጥር ታጥሮ፣ እኔ ነኝ አንደኛ ከማለት ያለፈ ድል አይሆንም፡፡
ዛሬ በአገራችን የምንመኘውን ለውጥ ለማምጣት ”የት ቦታ ቆመን?” ማለት ተገቢ ነው፡፡
 አርኪሜደስ የተባለ ሳይንቲስት “give me a lever and fulcrum and a place to stand and I can move the earth” ብሎ ነበር፡፡  
(“ሺብልቁን እና የምቆምበትን ቦታ ብትሰጡኝ አለምን አጎናት-አጦዛት ነበር” እንደማለት ነው፡፡) በ13 ዓመት እድሜያችን ውስጥ የት ጋር ቆመን ያለፉትን እንነቅፋለን? የት ጋር ቆመን የሌሎችን ፖለቲካዊ አካለ-ጎዶለነት እናያለን? በምን የሞራል-እሴት ትላንትንና ሌሎችን ተወቃሽ፣ እራሳችንን አወዳሽ ለማድረግ ይቻለናል? ይሄ ገብቷት ነው መሰል የአገራችን ዥንጀሮ እንደ አርኪሜደስ መሆን ሲያምራት፤ “መሬቱ ቢገለበጥ ኩንቲ እጠግብ ነበር፤ ግን የት ላይ ሆኜ?” አለች አሉ፡፡
ሁሉም ድርጅቶች ሊያስቡበት ይገባል፡፡ የልጆቹ አባት እንዳሉት፤ “የሁላችንም አስተዋፅኦ ቢደማመርስ  ምን ይፈጠራል?” ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡


Read 1555 times