Saturday, 03 June 2023 12:38

አሚጎስ ቁጠባና ብድር በ5 ዓመት ውስጥ የሃብቱን መጠን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ አቅዷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    የ10ኛ ዓመት በዓሉን በኢንተርኮንቴኔንታል አክብሯል
         በጥር 2005 ዓ.ም በ20 መሥራች አባላትና በ9ሺ ብር ካፒታል ተቋቁሞ፣ ዛሬ ከ5500 በላይ አባላትና ከ1ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ማፍራት የቻለው አሚጎስ ቁጠባና ብድር ኃ.የተ.ህብረት ሥራ ማህበር፤ ባለፈው  ሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም፣ በኢንተርሌግዠሪ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የተመሰረተበትን የ10ኛ ዓመት በዓሉን አክብሯል፡፡የአሚጎስ ቁጠባና ብድር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍጼም አብርሃ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ”ማህበራችን በ10 ዓመታት ውስጥ ያገኘው ክብር በአጠቃላይ ሠራተኞቻችን ከላይ እስከ ታች ያሉ የአመራር አካላት በመቀናጀት በአንድነት በመሥራታቸው የመጣ  ነው፡፡ ወደፊትም በአደራ የተሰጠንን እምነት ለመጠበቅና የአገልግሎታችንን ጥራት በቀጣይነት ለማሻሻል መሥራታችንን እንቀጥላለን፡፡” ብለዋል፡፡
ማህበሩ፤ በአሁኑ ጊዜ ከ5500 አባላት በላይ ሲኖሩት፣ ለ2750 የማህበሩ አባላት ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር የሰጠ ሲሆን ብዙዎችን አባላት የግል ሥራ እንዲጀምሩ፣ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ፣ የስራ መኪና እንዲገዙ እንዲሁም በተለያየ የሥራ ዘርፍ እንዲሰማሩ እያገዘ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
አሚጎስ ከሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች መካከል የግል ብድር፣ የቢዝነስ ብድር፣ የመኪና ብድር፣ የትምህርት ብድርና የቤት ብድር ይገኙበታል፡፡
የማህበሩ አባልና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ፣ በአምራች ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ ከማህበሩ ከፍተኛውን ብድር፣  7ሚ.500ሺ ብር  በመውሰድ፣ ለሥራቸው ማስፋፊያ ተጠቅመዋል፡፡ የአሚጎስ ብድርም ሆነ የአገልግሎት ፍጥነት እሳቸው ከሚሰሟቸውና ከሚያውቋቸው የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች በእጅጉ እንደሚሻል ባለሃብቱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አሚጎስ፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት፣ ሃብቱን ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ለማሳደግና የራሱ የሆነ ህንጻ ለመገንባት ወጥኖ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡


Read 762 times