Saturday, 03 June 2023 12:26

አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ የፀደይ ባንክ አምባሳደር ሆኖ ተሾመ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ፣ የፀደይ ባንክ ብራንድ አምባሳደር ሆኖ ተሾመ። አርቲስቱ ይህን ሹመት ያገኘው ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም   በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደ  ሥነስርዓት ነው።
አርቲስት ሰለሞን ለፀደይ ባንክ ብራንድ አምባሳደርነት የተመረጠበት ዋና ምክንያት፣ በኪነጥበቡ ዓለም በሙያው በፈጠረው ተወዳጅነትና በበጎ አድራጊነቱ እንዲሁም  በመልካም ሥነምግባሩ እንደሆነ፣  የፀደይ ባንክ ከፍተኛ አመራሮች በስነስርዓቱ ላይ ገልፀዋል።
ከ3 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋምነት ተነስቶ፣ በ50 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ሐብት ወደ ፀደይ ባንክነት ያደገው ተቋሙ፣ አርቲስቱን የባንኩ ብራንድ አምባሳደር አድርጎ በመሾሙ ታላቅ ኩራት እንደሚሰማው የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውም ወሰን ተናግረዋል።ፀደይ ባንክ በወርሃ መስከረም አጋማሽ፣ በፀደይ ወቅት፣ አማራ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋምን ተክቶ፣ ባንክ ለመሆን የበቃ  ሲሆን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ  ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማገልገል የተቋቋመ ከመሆኑ አንጻር፣ በአሁን ሰዓት በመላ ሃገሪቱ በተለይም በገጠሩ አካባቢ 600 ቅርጫፎችን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡  አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ፣ በኢትዮጵያ የፊልምና ቴአትር ኢንዱስትሪ፣ እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ድንቅ የትወና ብቃት ያለውና  አዛኝና ሩህሩህ  ባህሪን የተላበሰ በጎ አድራጊ በመሆኑ፣ በብራንድ አምባሳደርነት እንዳስመረጠው የተገለፀ ሲሆን፤ እስከዛሬ ከ60 በላይ ፊልሞች ላይ በአብዛኛው በመሪ ተዋናይነት፣ ከ16  በላይ የመድረክ ቴአትሮች፣ ከ6 በላይ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች እንዲሁም  በርካታ የሬዲዮ ድራማዎች ላይ በመሥራት አስደማሚ የትወና  ብቃቱን አስመስክሯል፡፡ ከሐገር ውስጥና ከውጪ ጉማንና ኢትዮ ፊልም ፌስቲቫል ሽልማቶችን ጨምሮ በርካታ ሸልማቶችን ማግኘት ችሏል፡፡ አርቲስቱ የዛሬ 8 ዓመት ባቋቋመው “ሕብረት ለበጎ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት” አማካኝነት፣ በገንዘብ እጦት ህክምና ማግኘት ያልቻሉ ወገኖችን የማሳከም ህልሙን እውን ለማድረግ ፣ በለገጣፎ ለገዳዲ 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ወስዶ፣  የሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ እያካሄደ ይገኛል።አርቲስት ሰለሞን የፀደይ ባንክ አምባሳደርነትን የተቀበለበትን ምክንያት ሲናገር፤ አንደኛ የባንኩ መሪ ቃል የሆነውን፣ “የሁሉም ባንክ” የሚለውን በመውደዱ፣ እንዲሁም  በአርቲስትነቱ እርሱም  የሁሉም አገልጋይ በመሆኑ፣ ከትንሽ ተነስቶ  ትልቅ  ደረጃ በመድረሱ፣ በገንዘብ እጦት የተቸገሩትን ሲረዳ በመቆየቱና ይህም እርሱ ከሚሰራው የበጎ አድራጎት ጋር በመመሳሰሉ እንደሆነ አስረድቷል፡፡
 ፀደይ ባንክ፣የቁጠባና ብድር ተቋም ሆኖ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ፣”አፍሪካ ባንከርስ አዋርድ”ን ጨምሮ 6 ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘቱም ታውቋል፡፡ ባንኩ ስራ የጀመረው በ7.75 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ አሁን በአጠቃላይ  13.3 ቢሊዮን ብር  ካፒታል  እንዳፈራ  የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ 13 ሚሊዮን የሚደርሱ ገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞች እንዳሉትም ጠቁመው፣ይህም  ቁጥር ከንግድ ባንክ ውጪ በግል ባንክ ደረጃ ያልተደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

Read 747 times Last modified on Saturday, 03 June 2023 13:04