Saturday, 27 May 2023 17:46

የአጭር አጭር ልብወለድ

Written by  በረከት ተስፋዬ-
Rate this item
(3 votes)

 ትንሽ የመኖር በር...
                      
          ሕይወት ይሄ ብቻ አይደለም። የምናየው ብቻ አይደለም መኖር __ የሚታየው፡፡ አንዱ የሕይወት መልኳ ነዉ። ምልዓትነቷን አይገልፅም። ይችን የምትታየዋን የኑሮን ገፅታ፣ ለእኔ ግን ምሉዕነቴን ለመደበቅ መሸትሸት ሲል የአረቄ ቤቶችን በር አንኳኳለሁ።
“ማነዉ?”
መልስ መስጠት አልፈልግም። እኔን ይዤዉ እዛ ድረስ እንደሄድኩ እንዲሰማኝ ለምን አደርጋለሁ።
መልሼ አንኳኳሁ። ‘ኳ .. ኳ .. ኳ .. ኳ’
የበሯ ግማሽ ክፍል በመሸጎሪያ የተደገፈ ዝግ ክፍሏ ድረስ ተከፈተ። በካቲካላ ጠረንና በሰካራም የተወለጋገዱ ቃላቶች ታጅቤ ወደ ዉስጥ ገባሁ። ይሞቃል። የዉስጤን ቅዝቃዜ እስከ መለኪያዉ ድረስ ደርሼ ለመሰናበት ጓጉቼ ግራ ቀኜን አማተርኩ። ብዙ ዓይን አረፈባት፤ ኮሳሳ ገላዬ።
መነጠልን እንደ ሰማይ የሚፈራ ማህበረሰብ ውስጥ ሐሳቡን ሊሸሽ የመጣ ባለበት፣ መፅሐፍ ይዞ መገኘትን የሚያህል እብደት የት አለ? ከቤቷ ጥግ ላይ ተሰቅሎ ዳንቴል ከለበሰ ቴፕ አፍ ውስጥ ጥላሁን ይተነፍሳል።
“ፈልጌ አስፈልጌ ያን ሰሞን ያጣኋት ... 4 ኪሎ ... 6 ኪሎ ... ካዛንችስ...”
ከጥርሴ ሳቅ እያመለጠኝ ተቀመጥኩ። የከተማ ናፍቆታቸዉን በሙዚቃ ጉያ ውስጥ ተወሽቀው፣ ጥላሁን ፀጉራቸዉን የሚያሻሽላቸዉ መስለዉ ታዩኝ።
መርሳቴና ሞቴ ባ’ንድ ላይ የአረቄ መለኪያው ላይ ተቀዱ። በአንድ ትንፋሽ ጠጣኋቸዉ።
“ፈልጌ አስፈልጌ አረቄ ቤት መጣሁ...”
ለመኖር የተፈጠረ እግሬ ሞትን ያሳድዳል። ለመስራት የተፈጠረ አንደበቴ የአምላክን
ቤተ-መቅደስ ያፈርሳል። እንዲህ እንዲህ እየተሟገትኩም እስካሁን አጠገቤ እንደተቀመጠች አላወኩም።
የምትሞርደዉ ጉረሮዋ ከዚያ ሁሉ ሁካታ አልፎ ተሰማኝ። አየኋት ... አየችኝ።
ሕይወትን እንድወዳት የሚያደርገኝ ክፍሌ ተገለጠ። ተረትኩላት።
ተረት ተረት
“የመሰረት”
አንችን መንጋት አንችን መምሸት
“እሽ”
ሁለት ክንፍሽ ሲገለጥ ባይ
የት ተገኘሁ? ሰማይ!
ምን አገኘሁ? ሌላ እኔን!
ባየዉ ባየዉ አይኔን አይኔን።
ተረት ተረት
“የላም በረት
በረት በረት”
ክልክላችን ላይ የምናድርበት።
በቃ! በቃ!!
“ምኑ በቃህ?”
አንችን ስሆን አየኝ አላህ።
“እሰይ...!”
ተረቴን መልሽ
“ዳቦዬን ይዘህ ና”
አልጠገብሽም
“አዎ!”
ምነዉ?
“ምንም።”
ዳቦ ለሆዶ እንጅ ለነፍስ ሆኖ አያዉቅም።
“አይ እንግዲህ...”
ክንፍሽ ሲገለጥ አንድ እግሬ አጠረኝ
“ለምን?”
መሄድ እያማረኝ።
“መብረር ስትችል ና”
ነይና አስተምሪኝ ሟች ነኝ ለጎዳና።
“እ?”
መጣሁ።
“ስትመጣ ግን”
እሽ
“እግር የለም ብለህ እመን።”
ሄድኩ። ወደ’ማይመለሱበት ...
አመሰገንኳት።
ለመወሰኔ ትንሽ መዋቀሻ ስለሰጠችኝ...




Read 705 times