Monday, 29 May 2023 00:00

የትኛው “ጉንዳን” እንሁን?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ትውስታ አድማስ

                    የትኛው “ጉንዳን” እንሁን?


          ”--የፖለቲካችን አሰላለፍ ጭራና ራስ ሆኗል። ሁለቱም ተስማምቶ መሀል ላይ መገናኘት ሲችሉ እርስ በርስ መናከስን መርጧል፡፡ አንድ አካል አንድ አምሳል መሆናቸውን ረስተው፣ አንዱ ጫፍ በሌላኛው ጫፍ ላይ ይነሳል፡፡ መሀላቸው እንዳይበጠስ እንደ መጠንቀቅ ይሳሳባሉ፡፡ ከተበጠሱ በኋላ እንደ መማርና እንደ መጠገን፣ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ይዘምታሉ፣ይፋለማሉ፡፡--”
               - በክብሮም በርሀ-


         ጉንዳኖች ተዓምረኛ ፍጥረቶች ናቸው፡፡ ከምንም በላይ ህብረታቸው የሚደንቅ ነው፡፡ ጉንዳኖች በህብረት “እኔ ነኝ ያለ” ወንዝ ማቋረጥ ይችላሉ። ጉንዳኖች በታታሪነታቸው የሚታወቁ አስገራሚ ፍጥረታት ሲሆኑ፤ የሠው ልጅን የማስተማር ብቃቱ አላቸው፡፡ የፍጥረታት ሁሉ ንጉስ ተደርጎ የተሾመው “ሰው”፣ በመጨረሻ ላይ ለጉንዳን እጁን ብቻ ሳይሆን እግሩን ይሰጣል፡፡  ጠቢቡ ያሬድ ከጉንዳን መማሩ ይነገራል፡፡ በትምህርት ተስፋ ቆርጦ የነበረው ያሬድ፤ ዛፍ ስር ሆኖ “ወድቆ መነሳትን” ተምሯል፡፡ በውጤቱም፣ ከውድቀት ተነስቶ ታሪክን ሰርቷል፡፡ ተንጠራርተን ጉንዳን ብለን የምንሰድባቸው ቻይናውያን ሳይቀር እንደ ያሬድ ከጉንዳን የተማሩ ይመስላል፡፡ የቻይናውያን የጥንካሬ ዋነኛ መስፈርታቸው  “ወድቆ መነሳት” ነው፡፡ አሸዋ ላይ ወድቆ ዶግ አመድ የሚሆን ብርጭቆ ከቁስ አይቆጥሩትም፡፡ እርግጥ ነው እኛ የምናውቃቸው የቻይና ዕቃዎች፣ አሸዋ ላይ “አሸዋ” የሚሆኑ ናቸው፡፡ የመድሎው ዓይነት፣ ወደ አደጉ ሀገሮች የሚልኳቸው ዕቃዎች ደግሞ “ተሰብረው የማይሰበሩ” መሆናቸው ይነገራል፡፡ አቤት ልዩነት፣ አቤት መናናቅ!
ወደ ነገራችን ስንመለስ፣ “The Story of Philosophy” በተሰኘው የዊል ዱራንት መፅሐፍ ገፅ 245 ላይ ሾፐንሀወር የተባለ ፈላስፋ፣ ቡልዶግ የተባለ የአውስትራልያ ጉንዳንን በተመለከተ ይነግረናል። የፈላስፋ ነገር ለማንም ሰው የማይታይ ይታየው የለ፡፡ ጉንዳኑ በሁለት ከተከፈለ በ”ጭራ”ና በ”ራስ” መሀከል  ለግማሽ ሰዓት ያክል የሚዘልቅ ፍልሚያ ይካሄዳል፡፡ “ጭራ” ሲናደፍ፣ “ራስ” ደግሞ በጥርሱ ይናከሳል፡፡ በውጤቱም ከሁለት አንዱ ይሆናል፤ ወይ ሁለቱም ይሞታሉ አልያ ደግሞ በሌላ ጉንዳን ይበላሉ፡፡ ቻይናውያን፤ “ነብሮች ሲፋለሙ ከተራራ ሆነህ ተመልከት” ይላሉ፡፡ አንደኛው መሞቱ ሌላው ደግሞ ማጣጣሩ ስለማይቀር፣ ሁለቱንም ነብሮች ለመግደል ይቀላል፡፡ እናም፣ እርስ በርሱ የተበላላ ጉንዳን፣ በሌሎች ጉንዳኖችን የሚበላው በቀላሉ ነው፡፡
እኛም ሆንን ጉንዳኖች በተፈጥሮ ቁጥጥር ስር መሆናችን አንድ ያደርገናል፡፡ ማናችንም ብንሆን ከተፈጥሮ ህግጋት ማምለጥ አይቻለንም፡፡ ተፈጥሮ ደግሞ ላጣጣማት ማር፣ ላጠመማት ምሳር ነች። ተፈጥሮን ተጠቅሞና ተጠቦ መኖር ጣፋጭ ነው። ተፈጥሮን አጣቦና ተጣቦ መኖር ደግሞ ተቀርቅሮ መሞትን ያስከትላል፡፡ ተፈጥሮን ተጠቅሞ በፍቅርና በሰላም መኖር፣ ራስን ከህሊና ያወዳጃል፡፡ ተፈጥሮን አጣሞና ግዴለሽ ሆኖ መኖር ደግሞ የገዛ አንገት ላይ እጀ-ገመድ ያስገባል፡፡ ዋናው ነገር አጠቃቀማችን ነውና፡፡
ራስን በጭራ ላይ አዝምቶ የገዛ ነፍስ ማድከም ስራ የሚመስለው ሰው አለ፡፡ የጉንዳኑ ራስ  ጭራን ማጥፋት ቀላል ይመስሏል፡፡ በአንፃሩ ጭራም በራስ ላይ የበቀል በትር ያሳርፋል፡፡ ዳሩ ግን፣ ሁለቱም አይተርፉም፡፡ ሁለቱም ለመበላት ራሳቸውን ይከሽናሉ፡፡
የፖለቲካችን አሰላለፍ ጭራና ራስ ሆኗል። ሁለቱም ተስማምቶ መሀል ላይ መገናኘት ሲችሉ እርስ በርስ መናከስን መርጧል፡፡ አንድ አካል አንድ አምሳል መሆናቸውን ረስተው፣ አንዱ ጫፍ በሌላኛው ጫፍ ላይ ይነሳል፡፡ መሀላቸው እንዳይበጠስ እንደ መጠንቀቅ ይሳሳባሉ፡፡ ከተበጠሱ በኋላ እንደ መማርና እንደ መጠገን፣ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ይዘምታሉ፣ይፋለማሉ፡፡
የፖለቲከኞች ጫፍ መርገጥ (ራስና ጭራ መሆን) ሳያንስ፣ ዳር ቆሞ ሞታቸውን የሚጠባበቅ አይታያቸውም፡፡ ይህ ወገብ በሌለውና ጭራና ራስ ብቻ በሆነው አካል የሚሞከር አይደለም፡፡ “ቆም ብሎ ለማሰብ” መጀመሪያ መቆም፣ ከዛ ደግሞ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለመቆም ወገብ ግድ ሲሆን ለማሰብ ደግሞ ከጭራ ጋር የተሰናሰለ ራስ ያስፈልጋል። ሁለቱም በሌለበት ግን መቆምም ሆነ ማሰብ የሚታሰብ አይደለም፡፡
ፖለቲከኞቻችን በጀመሩት “እልህና ወኔ” ከቀጠሉ፣ የአውስትራልያው ቡልዶግ ጉንዳን፣ “ጭራና ራስ” መሆናቸው አይቀርም፡፡ በጭራና ራስ ተደስቶ የሚያድር ባይኖርም ወገብ ሳይኖራቸው ወገብ፣ እግር ሳይኖራቸው እግር፣ ፍቅር ሳይኖራቸው ልብ ሆኖ የሚያኖራቸው ህዝብ አለ፡፡ የሚያስቀው ነገር የተገላቢጦሽ ሆነና፣ “የምናኖርህ ህዝባችን ሆይ” ብለው መፎከራቸው ነው፡፡ የሚደንቀው ነገር የማኖረው “እኔ ነኝ”፣ “እኔ ነኝ” ማለታቸውና በዚሁ መጣላታቸው ነው፡፡ የሚሰቀጥጠው ነገር፣ እነሱ ጭራና ራስ መሆናቸው ሳያንስ ወገብ ሆኖ የሚያገለግላቸውን ህዝብ፣ “ጭራና ራስ” ለማድረግ መወሰናቸው ነው፡፡ ተስፋ የሚያስቆርጠው ነገር ሁሉም ጭራና ራስ ሆኖ ሲያበቃ፣ ሁሉንም ጠራርጎ የሚበላ “ዳር ተመልካች” እና “እበላ ባይ” መኖሩን አለማየቱ ነው፡፡ ካልተበሉ በቀር አያምኑም ማለት እኮ ነው፤ “ፈንጅ አምካኝ ከስህተቱ አይማርም” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡
ስለሆነም፣ ጥያቄው ቀላል ነው፡፡ ጥያቄው፡- “የትኛውን ጉንዳን እንሁን?” ነው፡፡ ያ ተባብሮና የህብረት ሰንሰለት ፈጥሮ፣ ወንዝን የሚያቋርጠው ጉንዳን ወይስ ያ “ጭራና ራስ” ሆኖ፣ ራሱን በራሱ የሚበላውና ራሱን የሚያስበላው? እሳትና ውሃ ቢቀርብ እጃችንን የምንሰደው ምኑ ላይ ነው?
***
(ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ዌብሳይት፤30 ኦክቶበር 2016)

Read 1227 times