Saturday, 27 May 2023 17:05

ፒራሚዳዊ ዝርፊያና ቀጥተኛ የትስስር ግብይት -

Written by  ኤፍሬም አሊ - የኛ መንደር) yegna.mender@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ!
                         
       በሀገራችን ባለፉት ዓመታት ፒራሚዳዊ የንግድ መዋቅርን በመጠቀም እጅግ ጥቂቶች ብቻ የሚከብሩበት ነገር ግን ብዙሃንን የሚያራቆቱበት ህገወጥ የዝርፊያ ስርዓቶች ተግባራዊ ሆነው በስተመጨረሻም እንደ ጉም ተንነው ሲጠፉ ተመልክተናል። መሰረታቸውን በውጭ ያደረጉ እንደ ኩዌስት ኔት፣ ቲያንስ እና ፊያስ 777 የመሳሰሉ እንዲሁም በሀገር ውስጥ የተመሰረቱ መሰል ፒራሚዳዊ የማጭበርበሪያ ስልቶች ወደ ስራ ሲገቡና ራሳቸውን ሲገልጹ፤ ገሃዳዊ ዘራፊነታቸውን በቀመራዊ ሌብነት ደብቆ ለመፈጸም የሚጠቀሙባቸው የዳቦ ስሞች አሏቸው።
በዚህ አደገኛ ፒራሚዳዊ መዋቅር ተመስርተው የሚንቀሳቀሱት ህገወጥ ድርጅቶች፤ ቀጥተኛ ሽያጭ (Direct Selling)፣ ባለብዙ-ደረጃ ግብይት (Multi-level Marketing (MLM)) እና የአውታረመረብ (የትስስር) ግብይት (Network Marketing) በመባል ከሚታወቁት ህጋዊ (ህጋዊ አስመሳይ) የግብይት ዓይነቶች አንዱን ወይም ከአንድም በላይ በመጠቀም ስውር የዝርፊያ ስራቸውን በግልጽ ይጀምራሉ። አንዱ ድርጅት በተዘጋ ማግስትም ሌላኛው (ያው ራሱም በሌላ ስም ሊሆን ይችላል) እንደ አዲስ ተከፍቶ ስራውን ይጀምራል።
ፒራሚዳዊ መዋቅር ለምን ህገ ወጥ ይባላል? ከሌሎቹስ የሚለየው ምንድን ነው? መንግስት ለምን ቀድሞ ሊያስቆም አይችልም? ተጠቃሚና ተጎጂዎችስ ለምንና እንዴት በተደጋጋሚ ሊዘፈቁ ቻሉ? የማማለያና የማወናበጃ ስልቶቹስ ምን ይመስላሉ? ከመገናኛ ብዙሃንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለሞያዎችስ ምን ይጠበቃል? የሚሉትን ጥያቄዎችና ተዛማጅ ጉዳዮች በማንሳት፤ ከዚህ እንደሚከተለው ለመዳሰስ እንሞክራለን።
ፒራሚዳዊ መዋቅር ምንድን ነው?
የፒራሚዳዊ  መዋቅር  ግብይትን  በዋናነት  በዝርፊያ  ተግባርነት  የሚስፈርጀው  የሚጠቀመው  ፒራሚዳዊ  መዋቅር  ነው። ፒራሚዳዊ  መዋቅር  ወይም  ፒራሚዳዊ  ስርዓት  (Pyramid  Schemes)  ስያሜውን  ያገኘው  ፒራሚድ  ከተሰኘው  የሂሳብ ጂኦሜትሪያዊ ምስል ሲሆን፤ ፒራሚድ መሰረቱ ሰፊ ሆኖ ሁሉም የመሰረቱ ነጥቦች ወደ አንድ ነቁጥ የሚሰበሰቡበት ጠጣር ጂኦሜትሪያዊ  ምስል  ነው።  ለምሳሌ  የታላቁ  የግብጽ  ፒራሚድ  የመሰረቱ  ወለል  ስፋት  53  ሺህ  ካሬ  ወይም  5.3  ሄክታር ሲሆን፤  ሁሉም  የወለሉ  ነጥቦች  ከመሐል  በ146  ሜትር  ከፍታ  ላይ  ወደሚገኘው  ነቁጥ  በመሰብሰብ  የሚሰሩት  ምስል ፒራሚድ ይባላል። በዚህ አንጻር የፒራሚዳዊ መዋቅር ግብይት ማለት በፒራሚድ ቅርጽ እየተሳሰሩ ከአንድ ነቁጥ ወደታች የሚሰራጩ አባላትን በማፍራት የሚሰራ የግብይት ስርዓት ወይም የግብይት ማሳለጫ ትስስር ነው።
ፒራሚዳዊ መዋቅር ሊተገበር አይችልምን?
ፒራሚድን ወይም ፒራሚዳዊ መዋቅርን በተመጠነ መልኩ ለተለያዩ ተግባራት ሊውል ይቻላል፤ እየተጠቀምንበት ነው። ለምሳሌ፡- መሰረታቸው ተወስኖ በተለያየ ቅርጽ ለተሰሩ ቤቶች ጣሪያ (እንደ ብዙዎቹ ቤተክርስቲያናት) የምንጠቀምበት መዋቅር ነው። መሰረቱ ካልተገደበ ወይም ከሚገባው ያለፈ ከሆነ ግን (ልክ በጨለማ የእጅ ባትሪን ወደ ሰማይ እንደማብራት) መዳረሻው ፈጽሞ ሊካለል የሚችል አይሆንም። ለዚህ ማስረጃ የሚሆን አንድ ተረክ አንመልከት።
የስንዴ ፍሬዎቹና የቼስ ሳጥኖቹ እንቆቅልሽ፡
ተረኩ በተለያየ መልክ ይቀርባል። አንድ ንጉስ በቼስ ጨዋታ እጅግ ከመደመማቸው የተነሳ የጨዋታውን ፈጣሪ ለመሸለም ይፈልጋሉ። አንድ የጨዋታው ፈጣሪ (ነኝ የሚል ተንኮለኛም) ለመሸለም ይቀርባል። ንጉሱም ተሸላሚው የሚፈልገውን ሁሉ ሊሸልሙት  እንደፈቀዱ  ተናገሩ።  ተንኮለኛውም  (8×8=  64  ሳጥኖች  ያሉትን)  የቼስ  ሰሌዳ  አቅርቦ  “እኔ  ብርም  ወርቅም ሳይሆን በእነዚህ ሳጥኖች ልክ የስንዴ ፍሬ ነው የምፈልገው፤ እርሱም የመጀመሪያዋ ሳጥን ላይ አንድ ፍሬ ስንዴ፣ ሁለተኛዋ ላይ ሁለት ፍሬ ስንዴ፣ ሶስተኛዋ ላይ አራት ፍሬ ስንዴ፣ አምስተኛው ሳጥን ላይ ስምንት ፍሬ ስንዴ እየተደረገ . . . እስከ 64ኛው  ሳጥን  ያለው  ተሰብስቦ  ይሰጠኝ”  ሲል  ጠየቀ።  ንጉሡ  በተሸላሚው  ቀላል  ጥያቄና  ሞኝነት  ተበሳጭተው  “በሉ እንዳሻው ስጡት!” ብለው ባለሟሎቻቸውን አዝዘው ሄዱ። ነገር ግን ባለሟሎቹ በቼስ ሳጥኖቹ ብዛት ልክ የስንዴ ፍሬዎቹን 1፣  2፣  4፣  8፣  16፣  32፣  64፣  128፣  256፣  512፣  1024  .  .  .  እያደረጉ  ለማስቀመጥ  ቢሞክሩም  ሳጥኖቹን  ሳያጋምሱ  የንጉሡ ስንዴ  ሁሉ  አለቀ።  ንጉሡም  እንደቀላል  ቃል  የገቡት  ነገር  ፈጽሞ  የማይቻል  መሆኑን  ሲያውቁ  እጅግ  ደነገጡ።  በኋላ  ግን አንድ  ማምለጫ  ዘዴ  አፈለቁ።  በዚህ  ስልት  ስድሳ  አራቱን  ሳጥን  ሊሞላ  የሚችለው  የስንዴ  ፍሬዎች  ቁጥር  (ከሚታሰበው በላይ) እጅግ ብዙ እንደሆነ ስለገባቸው ተሸላሚውን እንዲህ አሉት፤ “አንተም የሚደርሱህን የስንዴ ፍሬዎች ብዛት በሙሉ ከአንድ ጀምረህ እየቆጠርክ ተናገር፤ እኔም ዋጋውን በወርቅና በብር አድርጌ እከፍልሃለሁ” አሉት። በዚህም ንጉሱ በብልጠት ማምለጥ ቻሉ፤ ምክንያቱም ስንዴውን መስፈርም ሆነ መቁጠር የማይቻል ነውና።
የስንዴ ፍሬዎቹ ብዛት ምን ያህል ይሆን ነበር?
1፣ 2፣ 4፣  8፣ 16፣ 32፣ . . .  እያለ በሚሄደው ስልት ስድሳ  አራተኛው (የመጨረሻው) ሳጥን  ውስጥ የሚቀመጡት  የስንዴ ዘሮች  ብዛት  2  ርቢ  64  (2  to  the  power  of  64)  ይሆናል።  ይህም  ብዛት  9,223,372,036,854,775,808  ሲሆን አጠቃላይ   የስንዴ   ዘሮቹ   ድምር   ደግሞ   18,446,744,073,709,551,615   ያህል   ነው።   ይህን   ወደ   ኪሎ   ስንቀይረው 1,199,038,364,791,120 ኪሎ ሲሆን፤ ይህም ብዛት ከአጠቃላይ የዓለማችንን የስንዴ ምርት  1,553 ጊዜ እጥፍ ይሆናል።
የፒራሚዳዊ መዋቅር ግብይት ለምን በወንጀልና በዝርፊያነት ይፈረጃል?
ከላይ ያየነው የእንቆቅልሹ ተረክ ያልተመጠነ ፒራሚዳዊ ርቢ ከቁጥጥር ውጭ እንደሚሆን የሚያሳይ ነው። በዚህ የግብይት መዋቅርም አንድ ሰው በስሩ ሁለት ሰው እየመለመለ፣ የተመለመሉት ደግሞ ሌላ ሁለት (በድምሩ አራት)፣ አራቱም በየስራቸው ሁለት ሁለት (በድምሩ ስምንት) . . . እያለ በሚሄድ ርቢ እንቀጥል ቢሉ፤ በገሃዳዊው ዓለም ለመተግበር ፈጽሞ አይቻልም። ምክንያቱም የመጨረሻዎቹ ሰዎች በስራቸው የሚመለምሉት ሰው ሊያገኙ አይችሉምና። ለምሳሌ፡- በዚሁ ስልት (በ2 ርቢ) የሚሄደውን መዋቅር 27ኛ ደረጃ ላይ ብንመለከት፤ የተመለመሉት ሰዎች 67,108,864 ሲሆን ለቀጣዩ 28ኛ ደረጃ እያንዳንዳቸው  ሁለት  ሁለት  ሰው  መመልመል  ይጠበቅባቸዋል።  ይህም  ማለት  ከ134  ሚሊዮን  በላይ  ሰው  ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው። ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የግብይቱ ተሳታፊ ቢሆን እንኳ ለ28ኛው ደረጃ የጎረቤት ሀገራትን ህዝቦች መመልመል የግድ ነው ማለት ነው። ለዚህም ነው ያልተገደበ ፒራሚዳዊ መዋቅርን በግብይት ቀርቶ በሰላምታና በመተያየትም ለመተግበር ማሰብ ቅዠት የሚሆነው።
ከሌሎቹስ የሚለየው ምንድን ነው?
ፒራሚዳዊ የግብይት መዋቅር ቀጥተኛ ሽያጭ (Direct Selling)፣ ባለብዙ-ደረጃ ግብይት (Multi-level Marketing (MLM)) እና የአውታረ መረብ ግብይት (Network Marketing) የሚሉትን ስያሜዎች በነጠላ ወይም በጥምረት በተለዋጭነት ሲጠቀም ይስተዋላል።
ቀጥተኛ ሽያጭ (Direct Selling)፡ ቀጥተኛ ሽያጭ (Direct Selling) የምርትና እና አገልግሎት ስርጭት ስልትን የሚገልጽ ሲሆን ይህም ቤት ለቤት (ልክ እንደ “ልዋጭ ልዋጭ” በየደጁ) ወይም ደንበኞች ባሉበት ስፍራ ሁሉ በመድረስ ቀጥተኛ ግብይት የሚያስፈጽም ስልት ነው። ፒራሚዳዊ ግብይትም መሰል መንገድን ቢከተልም፤ ይህኛው አዳዲስ አባላትን በማፍራት ላይ ያተኮረ እንጂ ምርትና አገልግሎትን ማድረስን ያስቀደመ አይደለም። ቀጥተኛ ሽያጭ ለተጠቃሚዎች እርካታ እንዲሁም ለምርትና አገልግሎት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጥ፤ በመዋቅሩ ውስጥ ተመዝግቦ መካተትን አስገዳጅ ስለማያደርግ ያለተጨማሪ ክፍያ (ባልተጋነነ ዋጋ) ይሰራል። የፒራሚዳዊ መዋቅር ግብይት ግን ተመልማዮችን እጅግ በተጋነነ የመመዝገቢያ ክፍያ (ቅድመ ክፍያ) የፒራሚዳዊ እርባታው አካል በማድረግ ከላይ ላሉት የመዋቅሩ አባላት (አዲስ ከገቡት የሰበሰበውን) ያቃምሳል።
በእርግጥ የቀጥተኛ ግብይትና የፒራሚዳዊ ግብይት መመሳሰል ቀጥተኛ ግብይትን እንዲጠረጠር ሲያደርገው፣ ፒራሚዳዊው ግብይትን ደግሞ በቀጥተኛ ግብይት ስም እንዲያጭበረብር አስችሎታል። “Direct Selling a Controversial Business Model” (2022) በተሰኘ የጥናት ጽሁፉ Richard Seow Yeaw Chong እንዳመለከተው፣ ቀጥታ ሽያጭ ከ130 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው የንግድ ሞዴል ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በብዙ ምክንያቶች ቀጥተኛ ሽያጭ ለግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ለመንግስታትም አወዛጋቢ የንግድ ሞዴል አድርጎታል።
ባለብዙ-ደረጃ ግብይት (Multi-level Marketing (MLM))፡ የፖላንድ ምሁራን Justyna Kaźmierczak እና Artur Łabuz በ2018 “MULTI-LEVEL MARKETING፡ FEATURES AND CONTROVERSY” በሚል ርዕስ ባደረጉት ጥናት፤
የባለብዙ-ደረጃ ግብይትም ከፒራሚድ እቅዶች የተቀላቀለና ግራ የሚጋባ መሆኑን ከህዝብ በሰበሰቡት ግብረ መልስ አስረድተዋል። እንደጥናቱ ሁለቱ ግብይቶች ተመሳሳይነትና የተደበላለቀ ሚና ቢኖራቸውም፤ ልዩነት ግን አላቸው። ባለብዙ- ደረጃ ግብይት (Multi-level Marketing (MLM)) ተደራሽነትን ለማስፋት ከቋሚ የችርቻሮ ስፍራ ርቆ ፊት ለፊት መሸጥን ያለመና ህጋዊ ስምምነትን መሰረት ያደረገ ስርዓት ሆኖ፤ በበርካታ ቦታዎች ገበያዎችን ለመፍጠር በቅርንጫፎች ግዥና ሽያጭ ያቀላጥፋል። የፒራሚዳዊ ግብይት ቅርንጫፎቹ አባላቱ ናቸው። የባለብዙ-ደረጃ ግብይት ትርፍ የተመጠነ ሲሆን፤ የትርፉ መጠን የሚወሰነው በምርትና አገልግሎቱ ሽያጭ ብዛት ልክ ነው። ፒራሚዳዊው ግብይት ግን ያለህጋዊ ስምምነት የከፍተኛ ትርፍ ተስፋ በመስጠት ላይ ብቻ ይቆማል። በተጨማሪም ለምርትና አገልግሎት ጥራት ቦታ ስለማይሰጥና (እንደ ባለብዙ- ደረጃ ግብይት) ተመላሽ ምርቶችን ወደመነሻቸው ማድረስ የሚያስችል ስምምነት ስለሌለው ተጠቃሚዎቹንና አባላቱን ለአደጋና ለኪሳራ ያጋልጣል።
የአውታረ መረብ ግብይት (Network Marketing)፡ የአውታረ መረብ ወይም የትስስር ግብይት (Network Marketing) አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ለተጠቃሚው ለማድረስ ያለውን አስቸጋሪ መንገድ ከሰው ወደ ሰው በማስተሳሰር ባልተቋረጠ እና በተሳለጠ መልኩ ማድረስ የሚቻልበት የግብይት ስልት ነው። ይህ ስልት ከምርትና አገልግሎት ሰጪው እስከመጨረሻው ተጠቃሚ ያለውን መንገድ በመረብ በማስተሳሰር፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለመድረስ የሚኖረውን የጊዜ የጉልበትና የገንዘብ ብክነት በማቃለል፣ በቅብብል ለማቅረብ የተዋቀረ አዋጭና ቀልጣፋ ስርዓት ነው።
ከላይ  እንደተመለከትናቸው  ሶስቱ  የግብይት  ስርዓቶች  የየራሳቸው  ልዩ  መገለጫ  ቢኖራቸውም  ብዙ  ጊዜ  የምናያቸው የግብይት  ስርዓቶች  የአንዱን  ወይም  የሁለቱንና  የሶስቱንም  ባህርያት  የያዙ  ሊሆኑ  ይችላሉ።  ፒራሚዳዊው  መዋቅርም በተጓዳኝ የሚሰጠውን ምርት ወይም አገልግሎት ሰበብ በማድረግ (የእጅ ለእጅ ሽያጩን እንደ ቀጥተኛ ግብይት፣ 1፣ 2፣ 4፣ 8፣  16  .  .  .  እያለ  የሚሄደውን  ፒራሚዳዊ  እርባታ  እንደ  ደረጃ፣  እንዲሁም  ፒራሚዳውን  መረብ  እንደ  ትስስር  በመቁጠር) ከላይ  ካየናቸው  ጋር  ያመሳስሉታል።  በዚህም  በፒራሚዳዊ  መዋቅር  አባላትን  እየመለመሉ  በሚያቀርቡት  ምርት  ወይም አገልግሎት  አማካኝነት  የመግቢያ  (የመመዝገቢያ)  ክፍያውን  ከምርቱ  ዋጋ  ጋር  ደምረው  (ሰውረው)  ይሰበስባሉ።  
መንግስት ለምን ቀድሞ ማስቆም አይችልም?
በበርካታ ሀገራት ፒራሚዳዊ መዋቅርን ተጠቅሞ ግብይትንም ሆነ ማንኛውንም የንግድ እንቅስቃሴ ማከናወን የተከለከለና በወንጀልም የሚያስጠይቅ እንደሆነ ደንግገዋል። ይሁን እንጂ “ፒራሚዳዊ መዋቅር ነው የምጠቀመው” ብሎ በገሀድ ገልጦ የሚመጣ ድርጅት ባለመኖሩ ድርጊቱ በቅድሚያ ሲፈረጅ አይስተዋልም። በሀገራችን ያለውን የህግ ማዕቀፍ በተመለከተ ግዛቸው ስለሺ የተባሉ ኢትዮጵያዊ አጥኚ “Legal Aspects of Multi-level Marketing (MLM) and Pyramid Schemes” (2019) በሚል ርዕስ ባቀረቡት የጥናት ጽሁፍ ላይ፣ የኢትዮጵያ ህግ የፒራሚዳል አሰራርን የሰረዘ ቢሆንም ለባለ- ብዙ ደረጃ ግብይት/ለአውታረመረብ ግብይት (MLM/Network Marketing) እውቅና የሰጠ ነው ብለዋል። ህጉ “የፒራሚድ  የሽያጭ  እቅድ”ን  (አዋጅ  ቁጥር  813/2013)  ቢሽርም  በአንድ  ንዑስ  ድንጋጌ  ብቻ  የተወሰነ  መሆኑና  ግልጽነትም የጎደለው መሆኑ እንደ ክፍተት የሚታይ ያደርገዋል። በተጨማሪም በህጉ አንቀፅ 22 ላይ (ለንግድ ሰዎች በተለየ) የፒራሚድ እቅዶችን መጠቀም መከልከልን ጨምሮ ብዙ መደረግ የሌለባቸው ተግባራትንም የዘረዘረ ይሁን እንጂ በድርጅቶች ላይ በዝርዝር ያልተገለፀ መሆኑ ሃላፊነቱን ለግለሰቦች ብቻ ነጥሎ የሚጥል ያደርገዋል።
በዚህ የህግ ክፍተት ምክንያት ፒራሚዳዊ መዋቅርን የሚጠቀሙ ድርጅቶች ፒራሚዳዊ ያለመሆናቸውን በድፍረት በመለፈፍ ስለሚጀምሩና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ ተቋማትና በመገናኛ ብዙሃንም ጭምር በስልጠና፣ ወርክሾፕና መግለጫ አማካኝነት ጩኸቱን ቀድመው በመቀማት እንደሚፈልጉት ስለሚቃኙት፤ ፒራሚዳዊነታቸውን በድርቅናና በይሉኝታ ክደው እንደ ስራ ፈጣሪና እንደ ኢንቬስተር እንዲታዩ ይሆናሉ። ስለሆነም በጥልቀት የሚመረምርና በግልጽ ሃላፊነት የተሰጠው ተቋም ባለመኖሩ ምክንያት የጉዳቱ ጥልቀትና ስፋት መጠን ካለፈ በኋላ የህዝብ እሮሮ ሲበረታ ብቻ (በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ውትወታ) በጸጥታ ተቋማት ጣልቃ ገብነትና እርምጃ ደብዛቸው ይጠፋል። ይሁን እንጂ ተከሳሽ ሲሆኑና ሲፈረድባቸው አይታይም። “Multilevel Marketing Diffusion and the Risk of Pyramid Scheme Activity” በተሰኘው በStacie Bosley እና Kim K. McKeage ጥናት፤ የፒራሚድ እቅድ እንቅስቃሴን ለመግታትና ዜጎችን ከመጭበርበር ለመታደግ ውይይት እና ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። በ’ኛም ሀገር የህግ ክፍተቱን ጨምሮ ሌሎችንም ቀዳዳዎች ለመድፈን በትኩረት ሊሰራበት ይገባል።
የፒራሚዳዊ መዋቅሩ የማማለያና የማወናበጃ ስልቶቹ፡
ከላይ ሆነው በሰው ገንዘብ መጫወት የለመዱት ብልጣብልጦች አዳዲስ ፒራሚዳዊ ስርዓቶች ሲመሰርቱ ቀድመው ከላይ ለመቀመጥ የሚጣደፉ ናቸው። እድለቢሱ ተረኛ ከሳሪ ግን በነሱ ስር ተመልምሎ በተስፋ ተሞልቶና ገንዘቡን ተበልቶ በባዶው ይቀራል። (ባለፉት እንዳየነው አረብ አገር ሰርተው ያጠራቀሙትን ጥሪት፣ በሬ ሸጠው ያመጡትን ገንዘብ፣ በዋስትና የተበደሩትን . . . ያጡ ምስኪኖች ነበሩ።) አንዳንዶቹ አዝማሪው እንደሚዘፍንለት ወራጅ ወንዝ የቀደመውን የኪሳራ ታሪክ ያልሰሙ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ግን ድርጊቱን እንደ ቁማር በመቁጠር ወይም ነገሩን በውል ባለመረዳት ደጋግመው ለመታለል የተዳረጉ ናቸው። ለመሆኑ ማታለያና የማወናበጃ ስልቶቻቸው ምን ምን ናቸው?
1. ዘመናዊነት፡- በፒራሚዳዊ መዋቅሩ መታቀፍንና ምርትና አገልግሎቶቹን መጠቀም እንደ ዘመናዊነት በመቁጠር፣ በዚህ የማይሳተፈውን ሰው ይነቅፋሉ። ይህ ጩኸታቸው ሲደጋገም ለራሳቸውም ሆነ ለሌላውም እውነት ይመስላል። ለዚህም ነው ሒሳባዊ መዋቅሩን የሒሳብ ምሁር፣ የግብይቱን ጉዳይ የንግድ ስራ ባለሞያ፣ የጤና ምርቱን ሐኪም፣ የገንዘብ ዝውውሩን ደግሞ የኢኮኖሚ ባለሞያ ሊነግራቸው ቢነሳ እንኳ ፈጽሞ ለመስማትም ዝግጁ የማይሆኑት።
2. ምጡቅ ሰዎች፡- የመዋቅሩን ባለቤት፣ ድርጅቱን እንዲሁም መስራቹን ወይም ቁንጮዎቹን ሰዎች እጅግ እንደ አዋቂና የተለየ አእምሮ ባለቤት የሆኑ አድርጎ እንደ ልዕለ ሰብ በማቅረብ ለማሳመን ይጥራሉ። የድርጅቶቹን የሀብት ብዛት፣ ዓለምአቀፋዊ እውቅና፣ የወደፊት ራዕይ (በሀሰትም ጭምር) አጉልቶ በመሳል አዳዲስ ተመልማዮችን ለማነሁለል ይጥራሉ።
3. ከመቅጽበት ባለጠግነት፡- ወደዚህ መዋቅር ውስጥ ለማስገባት ለሚመለምሉት ሁሉ እንደ ሞኝ ዘፈን (በተደጋጋሚ) የሚጠቀሟት አንዲት ተረት አለች፤ የእንሽላሊቷና የሸረሪቷ። በዚህ ተረት ሸረሪቷ አንዴ ድሩን ሰርታ ቁጭ ብላ ስትበላ እንሽላሊቷ ግን ምግብ ፍለጋ ስትንከራተት እንደምትኖር በማሳየት ቁጭ ብሎ መብላትን ያስጎመጃሉ። ለዚህ አጋዥ እንዲሆናቸው “በወር ስንት ማግኘት ይፈልጋሉ? መኪና ቤት አያስፈልግዎትምን? እርስዎስ ከማን ያንሳሉ? ለምን የመረጡት ሀገር በፈለጉት ጊዜ ሄደው መዝናናትን አያስቡም?” የሚሉ ምድራዊ ቅዥቶች በቁም በማሳለም የተለጠጠ ፍላጎትን አጭረው ከመቅጽበት ባለፀግነትን ያስመኛሉ። እዚህ ምኞት ላይ ዘው ብሎ የገባ ሰው የነሱ ታዳኝ ይሆናል፤ ምክንያቱም ብቸኛው “የከመቅጽበት ባለጸግነት” መንገዱ የነሱው ፒራሚዳዊ መዋቅር ነውና።
4. ዝነኞችና ዝነኝነት፡- የፒራሚዳዊ መዋቅራቸውን ንድፍ ሲያሳዩ እንደየደረጃው የሚሰጡት የማዕረግ ስያሜና የተለያየ ሽልማት አለ። ይሄም ተመልማዩ እንዲጓጓና እሱም ሌሎችን እንዲያጠምድና እንዲተጋ የሚያደርግ ነው። በተጨማሪም በህዝብ ዘንድ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን መርጦ በማምጣት ወይም ለይቶ በመሸለም ማስታወቂያ ይሰራሉ።
5.   ደፋርና ጭስ፡- ከተጋነነው ምኞታዊ ስብከታቸው በተጨማሪ እነርሱም ሁሉን ነገር ትተው እንደመጡ ምስክርነት ይሰጣሉ። ትልቅ ስራና ስልጣን ትተው እንደመጡና አሁን የሚያገኙት፣ እንደበለጠባቸው የወደፊቱም እጅግ የተለየ እንደሚሆን  ይሰብካሉ።  ስብከታቸውን  ሰምቶ  እንኳ  ለመግባት  የሚያቅማማ  ሲኖር፣  “እኔ  እከፍልልሃለሁ”  በማለት በመጀመሪያ ክፍያው ለመማረክና በኋላ በሱ አማካኝነት በሚገኘው ትርፍ ለማካካስ የሚያልሙም አሉ።
6. እድልና ስጋት፡- በዚህ ፒራሚዳዊ መዋቅር የሚያቀርቡትን ምርት ወይም የሚሰጡትን አገልግሎት በተለየ መልክ ስለው ያቀርቡታል። ሌላ ድርጅት እንደማያመርተው፣ በድጋሚ እንደማይመረት፣ በሌላ መንገድም እንደማይሰራጭ ወይም ቶሎ የሚያልቅ አድርጎ በመተረክ ተመልማዩ ከትርፉ በተጨማሪ ለምርቱን እንዲናፍቅ ያደርጋሉ። ለምሳሌ በኩዌስት ኔት ምርቶቹ (ሳንቲምና ሰዓት) ዳግም እንደማይመረቱና ወደፊት እጅግ በውድ ዋጋ ሊሸጡ እንደሚችሉ ሲሰብኩ ነበር። ሌላው ደግም ስጋትና ፍርሃትን በመጫር ነው። ጤናችን አደጋ ላይ እንደሆነ፣ የሰውነታችን ንጥረ ነገር እያለቀ እንደሚሄድ፣ የፀሐይ ብርሃን እንደሚጎዳን፣ ኦዞን እንደሳሳና እንደተቀደደ . . . ከነገሩን በኋላ መፍትሄውም እነርሱ የሚሸጡት መድሃኒት ብቻ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
እንዴት እንጠበቅ?
“እንዴት እንጠበቅ” ወደሚለው ከመምጣታችን በፊት “ለምንስ እንጠመዳለን?” የሚለውን መመልከት ይቀድማል። ማንኛውም እውቀት ጥቅም እንዳለው ሁሉ ፒራሚዳዊ መዋቅርም ጥቅም አለው። ችግሩ ጉዳቱን እያወቁ ለግል ጥቅማቸው ሀብትን ማጋበስን ብቻ ያስደቀሙና የሌሎች ጉዳትና ስቃይ የማይሰማቸው ሰዎች ለማጭበርበሪያነት የሚጠቀሙበት መሆኑ ላይ ነው። “Why are people trapped in Ponzi and pyramid schemes?” በሚለው የTaofik Hidajat ጥናት (Indonesia 2020) እጅግ መጓጓት፣ ስጋቶችን ችላ ማለት፣ በጭፍን በራስ መተማመን፣ በሰዎች መመራት እና የተዛቡ መረጃዎችን እንደ መጠመጃ ምክንያት አስቀምጧቸዋል።
ፕሮፌሰር Barbara R. Rowe “PYRAMID SCHEMES” በተሰኘው የጥናት ወረቀታቸው፣ የሚከተሉትን ስድስት የመጠንቀቂያና መመዘኛ ነጥቦች ጠቁመዋል።
1. ጊዜ መውሰድ፡- እንደዚህ ዓይነት ስልቶች ጠቃሚም ቢሆኑ እንኳ በአንድ ጀንበር የሚጠፉ ስላልሆኑ ተጣድፎ ከመዘፈቅ ይልቅ ጊዜ ወስዶ ማሰላሰልና መወሰኑ የተሻለ ይሆናል።
2. መጠየቅ፡- ማነው ድርጅቱ? ምንድነው የሚያቀርበው? ምን ልምድ አለው? ምን ልዩ ያደርገዋል? ምን ምን ጥናቶች ተሰርተውበታል? የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማቅረብ መልሱን በጥሞና ማጤን ጠቃሚ ነው።
3. መነሻ ገንዘቡ፡- የመነሻ ዋጋው ተመጣጣኝነት የግብይት ስርዓቱን ዓይነት ይወስነዋል። ፒራሚዳዊ ግብይት ከሌሎቹ በተለየ የተጋነነ ዋጋ እና የገዘፈ ተስፋን በመስጠት የሚጀምር ነው።
4. ዋስትና፡- ያልተሸጡ ወይም ሸማች ያልተገኘላቸው ምርቶች የሚመለሱበትና ቅድሚያ ከከፈልነው ቢያንስ 80% ክፍያው ተመላሽ የሚሆንበት የዋስትና ስርዓት የተዘረጋለት መሆኑን ማረጋገጥ።
5. ማማከር፡- ልምድ ያላቸውን እና የሚመለከታቸውን በቅርበት ማማከር።
6. ህጋዊነት፡- ለፒራሚዳዊ ግብይት የሚሰጥ ፈቃድ የለም። እነዚህ ድርጅቶች ግን የንግድ ፈቃድንና የምርት ጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በማሳየት የግብይት ስርዓታቸውን ህጋዊ ያስመስላሉ። ስለሆነም የግብይት ስርዓቱን የተመለከቱ የተረጋገጡና የታተሙ ሰነዶችን መያዝ መቻል ለዋስትናና ፒራሚዳዊ መሆን አለመሆናቸውን ለመለየት ያስችላል።
ከሚመለከታቸው ባለሞያዎችና ከመገናኛ ብዙሃን ምን ይጠበቃል?
ይህ የማጭበርበሪያ ስልት በተለያየ መልክ እየተመላለሰ ብዙዎችን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረገ ነው። በቀጥታ የሚመለከተው አካል አለመኖሩ፣ ቢኖርም እንኳ ትኩረት አለመስጠቱ ወይም ባለድርሻ አካላቱ በቅንጅት አለመስራታቸው ጥፋቱ ከደረሰ በኋላ እንጂ ቀድሞ ሳይደርስ እንዲያስቆሙ አላደረጋቸውም። በመሆኑም ይህን ክፍተት ለመሙላት መገናኛ ብዙሃኑ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር፣ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው በማሳሰብ፣ የተዳፈነውን በማጉላትና ህዝብን ቀድሞ በማንቃት ዜጎች እንዳይጭበረበሩና በራሳቸው መለየት እንዲችሉ ለማድረግ ግንባርቀደሙን ሚና በትጋት ሊከውኑ ይገባል።


Read 1795 times