Saturday, 27 May 2023 16:49

በአዲሱ ሸገር ከተማ ቤት የማፍረሱ ሂደት 100ሺ አቤቱታዎች ቀርበውበታል ተባለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የከተማ አስተዳደሩ መረጃው ያልተጣራና ከአንድ ወገን ብቻ የተገኘ ነው ብሏል

        በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው ዜጎችን በግዳጅ የማስነሳትና ቤቶችን የማፍረስ ሂደት 100ሺ ቅሬታዎች እንደቀረቡበት ተገለፀ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ መረጃው ያልተጣራና ከአንድ ወገን ብቻ የተገኘ ነው ሲል አስተባብሏል፡፡የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ በሸገር ከተማ “ህገወጥ ግንባታ” በሚል እየተካሄደ ካለው የቤት ፈረሳ ጋር በተያያዘ ከአንድ መቶ ሺ በላይ አቤቱታዎች እንደቀረቡለት ገልጿል፡፡
ተቋሙ በተያዘው በጀት አመት ከ133ሺ በላይ አቤቱታዎችን መቀበሉን ገልፆ፤ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ እየተካሄደ ካለው የቤት ፈረሳ ጋር የተያያዙ አቤቱታዎች እንደሆኑም አመልክቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ “ህገወጥ ግንባታ” ናቸው እያለ ለሚያፈርሳቸው የመኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች ምትክ ቦታ እንደማይሰጥና ለተፈናቃዮችም ጊዜያዊ መጠለያ እንዳልተዘጋጀላቸው የገለፀው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ይህ ሁኔታም ተቋሙን እጅግ እንዳሳሰበውና መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክቷል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በከተማው እየፈረሱ ያሉት ቤቶች በህገወጥ መንገድ የተገነቡና የግንባታ ፈቃድ የሌላቸው ቤቶች መሆኑን ጠቁሞ፤ እርምጃው የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጋር የተያያዘ ነው ብሏል፡፡
በህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተገለፀውና 100ሺ ቅሬታዎች ቀረቡበት የተባለው ጉዳይም ከእውነት የራቀ፣ ውይይት ያልተደረገበትና፣በአግባቡ ያልተጣራ እንዲሁም ከአንድ ወገን ብቻ በተገኘ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው ሲል አስተዳደሩ አስተባብሏል፡፡



Read 2079 times