Saturday, 20 May 2023 20:14

አስራት ሀይሌ ( ጎራዴው )

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

አስቸኳይ ድጋፍ ለሕክምናው ይፈልጋል። በቀዶጥገና ለሚያስፈልገው ህክምና ብቻ ከ35 ሺህ ዶላር በላይ መክፈል ይጠበቅበታል። ባለፈው ሰሞን በጎፈንድ ሚ የተሰበሰበለት 14ሺ ዶላር እየደረሰ ነው።  የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከ53 ዓመታት በላይ አገልግሏል
       ድጋፍ ለማድረግ ሁለቱ የባንክ አካውትት ቁጥሮች
          ~በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000544405617
          ~በንብ ባንክ ደግሞ 7000043195037



        የኢትዮጵያን እግር ኳስ በተጨዋችነትና በአሰልጣኝነት ከ53 ዓመታት በላይ ያገለገለው አስራት ኃይሌ አስቸኳይ ህክምና ያስፈልገዋል።
የጥቁር አንበሣ ሆስፒታል የሐኪሞች ቦርድ እንደገለፀው አስራት በግራ ጭንቅላቱ የኋላ ክፍል እጢ ተፈጥሮበታል። እጢው በቀዶ ጥገና እንዲወጣለት ህክምናውን በቱርክ አገር ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማድረግ ይኖርበታል። የህክምና ወጭውን ለመሰብሰብ በስሙ የተቋቋመው ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ስራውን የጀመረ ሲሆን በውጭ አገር ሕክምናውን እንዲያገኝ የጀመረውን ጥረት ክለቦች፣ የቀድሞ ተጨዋቾች፣ ሌሎች የእግር ኳስ ባለድርሻ አካላት እየደገፉ ናቸው።
ኮሚቴው በማሳሰቢያው አስራት ኃይሌ ህክምናውን በአስቸኳይ የማያገኝ ከሆነ ህይወቱ አደጋ ላይ ይወድቃል።
አስፈላጊውን የተሟላ ህክምና ለማግኘት መዘግየቱ በሽታው በግራ ጆሮው ላይ የመሥማት ችግር ያመጣበት ሲሆን በእይታው ላይ ብዥታ በመፍጠር ሁኔታን ሊያባብስ እንደሚችል በፊቱ ላይ አስከፊ ጉዳት እንዳያደርስበት ተሰግቷል። ሙሉ ህክምናውን በሳምንት ውስጥ ማድረግ እንዳለበት የሐኪሞች ቦርድም አሳስበዋል።  ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ “የአውሮፕላን የደረሰ መልስ ቲኬት ወጪ የህክምና ክትትልና ሌሎች ወጪዎችን ሳይጨምር ለኦፕራሲዮኑ ብቻ ከ35 ሺህ ዶላር በላይ ተጠይቋል።
ከሳምንት በፊት ሩት ኃይሌ በተከፈተው በጎፈንድሚ ገፅ የተሰበሰበው እስከ 14000 ዶላር ነው፡፡ በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው የሚመራው ኮሚቴ ከተቋቋመ በኋላ ደግሞ የተለያዩ ድጋፎች እየተሰጡ ናቸው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አብነት ገብረመስቀል 150ሺ ብር እና ለህክምናው የሚጓዙትን ሙሉ የትኬት ወጭ ለመሸፈን ቃል ገብተዋል፡፡
 የአዲስ አበባ መስተዳደር አስራት ሃይሌን ቤቱ ድረስ ሄዶ ከመጠየቅ ባሻገር 50ሺ ብር በእጁ መስጠቱና እንዲሁም 200ሺ ብር በባንክ አካውንቱ እንዳስገባለት ታውቋል፡፡
አስራት ኃይሌ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በክለብና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል።በተጨዋችነት ከ20 ዓመታት በላይ በአሰልጣኝነት ከ33 ዓመታት በላይ በክለብ፤ በተስፋ ቡድኖች እና በዋና ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ሰፊ የስራ ልምድ አለው። በክለብና ብሄራዊ ቡድን ደረጃ በአገርና በአህጉር በርካታ  የዋንጫ ድሎችንም ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአገር ውጭ አሸንፎ ዋንጫውን በማግኘት ፈርቀዳጅ ታሪክ የሰራው አሰልጣኝ አስራት፤ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የተካሄደ ሴካፋን በማሸነፍ ለሁለት ጊዜያት የሴካፋ የዋንጫ ድሎችን የተቀዳጀ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ 3ኛ ደረጃን ያገኘበትን ድል በዞኑ እግር ኳስ አስመዝግቧል።  አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በክለብ ደረጃም ሲያገለግል የተለያዩ ክለቦችን አሰልጣኝነት በፕሪሚዬር ሊጉ ከፍተኛ ውጤታማነት እና ልምድ ካላቸው አሰልጣኞችም ዋናው ተጠቃሽ ይሆናል። በተለይ ለሰባት የውድድር ዘመናት በቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝነት ሲያገለግል  6 የፕሪሚዬር ሊግ የሻምፒዮናነት ክብሮችን አግኝቷል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር  ሊግ ከሰባት ጊዜ  በላይ የኮከብ አሰልጣኝነት ሽልማቶችን በመሰብሰብም የተሳካለት ነው፡፡
አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በፕሪሚዬር ሊግ እጅግ ስኬታማ የሆነበትን የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከለቀቀ በኋላ መከላከያ፤ መብራት ኃይልና የመድን ሌሎቹ ያሰለጠናቸው ክለቦች  ናቸው፡፡ ከመከላከያ ክለብ ጋር  የጥሎ ማለፍዋንጫን፤  ከመብራት ኃይል ክለብ ጋር የሲቲ ካፕ ዋንጫን እንዲሁም በክለብ ደረጃ የነበረው የመጨረሻ ቆይታው ባለፈው የውድድር ዘመን የመድን ክለብ አሰልጣኝ ሆኖ ከመስራቱ በፊት ክለቡን የብሄራዊ ሊግ ሻምፒዮን አድርጎ ወደ ሊግ ውድድር ለመመለስ የበቃ ነው።



Read 804 times