Saturday, 20 May 2023 15:24

የበኬ ከተማ ሃብትና ጌጥ የሆነው ዘመናዊ ሆቴል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “ሆቴሉን እንድሰራ ያደረገኝ የህዝቡ ፍቅር ነው”


         ከአዲስ አበባ በስተሰሜን በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሰንዳፋ በኬ ከተማ፣ ድንገት የበቀለ የሚመስል ባለ ግርማ ሞገስ  ዘመናዊ ሆቴል ተንጣሎ  ይታያል፡፡
በእርግጥ ለከተማዋ ነዋሪና በአካባቢው ለሚመላለስ  ሰው ድንገት የበቀለ  አይደለም፡፡ ከ5 ዓመት በላይ ጊዜና 450 ሚሊዮን ብር ገደማ የፈጀ ኢንቨስትመንት ነው፡፡
የበኬ ከተማ ሃብትና ጌጥ እንደሆነ የተነገረለት “ቱ አር ኤን ሰለሞን ሆቴልና ስፓ”፤ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም፣ ከግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት እንደሚመረቅ የሆቴሉ አስተዳደር አስታውቋል፡፡  
በቀድሞው የደርግ መንግሥት  አገራቸውን በወታደርነት ባገለገሉት መቶ አለቃ ሰለሞን አዳሙ የተገነባው ይኸው ባለ  5 ኮከብ ሆቴል፣ ባለፈው ሰኞ ግንቦት 7፣ በሚዲያ ቡድን አባላት ተጎብኝቷል፡፡
 በጎጃም ጠቅላይ ግዛት፣ ይልማና ዴንሳ በሚባለው አካባቢ የተወለዱት ሰለሞን አዳሙ፤ ገና በ5 ዓመት  ዕድሜያቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው፣ አውቶብስ ተራ አካባቢ ነው ያደጉት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በ1973 ዓ.ም፣ በ21ኛ ተራራ ክፍለ ጦር ውስጥ ተቀጥረው፣ በተራ ወታደርነት፣ ለ4 ዓመታት በኤርትራ ውስጥ  ማገልገላቸውን ይገልጻሉ፤ በብዙ ውጊያዎች ላይ መሳተፋቸውንና በተዋጊ መሃንዲስነት መሥራታቸውንም በማከል፡፡  
“በ1977 ዓ.ም ባገኘሁት  ዕድል የ48ኛ የእጩ መኮንኖች   ኮርስ ተወዳድሬ በጥሩ ተማሪነት ተመርቄ እዚያው ተሹሜአለሁ፤ የቶፖግራፊ አስተማሪም ነበርኩ፡፡” ይላሉ፡፡
በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረ ጊዜ ጦላይ ተሃድሶ መግባታቸውን የሚናገሩት መቶ አለቃ ሰለሞን አዳሙ፤ከዚያ ከወጡ በኋላ ወደ ሥራ የመመለስ ዕድል ቢያገኙም፣ ከእንግዲህ ወዲያ ወታደር አልሆንም ብለው ወደ ሲቪሉ ማህበረሰብ መቀላቀላቸውንና ወደ ንግድ ሥራ መግባታቸውን  ይገልጻሉ፡፡
የንግድ መነሻ  የሆናቸውን  3ሺ ብር ያገኙት ግን ከድለላ ሥራ መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ ብዙ ነገሮችን ነግጄአለሁ የሚሉት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የሲጋራ ጅምላ ፈቃድ እንደነበራቸው፣ እህል መነገዳቸውን፣ መርካቶ ዱባይ ተራ የልብስ ሱቅ እንደነበራቸውና  ጣውላ መነገዳቸውን  ይናገራሉ፡፡ በመጨረሻም አሁን  በከተማችን  የሚታወቀውንና ከ200 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የከፈተውን  “ቱ አር ኤን ሰለሞን ፈርኒቸር” አቋቁመዋል፡፡
ይሄ ድርጅት አድጎና ጎልብቶ ባፈራው ሃብት ነው የሰንዳፋው  ዘመናዊ ሆቴል የተገነባው የሚሉት  ባለሃብቱ፤ በዚህ ትልቅ ኢንቨስትመንት ላይ  አዋሽ ባንክና ዳሽን ባንክ ብድር በመስጠት አሻራቸውን አሳርፈዋል ብለዋል፡፡   
በ2ሺ ካ.ሜ ቦታ ላይ በግርማ ሞገስ የተሰደረው  ውብ  ሆቴል፣ ደረጃቸውን የጠበቁና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው 40 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ነው፡፡ ከሬስቶራንት ባርና ካፌ በተጨማሪም፣ የሳውና ስቲም ባዝና ማሳጅ  አገልግሎቶችንም አካትቶ ይዟል፡፡
በሆቴሉ ግንባታ አብዛኛው ግብአት ከውጭ የመጣ ሳይሆን የአገር ውስጥ መሆኑን የሚናገሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የሆቴል የእንጨት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ የተከናወኑት በ”ቱ አር ኤን ሰለሞን ፈርኒቸር” መሆኑን ገልጸዋል፡፡  
“ይህን ሆቴል ለመሥራት ቦታ የወሰድነው  በ2009 ዓ.ም ነው፤በዚያን ወቅት በኦሮሚያና በሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ የነበረውን የጸጥታ  ሁኔታ ሁሉም የሚያውቀው ነው” ያሉት ባለሃብቱ፤ “በብዙ መስዋዕትነት ነው እዚህ የደረስነው፡፡” ብለዋል፡፡
“የሰንዳፋ በኬ አካባቢ ህዝብ በጣም ጨዋና ትልቅ  በመሆኑ እኛንም እንድንሰራ፣ እንዳንሸሽ አድርጎ፣ ይህንን ሆቴል የራሱ ሃብት አድርጓል፡፡” ሲሉም አስረድተዋል፤መቶ አለቃ ሰለሞን፡፡
ህዝቡ ሆቴሉን  እንደራሱ ንብረት እንደሚቆጥረውና እንደሚጠብቀው  ባለሃብቱ ሲገልጹም፤ “የእኛ ካሜራ የአካባቢው ህዝብ ነው፤ኮሽ ባለ ቁጥር ህዝቡ ነው ሆቴሉን ወጥቶ  የሚጠብቀው፡፡ ይህን ሆቴል ያሰራኝ የአካባቢው ህዝብ ፍቅር ነው፡፡” ብለዋል፡፡
በረብሻና ግርግር  ወቅት የነበረውን ሁኔታ አስታውሰውም፤ “ከበኬ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ሁሌም የአካባቢው ነጋዴዎች  በመኪና አጅበው  ይሸኙኝ ነበር፤ቤቴ በደህና መግባቴንም ስልክ ደውለው ያረጋግጡ ነበር፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህንን እውነታ በዕለቱ  ለጋዜጠኞች አጭር  መግለጫ  የሰጡት  የከተማዋ ከንቲባ አቶ አለማየሁ ተንኮሉም በድጋሚ  አረጋግጠውታል፡፡  የበኬ ህዝብ እንደሌላው የኦሮሚያ አካባቢዎች ህዝብ ሁሉ ሰላም ወዳድና አቃፊ ነው  ያሉት  ከንቲባው፤ ህብረተሰቡ የአቶ ሰለሞንን  ሆቴል እንደራሱ ንብረት እንደሚያየውና እንደሚሳሳለት መሥክረዋል፡፡  
በኬ ከተማ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚከናወንባት ሥፍራ መሆኗንና፣ ሃቀኛ አልሚዎችን ብዙ ርቀት ተጉዘው እንደሚያስተናግዱ የገለጹት ከንቲባ አለማየሁ ተንኮሉ፤ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡



Read 1865 times