Monday, 15 May 2023 20:47

ለሰንዳፋዋ በኬ ከተማ ሃብትም ጌጥም የሆነው ድንቅ ሆቴል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ባለሃብቱ፤ ሆቴሉን እንድሰራ ያደረገኝ የህዝቡ ፍቅር ነው ብለዋል

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሰንዳፋ በኬ ከተማ ድንገት የበቀለ የሚመስል ባለ ግርማ ሞገስ ድንቅ ሆቴል ቆሞ ይታያል፡፡ በእርግጥ ለከተማዋ ነዋሪና አካባቢውን ለሚያውቅ ሰው ድንገት የበቀለ አይደለም፡፡ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከ5 ዓመት በላይ ጊዜና 450 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡

የበኬ ከተማ ሃብትና ጌጥ እንደሆነ የተነገረለት ይኸው "ቱ አር ኤን ሰለሞን ሆቴልና ስፓ"፣ ከግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት እንደሚመረቅ ነው የተገለጸው፡፡

በቀድሞው የደርግ መንግሥት ጦር ሠራዊት ውስጥ አገራቸውን በወታደርነት ባገለገሉት መቶ አለቃ ሰለሞን አዳሙ የተገነባው ይህ ባለ  5 ኮከብ ሆቴል፣ ዛሬ ረፋድ ላይ በሚዲያ ቡድን አባላት የተጎበኘ ሲሆን ጋዜጣዊ መግለጫም ተሰጥቷል፡፡

በ1982 ዓ.ም የደርግ መውደቅን ተከትሎ፣ የድለላ ሥራ መጀመራቸውን  የሚናገሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ በኋላም በ3ሺ ብር ካፒታል ወደ ንግድ ሥራ መግባታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ባለሃብቱ በከተማችን  የሚታወቀው የቱ አር ኤን ሰለሞን ፈርኒቸር  ባለቤት ሲሆኑ፤የሆቴሉ ህንጻ የእንጨት ሥራዎች በሙሉ የተከናወኑት በዚሁ ድርጅታቸው ነው ተብሏል፡፡

በሰንዳፋ በኬ ከተማ በ2ሺ ካ.ሜ ቦታ ላይ በግርማ ሞገስ የተንጣለለው ሆቴሉ፤ደረጃቸውን የጠበቁና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው 40 የመኝታ ክፍሎች አሉት፡፡ ከሬስቶራንት ባርና ካፌ በተጨማሪም የጃኩዚና ስፓ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡

በተለይ የአካባቢው ቀዝቃዛ አየርና ያማረ ተፈጥሯዊ ዕይታ  ሆቴሉን ተመራጭና ተወዳጅ እንደሚያደርገውም ተነግሯል፡፡

ሆቴሉ ያረፈበትን ቦታ በ2009 ዓ.ም መውሰዳቸውን የተናገሩት መቶ አለቃ ሰለሞን፤ የሊዝ ክፍያውን የፈጸሙት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን  መልቀቃቸውን ያስታወቁ ዕለት መሆኑን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ጎጃም ውስጥ የተወለዱት ባለሃብቱ፣ የጸጥታና ደህንነቱ ሁኔታ እጅግ አስጊ በነበረበት ወቅት መዋዕለንዋያቸውን እንዴት በኦሮሚያ ክልል በምትገኘው የሰንዳፋዋ ቤኪ ከተማ ለማፍሰስ እንደደፈሩ ተጠይቀው ነበር፡፡ መቶ አለቃ ሰለሞን ሲመልሱም፤ "የእኛ ካሜራ የአካባቢው ህዝብ ነው፤ኮሽ ባለ ቁጥር ህዝቡ ነው ሆቴሉን ወጥቶ ከአደጋ የሚጠብቀው፡፡ የአካባቢው ህዝብ ፍቅር ነው ይህን ሆቴል ያሰራኝ፡፡" ብለዋል፡፡

ባለሃብቱ አክለውም፤ "ረብሻና ግርግር በነበረበት ወቅት ወደ አዲስ አበባ ስመለስ የአካባቢው ነጋዴዎች  በመኪና አጅበው ለገጣፎ ድረስ ይሸኙኝ ነበር፡፡" ሲሉ የህዝቡን ፍቅር ገልጸዋል፡፡

ይህንን እውነታ ለጋዜጠኞች መግለጫና ማብራሪያ የሰጡት  የከተማዋ ከንቲባ አቶ አለማየሁ ተንኮሉም አረጋግጠውታል፡፡  በኬ የሁሉም ብሔር ተወላጆች በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ ናት የሚሉት ከንቲባው፤ ህብረተሰቡ መቶ አለቃ ሰለሞን የገነቡትን ሆቴል እንደራሱ ንብረት እንደሚያየውና እንደሚሳሳለት ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ያሉትን ሃብቶች ለጋዜጠኞች በዝርዝር የጠቀሱት ከንቲባ አለማየሁ፤አሁን ደግሞ ሌላ ሃብት ጨምረናል ብለዋል - ባለ 5 ኮከቡን አስደማሚ  ሆቴል ማለታቸው ነው፡፡ ሃቀኛ አልሚዎችን ብዙ ርቀት ተጉዘው እንደሚያስተናግዱ በመግለጽም፤ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡



Read 2424 times