Saturday, 13 May 2023 20:48

ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  “የ16 ዓመቷ ልጅ ሞት እስካሁን ይጸጽተኛል…”             
የጽንስ እና የማህጸን ህክምና ስፔሻሊስት
ዶ/ር አየለ ደበበ
በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለምማቀፍ ደረጃ ከ10 እርግዝናዎች መካከል 6 ጽንስ ይቋረጣል። 45በመቶ የሚሆነው ጽንስ የማቋረጥ ሂደት የሚከናወነው ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ነው። በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ይህን ድርጊት በመፈጸም 97በመቶ ይይዛሉ። ለእናቶች ሞት መንስኤ ከሆኑ 5 ምክንያቶች ውስጥ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ይመደባል።
የዶሻ ኤም ሲ ኤስ ሴንተር ባለቤት የሆኑት የጽንስ እና የማህጸን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር አየለ ደበበ ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ጽንስ ከማቋረጥ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልምድ አካፍለውናል። ዶ/ር አየለ ደበበ የትውልድ ቦታቸው በሆነው አምቦ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። በአምቦ ሆስፒታል ጠቅላላ ሀኪም ሆነው እንዲሁም ስፔሻሊስ ከሆኑም በኋላ በድምሩ ለ10 ዓመታት አገልግለዋል። በበሆስፒታሉ ወቅቱ የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የነበሩት እሳቸው ብቻ ነበሩ። እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር በወቅቱ የህክምና ተቋማት(ሆስፒታሎች) በብዛት አልነበሩም። የአምቦ ሆስፒታል ለአምቦ እና ለአከባቢው(ምዕራብ ሸዋ) የሚያገለግል ብቸኛው ተቋም ነበር። “በጣም ከባድ ነበር፤ እንዳሁን ጤናጣቢያ በየወረዳው ባለመኖሩ ታካሚዎች ለህክምና የሚመጡበት ጉዳይ በጣም ከባድ (የመጨረሻ ደረጃ ሲሆን) ነበር” በማለት የነበረውን ችግር ተናግረዋል። ዶ/ር አየለ በሆስፒታሉ በማገልገል ላይ ባሉበት ወቅት እስከአሁን ከአይምሯቸው የማይጠፋ አንድ ክስተት ተፈጠረ። አንዲት ሴት ከገጠራማ አከባቢ ለትምህርት ስትል ወደ አምቦ ከተማ ታመራለች። የሄደችውም አጎቷ ቤት ነበር። በዚህ መሀል በዙሪያዋ ካሉ ሰዎች(ዘመድ) ከአንዱ እርግዝና ተፈጠረ። ልጅቷም ከዘመድ የተፈጠረ እርግዝና በመሆኑ እና ወላጆቿም ይህን ጉዳይ የሚቀበሉት ባለመሆኑ ፅንሱን ለማቋረጥ ወሰነች። ጽንሱን ለማቋረጥ የሄደችውም ዶ/ር አየለ ይሰሩበት ወደነበረው አምቦ ሆስፒታል ነበር። በእለቱ ዶ/ር አየለ ተረኛ ስለነበሩ ከባለታሪኳ ጋር ተገናኙ። ዶ/ር አየለ እንደተናገሩት ከ25 ዓመታት በፊት በነበረው የኢትዮጵያ ህግ መሰረት ፅንስ ማቋረጥ በምንም ምክንያት አይፈቀድም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ ነው ተብሎ በህክምና የትምህርት ተቋማት የሚመከር ጉዳይ እንዳልነበር ባለሙያው ተናግረዋል። ስለሆነም አገልግሎቱን ማግኘት እንደማትችል ለተጎጂዋ መንገራቸወን የህክምና ባለሙያው ያስታውሳሉ። አክለውም “ህገወጥ ነው፤ ሁለታችንንም ለእስር ይዳርገናል” በማለት ለታካሚዋ የነግሯታል። እሷ ግን ንግግራቸውን ለመቀበል ፍቃደኛ አልነበረችም። እነርሱ አገልግሎቱን የማይሰጧት ከሆነ በእራሷ መንገድ ፅንሱን እንደምታቋርጥ እና እራሷንም እንደምታጠፋ ተናገረች። ምንም እንኳን ዶ/ር አየለ እና ሌሎችም የህክምና ባለሙያዎች ለማግባባት እና ከመንገዷ ለማስቆም ቢሞክሩም ታካሚዋ በሃሳባቸው ሳትስማማ በሀሳቧ ጸንታ ሄደች። ባለታሪኳ በተመሳሳይ ቀን ወደ አመሻሽ ላይ ተመልሳ ወደ ሆስፒታል አመራች። አመሻሽ ላይ ስትሄድ ግን እራሷን ስታ ነበር። መርዝ ጠጥታ እራሷን ለማጥፋት መሞከሯን ነው የህክምና ባለሙያው የተናገሩት። የደረሰባት ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር ህይወቷን ማትረፍ አልተቻለም። “ጠዋት በሰላም ያየኋት የ16 ዓመት ልጅ፤ በትምህርት ተስፋ የነበራት፤ ህይወቷን ማዳን ስንችል መሞቷ ሁልጊዜም ይፀፅተኛል፤ እስካሁን ይፀፅተኛል።” ብለዋል የህክምና ባለሙያው።
50 በመቶ የእናቶች ሞት መንስኤ በመሆን ለዘመናት የቆየው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ መሆኑን የህክምና ባለሙያው የጠቀሱ ሲሆን ከሞት በተረፉት ላይ ደግሞ ማህፀን ሙሉበሙሉ እስከመውጣት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግረዋል። ዶ/ር አየለ “ለ16 ዓመት ልጅ ከዚህ በኋላ ማህፀን የለሽም፣ የወርአበባ አታይም፣ ልጅ መውለድ አትችይም” ብሎ መንገር ምን ያህል ከባድ እንሆነ በመገንዘብ የችግሩን ሁኔታ መረዳት ይቻላል ብለዋል። እርግዝና ሲፈጠር የጽንሱ እናት እና አባት በጋራ ሳይሆን እናት ብቻ ተጠያቂ እንዲሁም የችግሩ ተጋፋጭ የሚደረጉት ትደረጋለች። “ብዙ ወንዶች ሀላፊነት ከመውሰድ ይልቅ መሸሽን ይመርጣሉ” ብለዋል ዶ/ር አየለ ደበበ። ስለሆነም ሴቷ ችግሩን ለብቻዋ ለመጋፈጥ ትገደዳለች። በብዛት ጽንስ የሚያቋርጡ ሴቶች እርግዝና የተፈጠረው ያለፍላጎታቸው መሆኑንም ባለሙያው ተናግረዋል። ታያ በተባለ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የስነተዋልዶ ጤና እና መብት ፕሮግራም ማኔጀር የሆኑት ጠቅላላ ሀኪም ልዕልና ሽመልስ በተመሳሳይ መልኩ በሴቷ ላይ ሀላፊነት የመጣል እና ጥፋተኛ የማድረግ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል። የህክምና ባለሙያዋ እንደተናገሩት በመጀመሪያ እርግዝናው ሲፈጠር የሚከሰት ጭንቀት ይኖራል። ከዛም ጭንቀቱን አልፈው ለመወሰን እና ወደ ጤና ተቋም ለመሄድ ብዙ ውጣ ውረድ ያሳልፋሉ። “ሰው አየኝ አላየኝ እንዲሁም ጤና ተቋማት ላይ ያሉ ሰዎችም ያውቁኝ ይሆን በሚል ስጋት ነው ወደ የህክምና ተቋማት የሚሄዱት” ብለዋል የህክምና ባለሙያዋ። ባለሙያዋ እክለው ይህ አገልግሎት በመንግስት የህክምና ተቋማት በቀላሉ የሚገኝ አለመሆኑን ተናግረዋል። ስለሆነም በግል ተቋማት ይህን አገልግሎት ለማግኘት ገንዘብ ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ ይሆናል። ወደ ህክምና ተቋማት ከሄዱ በኋላ ደግሞ የሚያዩት ፊት ከባድ ነው። በተለይ አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሴቶች ላይ ይበልጥ መገለሉ ከፍ ያለ ነው ብለዋል የህክምና ባለሙያዋ። “እንዴት በዚህ ሁኔታሽ ልጅ ታረግዢያለሽ” የሚል ንግግር እንደሚሰነዘርባቸው ባለሙያዋ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ፅንስ የማቁረጥ አገልግሎቱ ከተሰጠ በኋላም መገለሉ ይበልጥ እንደሚጨምር ተናግረዋል። ባለሙያዋ እንደተናገሩት ፅንስ የማቋረጥ ሂደት በእራሱ ህመም ያለው ነው። አገልግሎቱን ካገኙ በኋላ ሰውነትን መንከባከብ ያስፈልጋል። “በብዛት ፅንስ የሚያቋርጡ ሴቶች በድብቅ ስለሆነ አገልግሎቱን የሚያገኙት እራሳቸውን ለመንከባከብ እድል አያገኙም። እንዲሁም ተፅዕኖው በጣም ከባድ ስለሆነ የሚደግፍ አካል አይኖራቸውም” ብለዋል የህክምና ባለሙያዋ። “በተለያዩ መድረክ የምናገኛቸው ወጣቶች ይህንን አገልግሎት ለማግኘት ሲፈልጉ ነገሮች ቀላል እንዳልሆኑ ይናገራሉ” በማለት የህክምና ባለሙያዋ የተናገሩ ሲሆን እንደ ሀጢያት እና ጥፋት ስለሚታይ የሴቷን ሁኔታ የሚረዳት የለም ብለዋል። እንደ ዶ/ር ልዕልና ሽመልስ ንግግር ሴቷ ለምን ይሄን አደረገች የሚለውን ብዙ ጊዜ ወደኋላ ሄዶ የሚመረምር አካል አይገኝም።
ሙሉበሙሉ የሴቷ ጥፋት ተደርጎ ነው የሚወሰደው። አስገድዶ መደፈር የደረሰባት ሴትም ብትሆን ከአለባበሷ ወይም ከነበረችበት ቦታ ጋር በማያያዝ እሷን ጥፋተኛ የማድረግ እንጂ ጥቃት የፈፀመው ላይ ትኩረት እንደማይደረግ ባለሙያዋ ተናግረዋል። አክለውም በህጉ መሰረት አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ሴቶች አገልግሎቱን ለማግኘት መቸገራቸውን ተናግረዋል።በ1998ዓ.ም በተሻሻለው የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቁረጥ አገልግሎት የሚሰጠው በ4 ምክንያቶች አማካኝነት ነው።
በመደፈር ወይንም በዘመድ መካከል በተደረገ የግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ጽንሱ የተገኘ ከሆነ
የእርግዝናው መቀጠል በእናቲቱም ሆነ በጽንሱ ህይወት ወይንም በእናቲቱ ጤንነት ላይ አደጋ የሚያመጣ ሲሆን
ጽንሱ ሊደን የማይችል ከባድ የአካል ጉድለት ያለው [ዲፎርምድ] ሲሆን ወይም
አንዲት እርጉዝ ሴት የአካል ወይንም የአእምሮ ጉድለት ያለባት መሆንዋ ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሰች በመሆንዋ የሚወለደውን ህጻን ለማሳደግ የህሊናም ሆነ የአካል ዝግጅት የሌላት ሲሆን ነው።
ዶ/ር ልእልና ተሾመ “ወጣቶች ሀገራችን በምትፈቅደው መሰረት ይሄንን አገልግሎት እንዲጠቀሙ መክራለሁ” በማለት የተናገሩ ሲሆን በተቻለ መጠን እራሳቸውን እንዲጠብቁም አሳስበዋል። በአፍላ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በመጀመሪያ አላማቸውን እንዲያስቡ እና የግብረ ስጋ ግንኙነት ቶሎ እንዳይጀምሩ በማለትም ተናግረዋል። እንዲሁም የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እንዲጠቀሙ ምክራቸውን ለግሰዋል።
 ነገር ግን አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ [ህጉ ላይ እንደተቀመጠው] ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አገልግሎቱን የማግኘት መብት እንዳላቸው ጠቁመዋል። በተጨማሪም በተለይ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች አገልግሎቱን ለሚያገኙ ሴቶች ተገቢውን እገዛ እንዲሰጧቸው በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።
 የህክምና ባለሙያዋ የአንድ ሀገር እድገት እና ውድቀት የሚለካው በእናቶች ሞት ቁጥር መሆኑን አስታውሰው ከ20 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ባደረገችው የህግ ለውጥ መሰረት ደህንነቱ ባልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ቁጥር መቀነሱን ተናግረዋል። በመጨረሻም የህክምና ባለሙያዋ “ወደኃላ መመለስ የለብንም። እያንዳንዷን ሴት ለመደገፍ እሷን ለማብቃት ሀላፊነት አለብን። ይህን ካለደረግን በሚቀጥለው ትውልድ የታሪክ ተጠያቂ ነው ምንሆነው” ብለዋል።



Read 542 times