Saturday, 13 May 2023 20:40

የሚዳቋ ጅራት እርቃኗንም አይሸፍን አምላክንም አያስመሰግን

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከእለታት አንድ ቀን አንድ መጠጥ ቤት የነበረው ባላባት ነበረ። ይህ ሰው በጣም ስስታምና እምነተ-ቢስ ሰው ነበር።  በህልሙም በእውኑም  አግባብነት  የሌለው ትርፍ ከማግበስበስና ሀብታም ከመሆን በስተቀር የሚያስበው ነገር የለም። ሆኖም ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግ በየዕለቱ እየደኸየ ነበር የመጣው። አንድ ቀን አንድ አጎቱ ሊጠይቁት መጡ። ለረዥም ጊዜ አልተገናኙም ነበር።
“ሥራ እንዴት ነው?” አሉ አጎቱ።
“ኧረ እንደው ምኑም አልሳካልህ ብሎኛል። በየቀኑ መደህየት ሆኗል የኔ ነገር። የቢራው በርሜል ውስጥ ውሃ ጨምሬ አቅጥኜ ልሸጠው ሞከርኩ።  ወይኑንም በውሃ አቅጥኜ አብዝቼ  ለመሸጥ ሞከርኩ፤ የመጨረሻ እርካሽ የሚባለውን ስጋና ቅጠላ ቅጠል ገዝቼ በውድ ለመሸጥም ሞክሬያለሁ። በተቻለኝ መጠንም ሂሳብ ስመልስ የተሳሳተ መልስ እየሰጠሁ ላጭበረብርም ሞከርኩ። ብዙ ብር አገኝ መስሎኝ ያልፈነቀልኩት ድንጋይ፣ ያልበጠስኩት ቅጠል አልነበረም። ያም ሆኖ አሁንም ከመደህየት አላመለጥኩም። ምን ችግር ውስጥ እንደገባሁና ምን አይነት የኮከብ ጠማማ እንዳለኝ አይገባኝም።”
“እኔ ግን አንተን ሀብታም የሚያደርግህ አንድ ዘዴ አውቃለሁ” አሉ አጎትየው። “ና ላሳይህ” አሉና ቢራውም፣ ወይኑም፣ ምግቡም ወደሚከማችበት ወደ ዋናው መጋዘን ይዘውት ሄዱ። ከዚያም በሩን በትንሹ ከፈት አድርገው “በል በቀዳዳው አሾልከህ እይ” አሉት።ባለመጠጥ ቤቱ ግን ምንም ነገር ከተለመደው ውጪ ሊታየው አልቻለም። “ኧረ ምንም አይታየኝም” አለ።
“እስቲ እግርህን በእግሬ ላይ አድርግ።  እጅህን ደግሞ እኔ ራስ ላይ አድርግና ለማየት ሞክር።” አጎቱ እንዳሉት አደረገ። ከዚያ እንደገና ወደ መጋዘኑ ተመለከተ። አይኑ ማመን አቃተው። ከመጋዘኑ መካከል ከወለሉ ላይ አንድ ወፍራም አጭር ቁዝር ሰውዬ ተቀምጧል። ምግቡን አሁንም አሁንም ይጠቀጥቃል። ኬክ በቅቤ፣ በጨው፣ በዱቄት ያሻምዳል። ከዚያም አሳማና  እንቁላል ይጎርሳል። ደሞ በዚያ ላይ ቢራ ይጨምርበታል። ደሞ ይጎሰጉስበታል።
“ማን ነው? ምንድን ነው ይሄ?” ሲል ጠየቀ ባለግሮሰሪው።
“ይሄ የቅቤ አምላክ ይባላል።” አሉ አጎትየው። “እነዚህ አማልክት ስስት ባለበትና እምነተ-ቢስነት በነገሰበት መጠጥ ቤት ሁሉ ይኖራሉ። ማጭበርበርና ዳተኝነት ባለበት ቦታ ሁሉ ይመጣሉ።”
“ግን እንደዛ ካለ ባህሪዬ እንዴት አድርጌ ማምለጥ እችላለሁ?”
“ማምለጥማ አትችልም። ደንበኞችህን ባታለልክ ቁጥር የቅቤ አምላክ አንተን ያታልልሃል። እርግጥ ነው ይህን አመልህን ትተህ ለደንበኞችህ ቀና አገልግሎት መስጠት ስትጀምር የቅቤ አምላክም ጥሎህ ይጠፋል። ግን ለደንበኞችህ በጣም ምርጥ ምግብ አቅርበህ ተመጣጣኝ ክፍያ መጠየቅ ይኖርብሃል። ይሄን መናኛ ምግብና የቀጣጠነ መጠጥ እያቀረብክ እንደምታደርገው ያለ ተግባር አማልክቱ እንዲሸሹ አያደርጋቸውም።”
ይህንን ብለው አጎትየው ትተውት ሊሄዱ ተነሱ። በቅርቡ ተመልሰው እንደሚጠይቁት ቃል ገቡለት። ከዚህ በኋላ አጎት አልተመለሱም። ባለ ግሮሰሪው ግን ሆቴሉን ማሻሻሉን ቀጠለ። ባሻሻለውም ቁጥር ትርፉ እየጨመረ መጣ። ሃብታም ሆነ፡፡ መጠጥ ቤቱ ጢም ብሎ ይሞላ ጀመር። የዚህን መጠጥ ቤት ምግብ ለመቅመስ ከሩቅም ከቅርብም በላተኛው ይፈላ ጀመር። ቢራው ይደነቅ ጀመር። ወይኑም ስሙ የተጠራ ሆነ።
ከዓመት በኋላ አጎትየው መጡ። ሁኔታው ሁሉ መለወጡንም አዩ። “እስቲ አሁን ወደ መጋዘንህ እንሂድ” አሉት።
እንደቀደመው ጊዜ አሾልከው ተመለከቱ። አሁን ከወለሉ ላይ የተቀመጠው አንድ ቀጫጫ፣ ደካማ፣ በሽተኛ መልክ  ያለው የቅቤ አምላክ ነው። ምግብ ለመብላት እየፈለገ ቅንጣት ታህል ጉርሻ ወደ አፉ ለማድረስ አቅም ያጣ ነው።
“አየህ” አሉ አጎት፣ “ታማኝነትና ጠንካራ ሰራተኝነት ባለበት ቦታ ሁሉ ዝር አይሉም። ይሄ መንፈስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሟች ነው። አንተ ወደ ጥንቱ የማታለል ተግባር እስካልተመለስክ ድረስ ወደዚህ ዝር አይልም።”
ባለግሮሰሪውም፡-
“ታማኝነትና ጠንካራ ሰራተኝነት የማታ የማታ ትርፋማ እንደሚያደርጉ ተገንዝቤያለሁ”” አለ።
***
በታማኝነትና በሠራተኝነት ላይ የሚያምን ግለሰብ፤ ኃላፊ፣ ባለስልጣን፣ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት ማግኘት መታደል ነው። ትርፍ ከየትም ይምጣ ከየት መገኘት አለበት የሚል እምነት ደግ አይደለም። ውሎ አድሮ ከሰው ዘርፎም፣ ሰውን ገድሎ ቀምቶም ያገኙትን ትርፍ ትክክለኛ ሀብቴ ነው ማለትን ያስከትላል። የፖለቲካ የበላይነት ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተሄዱ ብዙ እኩይ ጉዳዮች ነበሩ። አሉም። ቢራው ላይ ወይም ወይን ጠጁ ላይ ውሃ እየጨመረ ሊያተርፍ እንደሞከረው ባለግሮሰሪ ብዙ ዓይነት የማማለያ መንገዶችን በመጠቀም ህዝቡን ለማጭበርበር የሞከሩ ብዙዎች ናቸው። ቋቱ ግን አልሞላም። የቅቤ አምላክ ውስጥ ውስጡን እየቦጠቦጠና እየሸረሸረ በአድልዎና በግፍ የተደበቀውን ሀብት ሁሉ ኦና እንዲቀር ያደርገዋል። ምልኪው ከባድ ነው፣ ሌሎችን በመበደል፣ ከሌሎች በመዝረፍ የሚካበት ሀብት መቅኖ የለውም። የኋላ ኋላ ወዳጅንም አርቆ፣ ሀብትንም አራቁቶ የራስን ህልውና ጭምር ወደማጣት ያመራል።
በሀገራችን የሚታየው የፖለቲካ ሙስናና የኢኮኖሚ ሙስና ተሳሳሪነትም፣ ተባባሪነትም ያላቸው ናቸው። በተለይ የፖለቲካ ስልጣንን ተገን አድርጎ የግል ወይም የድርጅት ኢኮኖሚያዊ ቋትን መሙላት የተለመደ ጉዳይ ነው። የማታ ማታ በገዛ ድርጅትም ሆነ በሌላ ባለጊዜ ወደ ዘብጥያ መውረድ እጅግ የታወቀ፣ እንደ ጸሐይ መግባት መውጣት የተረጋገጠ ሀቅ በመሆን ላይ ነው። አንድ የሀገራችን ፀሐፌ ተውኔት በአንደኛው ቴያትሩ ውስጥ ወህኒ ቤትን የገለጸው በንጉሥ አንደበት ነው። ንጉሡ  ወህኒ ቤቱን ሲመርቁ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ይላሉ፡-
“የአባታችን ርስተ-ጉልት የሆነውን የሀገር ወህኒ ቤት መርቀን ስንከፍትላችሁ፤ እናንተም በተለመደው ባህላችሁ በመተሳሰብ እንድትተሳሰሩበት ነው”
እውነቱ ሁሌም ይሄው ነው። የፖለቲካውም የኢኮኖሚውም ማረፊያ ወህኒ ቤት ነው። የአባት ምርቃት ሆኖም ይሁን የሀበሻ የአጥንትና ደም ነገር፤ “በመተሳሰብ መተሳሰር” እስከዛሬ “የተለመደ ባህላችን” ሆኖ ቀርቷል። “ታማኝ ነው ያሉት የስለት እቃ ይሰርቃል” እንዲሉ ከመነሻው ስለ ዲሞክራሲያዊ ልእልና፣ ስለ ህዝባዊ ፍትህ፣ “አንድ ጥይት ስለማትተኮስባት” ሰላማዊ ሀገር፣ ነጻነቱን ካሰጡት አራስ ነብር ስለሆነ ህዝብ፣ በህዝብ ሀብት ስለበለጸጉ የቀድሞ ባለስልጣናት ሊያወጋ “ከዚህም ወዲያ ታላቅ መሪ፣ ከዚህም ወዲያ አማራጭ-የለሽ የፖለቲካ ድርጅት ኢትዮጵያ ከእንግዲህ አይኖራትም” ይባላል። አንድ ጀምበር ሳይሻገር ዲሞክራሲው የግሉ ዲሞክራሲ፣ ፍትሁም በአድልኦ የተሞላ የግሉ ፍትህ፣ ሰላሙም ጦር የሚሰበክበት፣ መሳሪያ የሚወለወልበት ከመንደር ቡድን እስከ ጎረቤት ሀገር የሚናቆርበት፣ የኢኮኖሚ ምዝበራውም ከስርዓታዊ-ዕዝ ኢኮኖሚ ወደ ፓርቲያዊ  አሊያም ባለስልጣናዊ ዕዝ-ኢኮኖሚ  Partisan Lords የፓርቲ- ባላባቶች የተፈጠሩበት ሆኖ ይገኛል።
ጊዜ ካለፈ አገር ከደቀቀች፣ ህዝብ ከተጎዳ በኋላ “በዚህ ባልፍ ኖሮ ድጡ አይጥለኝም ነበር” አይነት በውስጡ “አልተሳሳትኩም” የሚል አንድምታ ያለው ጸጸታዊ ማረሚያ ይቀርባል። የኢትዮጵያ አለመታደል፣ ከበቀልና ከጸጸት አዙሪት የማትወጣ ሀገር መሆኗ ነው። ጧቱን ይህን ባታደርግ  ጥሩ ነው ሲሉት፣ “ከእኔ ወዲያ  ፍልስፍና ላሳር ነው” ሲል ይቆይና “በግንዛቤ ችግር ምክንያት እስካሁን የሄድንበት መንገድ ሁሉ ስህተት ነበር። ዲሞክራሲያዊነትን ከማላላት  ማዕከላዊነትን ማጥበቅ፣ ከመብት ማክበር ይልቅ ጸጥታን ማስከበር ይሻላል ወዘተ” ወደሚል መደላደያ መሸጋገር እንግዳ አልሆኑም። አንዱን ቀዳዳ ሲያጥፉት ሌላ ቦታ እየተነደለ፣ አንዱን በር ሲዘጉት ሌላ እየተከፈተ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረው የኢትዮጵያ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር መላው እንደጠፋ ነው። ነውሩ በቀላሉ አይሸፈንም። ገበናው አደባባይ  ለመውጣት ጊዜ አይፈጅበትም። በሀገር ደረጃም ሆነ በመስሪያ ቤት ደረጃ መርከቡ ሲሰምጥ ከመርከቡ ከመውረድ ይልቅ ያልሰጠመው የመርከቡ ክፍል ላይ ለመቀመጥ መጋፋት እንደ ፖለቲካዊ ቅልጥፍና ከተቆጠረ ሰንብቷል። ለዚህ የሚሰጡ ወቅታዊ የሚመስሉ፣ በጥናት የተደገፉ የሚባሉ፣  በስብሰባ የጋራ መግለጫ የታጀቡ፣ በአዳዲስ መመሪያ የተቀነበቡ አያሌ ሽፋኖች ይቀርባሉ። ችግሩ ግን፤ “የሚዳቋ ጅራት፣ እርቃኗንም አይሸፍን፣ አምላክንም አያስመሰግን፤” እንደሚባለው መሆኑ ነው።

Read 1557 times