Sunday, 14 May 2023 00:00

እስኪ አንድ ጊዜ ስለ “አንዳፍታ ላውጋችሁ”

Written by  -አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

 አንድ በአካል የማያውቀኝ ህመምተኛ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ተኝቶ  ዘመዶቹ ሊጠይቀት ይሄዱና፣ ያው ሆስፒታል ሲኬድ ምናምን ተይዞ ይኬድ የለም? እዚህ በመሆንህ ልታገኘው ያልቻልከው ነገር ካለ ንገረን ምን እናምጣልህ ብለው ቢጠይቁት፣ የጌታቸው ጽሁፍ ወጥቷል ሲሉ ሰምቻለሁና እሱን ፈልጋችሁ አምጡልኝ አለ ብለው ነገሩኝ!፡፡ መቼም ይሄ  ህመምተኛ ጽሁፌን የፈለገው ተረት አምሮት ወይም ስለ ቅምጥል አስተዳደጌ ለማወቅ ፈልጎ ሳይሆን፣ የሀገሬ ልጆች ስቃይ ተሰምቶኝ የጻፍኩትን  ለማንበብ ነው፡፡ (ታዛ-ቅፅ 04.ቁጥር 38.ጥቅምት 2013)
         -አብዲ መሐመድ-        ወደ አገራችን መጥተው ስለ ጽላቱ በስፋትም በጥልቀትም አጥንተው መጽሐፍ  ካስጠረዙ ምሁራን መካከል  ስቱዋርት ሙንሮ ሄይ እና ግራሀም ሀንኮክ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ ሙንሮ ሄይ የተባለ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ምሁር “The Ark of Covenant” የተሰኘ በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተ መጽሐፉን ሲያዘጋጅ እንደ ግብአት ከተጠቀመባቸውና ካገለገሉት፣ በኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶችና ታሪካዊ ሰነዶች  ላይ ከተጻፉ ድርሰቶች መካከል የፕሮፌሰር  ጌታቸው ኃይሌ  ምርምሮች  ዋነኞቹ እንደነበሩ በጥናቱ አስቀምጧል፡፡
ሙንሮ በዚህ ጥናቱ ውስጥ ፕሮፌሰሩን  እንዲህ ሲል ያወሳቸዋል፤…“በእውነቱ በአገሪቱ  ለዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ በርካታ ቅርሶች በቃጠሎና በዘረፋ  መውደማቸው ይታወቃል፡፡ እንደ ጌታቸው ኃይሌን የመሳሰሉ የስነጽሁፍ ምሁራን  የወደሙና  የተጎዱ ስነጽሁፋዊ ቅርሶችን በመጠገንና በማቆየት ከጥፋት  እየታደጉ  በማኖር ረገድ ባለ  ውለታዎች ናቸው፡፡” (ገጽ 60)
የዩኒቨርሲቲ መምህርነት መደበኛ ስራቸውን በጡረታ አቁመው የእድሜያቸውን ማምሻ እንደልብ እያነበቡ እየጻፉና እየተመራመሩ ካገባደዱ በጣት ከሚቆጠሩ አንጋፋ የታሪክ ምሁራን መካከል ከሁለት መንፈቅ በፊት ያጣናቸው የስነ-ልሳንና ስነ-ድርሳን ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አንዱ ነበሩ፡፡ አዳዲስ ስራዎችን በመጽሐፍም በጥናታዊ ጽሁፍ  መልክም እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ሲያቀርቡ ኖረዋል፡፡ የህይወት ጉዞዋቸውን የሚያስቃኘውን መጽሐፍ ጀባ ካሉንም ሰነባብተዋል፡፡ ከምርምሮቻቸው ለአንድ አፍታ ፋታ ወስደው በግል ህይወቴ የደረሰውንና ያጋጠመኝን እስኪ አንዳፍታ ላውጋችሁ አንብቡኝ፣ ያሉንም በዚሁ የእድሜ  ጀምበር ማዘቅዘቂያ በአረጋዊነታቸው ላይ ሆነው ሳለ ነበር፡፡...“የህይወት ታሪኬን ለመጻፍ  ከገፋፉኝ ምክንያቶች አንዱ የቅርብና የሩቅ ወዳጆቼ ፍላጎትና ግፊት ነው፡፡ ታሪክህን  መዝግበው ወይም እኛ እንመዝግበው የሚሉኝ ሰዎች ቁጥር እየበዙም መሄዳቸው ነው”…ሲሉ ጀምረው የራሳቸውን የህይወት ታሪክ በራሳቸው ብዕር ከትበው የጊዜ ቅደም ተከተልን-የትዝታ  መስመርን ተከትለው፣  በሰባት ምዕራፎች የአገር ቤት አስተዳደጋቸውን፣  የካይሮ  የትምህርት ዘመን ቆይታቸውን፣ የጀርመን አገር ጉብኝታቸውን፣ የቤተሰብ አስተዳደር ተሞክሯቸውን…ወ.ዘ.ተ!  በዝርዝር አስፍረውልናል፡፡ (ለሦስተኛ ጊዜ አስመስጋኝ በሆነ በላቀ  ጥራት ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡)
በእርግጥ የጌታቸው ኃይሌ ግለ-ህይወት ታሪካቸው ከህይወት ዘገባዎች (diaries) የተውጣጣ ሆኖ በተለይ ደግሞ ከግል ማስታወሻዎች (memories) እና ከትዝታዎች (reminiscence) ጋር በጥብቅና በቅርብ የተቆራኘ ነው፡፡ ብርሃኑ አድማሱ የተባለ የታሪክና ቋንቋ ተመራማሪ በህይወት ታሪክ ላይ በጻፈው ጥናታዊ ሀተታው፤ አንድ የህይወት ታሪክ (Biography) ከሚመዘንባቸው አንኳር ሙያዊ ነጥቦች መካከል መራጭነት፣ አጓጊነት እና ስዕላዊ አመልካችነት…ቀዳሚ ሆኖ እሚቀመጥ ነው ይላል፡፡ አንድ ግለ ህይወት ታሪክ የሚጽፍ ሰው በኖረበት ዘመን ሁሉ ያየውን፣ የሰማውንና ያደረገውን ሁሉ አግበስብሶ የሚጽፍ ከሆነ አሰልቺ ብቻ ሳይሆን ሊጠላም ይችላል፡፡ ስለዚህ የሚጽፉትን የግድ መምረጥ ይኖርባቸዋል!…ይላል፡፡ በእርግጥ ምኑንና እንዴት ይመርጣሉ ስለሚለው አጥኚው ያስቀመጠው ባይኖረውም፣ ጌታቸው ኃይሌ በመሠረታዊነት የመራጭነት ችሎታቸው ላቅ ያለ ሆኖ ይታያል፡፡  በ“ፊደል ሰራዊት”፣ በ“ቱቢገን ዩኒቨርስቲ”፣ በ“ሂጂ ባላት ገንዘብ”…ውስጥ ጥሩ መራጭነታቸውን፤ ከ“መቃብር ቤት ወደ ኪራይ ቤት”፣ በ“ትልቅ ጭንቅላት ያለው አጭበርባሪ”፣ በ“እናንተ ናችሁ የምታባልጓቸው”…ውስጥ አጓጊነታቸውን፤ እንዲሁም   በ“የካምፓላ ስብሰባ”፣ በ”ኋይት ሀውስ”…እንደ ካርታ ስዕላዊ አመልካችነትን…በወጉ ተጠቅመው ሁሉን ያማከለ ተደናቂ ግለ-ታሪክ ጽፈውልናል፡፡ እኛም ጌታቸው ኃይሌን ለማየት በመነጽርነት ከተገለገልንበት ድንቅ ስራ ነው ብለን ለመመስከር አይገደንም፡፡
 ሊቁ ታሟል አሉ፣ ዳነ ወይ ከሞት
የሚያናፋ ወደል አህያ ረግጦት  
ጌታቸው ያወቀው ሁሉ ከማያረካው ከሊቅ አባት የተገኘ ልጅ ነበር፡፡ ከግራዝማች ኃይሌ ወልደየስ! ከመጽሐፈ ሰዋሰው እስከ መጽሐፈ መነኮሳት በሙሉ በቤታቸው ነበሩ፡፡ እንደመታደል ሆኖ የቤታቸው ግድግዳ “የቄሳር መንግስት መልክተኛ” በሚባለው በዘመኑ ጋዜጣ  ተሸፍኖ ነበር፡፡ አማርኛ ማንበብ የጀመረው እሱን እያንጋጠጠ በማንበብ ነው፡፡ ያነበበውን ለመድገም ምንም አያዳግተውም፡፡ እድሜው እየጨመረ ሲሄድ በትምህርት ቤቱ የሚሰጠው እውቀት ጥሙን መቁረጥ አልቻለም፡፡ ከሚተርፈው ጥቂት ጊዜ እየቀነሰ ብሪቲሽ ካውንስል ቤተ-መጻሕፍት ማዘውተር ተያያዘ፡፡ ታሪክ ይወድዳል፣ በተለይ የናፖሊዎን ታሪክ ሲበዛ ያስደስተዋል፡፡ ፒያሳ በርካታ መጽሐፍት የሚሸጥበት ቦታ ነበር በጊዜው፡፡ ከአባቱ ፍራንክ ለምኖ የታሪክ መጽሐፍ ይገዛል፡፡ ከምግብ ይልቅ የእውቀት ረሃብ የበለጠበት ጌታቸው፤ ከእውቀት ጋር የተለማመደው እራሱን እንዲህ በማስተማር ነው፡፡
እንደ ልጅ  በቅጡ ሳይጫወት፣ አስራ ሰባት አመት እስኪሆነው ድረስ ለእግሩ ጫማ ያላየባት፣ ተወልዶ ያደገባት የሸዋ ግዛት የሆነችው ሸንኮራ ተብላ በምትጠራ ብዙ ታሪኮች የሚከናወኑባት ሀገሩ ነበረች፡፡ ሸንኮራ ውስጥ  ታሪክ አድርጎ ቦታ ያልሰጣቸው እንደ ቀልድ የሚያሰፍራቸው የልጅነት ትዝታ ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው ወግና ባህሎች፣ ስነ-ቃሎች፣ አፈ-ታሪኮች፣ ማህበራዊ መስተጋብሮች፣ የተፈጸሙ የታሪክ ሁነቶች…በጣሙን ያስደምማሉ፡፡… “ጎረቤታችን አባቴ እንደ አባቱ የሚያያቸው ጌታ ዲነግዴ አቅራቢያችን የሚውለው የሳምንት ገበያ ሲደርስ፣ ከከብቶቻቸው አንዱን በሬ ለመሸጥ ገበያ ይወስዳሉ፡፡ ግን አንዳንድ  ጊዜ ገበያ እስኪፈታ እዚያው ውለው በሬውን ሳይሸጡት ይቀሩና መልሰው  ያመጡታል፡፡ አባቴ “ጌታ ምነው በሬውን መለሱት ገዢ አጡ እንዴ?” ሲላቸው “የለም  ልጄ  ገዢስ ሞልቶ ነበር፤ ግን ስጠይቃቸው በቀዬው ለበሬዬ የሚበቃ የመስኖ ሳር ያለው አንድም ሰው አላገኘሁም፡፡ ለእነሱ በሬዬን ሸጬ ረሃብ ላይ እንዳልጥለው ብዬ አመጣሁት” ይሉታል፡፡ (ገጽ 47)
ጌታቸው ኃይሌ ከሀገር ውስጥ አዲስ መንፈሳዊ ኮሌጅ እስከ ሞስኮ፣ ካይሮ…ደረጃ በደረጃ እያደገ ጀርመን ዩኒቨርስቲ ድረስ የሚጓዘውን የትምህርት ዘመናቸውን፣ በግለ-ታሪካቸው ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ያወጉናል፡፡ አብረዋቸው ትምህርት ላይ ከነበሩት አብዛኛዎቹ ምዕራብ አውሮፓውያን በይበልጥም ጀርመኖች ናቸው፡፡ ከጌታቸው ውጪ ብዙ ኢትዮጵያውያን አልነበሩም፡፡ (በኋላ ላይ ፕሮፌሰር አምሳሉ አክሊሉ፣ ስርገው ሐብለ ስላሴ፣ እጓለ ገብረ ዮሐንስና ሰይፉ መታፈሪያን አግኝተዋል) የየት ሀገር ልጆች እንደሆኑ ሲጠያየቁ እሱ ከኢትዮጵያ ሲል ሁሉንም ያስገርማቸዋል፡፡ ክረምት ለሁለት ወር እረፍት ይዘጋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነው ማንኛውንም ስራ ይሰሩና በአጠራቀሙት ገንዘብ አገር ለማየት የሚነሱት፡፡ የስራው ዓይነት ከቀላል የአሸዋና ሲሚንቶ ቡኮ አቀባይነት እስከ ከባድ የማርቼዲስ ቤንዝ ባትሪ ገጣጣሚነት ይደርሳል፡፡ ከዚያ ውጭ የዙረት፣ የሀገር ጉብኝት መርሀ ግብር በሰፊው ይደረጋል፡፡ አንዳንዴ የቦታ ቅኝት በእግር ጉዞም ይከናወናል፡፡…“አንድ ቀን ፓሪስ አንድ ሠፈር ውስጥ ጭር ባለ መንገድ ስሄድ ሁለት ወጣቶች አንድ ወንድና አንድ ሴት እፊት-እፊቴ ይሄዳሉ፤ ቆም ብለው ሲሳሳሙ ሳይ፣ “እኔን ያላፈሩኝ ከሰው ባይቆጥሩኝ ነው፣ ጭር ያለ መንገድ ሰው ሳያያቸው  የሚሳሳሙት” ብዬ ዘረኝነታቸውን ታዝቤ አለፍኩ፡፡ (ገጽ 111) መጽሐፉ ለታሪክ ሁነኛ ግብአት መሆን የሚችሉ ብዙ ትርክቶች አሉት፡፡ በተለይ ምሁሩ የወጣትነት ተግዳሮቶችን የተረኩበት የመጽሐፉ ክፍል ለአንባቢ ሳቢና ማራኪ ናቸው፡፡ ማለፍያ አድርገው ተነባቢ በሆነ ቀላል አማርኛ ከትበውታል፡፡ የህይወት ጉዞዋቸው ያን ያህል ውስብስብ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ በሚያብሰለስሉና በሚያስተክዙ  ታሪክና  ባህል ነክ ተረኮች የተሞላ መሳጭ ነው፡፡ በዚያው ልክ አስቸጋሪ የህይወትን ዚቅ ለመግፋት የተገደዱበት ጊዜ እልፍ ነው፡፡ በተለይ ስለ ኢትዮጵያ  ፖለቲካ በሚጽፉበት ዘመን፡፡ ጌታቸው እንደ ዜጋ በሀገር ጉዳይ ይመለከተኛል በሚል በሚሳተፉበት ወቅት “ፖለቲካውን ለኛ ትተህ አንተ በሙያህ ላይ አትኩር” የሚሉ ከተለያዩ አካላት የሚደርሷቸውን ትዕዛዛት ወደ ጎን ብለው የደርግን የተሳሳተ የአገዛዝ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ይጎዳታል በሚል እሳቤ፣ የማያምኑበትን በመቃወም ሲጽፉ  እንዴት እንደነበር፣ ሲናገሩ ያደረጓቸውን ንግግሮች በየምዕራፉ ጣልቃ አጽንኦት ሰጥተው ምሁሩ ያጋራሉ፡፡ አንዳንዴ እሳቸውን እንዲህ የሚሏቸውን ሰዎች አጥብቀውና አበክረው ይጠይቃሉ፡፡ ስለ ሀገሩ ፖለቲካ ለመናገር መብት ያለውና የሌለው አለ ወይ? ባለሙያ ምሁር መሆን የመናገርና የመጻፍ ነጻነትን ያስገፍፋል ወይ? ባለሙያ ምሁር እንዳይናገር፣ ሙያ አልባው ወይም ያልተማረው እንዲናገር የሚያዝዝ  ባህልም ሆነ ህግ አለ ወይ? ስለ እናት አገሩ ለመናገርና ለመጻፍ መብት ያለው ማነው? ታዲያ ይኼንን ጊዜና እውቀታቸውን ለፖለቲካው ሲያውሉ ለእረፍትና ለመዝናናት ሲሉ ብቻ ሳይሆን ለሙያና ለምርምር ሊሰጡት ከሚገባ ጊዜ እየወሰዱም መሆኑ ለአገራቸው ያላቸውን ተቆርቋሪነት በጉልህ እናይበታለን፡፡ በሁለቱም ስርአቶች ውስጥ ለአገር አንድነት ያደረጓቸውን ትግሎችና የነበራቸውን ተሳትፎ፣ የከፈሉትን  ዋጋና መስዋዕትነት ሊያሳዩን ሞክረዋል፡፡ ጌታቸው ኃይሌ በአብዮቱ ወቅት በነበራቸው ግላዊ ጠንካራ አቋም ምክንያት ለደርግ ታጣቂ ፖሊሶች እጄን አልሰጥም በሚል የተኩስ ልውውጥ፣ የጥይት ዶፍ ወርዶባቸው ያልሞቱት በተአምር ነው፡፡ ከዚህ ክስተት አንዷ ጥይት አከርካሪያቸውን ስላገኘቻቸው ቀሪ ዘመናቸውን በዊልቸር ላይ ተቀምጠው ለመግፋት ቢገደዱም  እንኳን በመጽናናትና በኑሮ ተስፋ መቁረጥ መሀል የሚያደርጉትን ግብግብና እልህ አስጨራሽ  ከራስ ጋር ፍልስፍና ነክ ሙግታቸው በእጅጉ ያስደምማል፡፡…“አሁን አሜሪካ አገር ስኖር ሐኪም ቤት እጎበኛለሁ፣ በአጋጣሚው ነርሶችና ሀኪሞች ሌሎችም ምን ሁነህ ነው ወንበረኛ  የሆንከው ሲሉኝ፣ ምስራቅ ላያምኑህ አራት ሺህ ጥይት ተተኩሶብኝ አንዷ ስላገኘችኝ ነው ማለትክን አቁም” ትለኛለች፡፡ እኔ ግን የምነግራቸው ሲደነግጡ ለማየት እየፈለኩ ብቻ ሳይሆን፣ ዲክቴተሮች እንዴት እንደሚጫወቱብን ለማሳየት ጭምር ነው፡፡” (ገጽ 250)ደራሲ ክቡር ሀዲስ አለማየሁ የኢትዮጵያ ዘመናዊውን ትምህርት ከጥንቱ  የኢትዮጵያ ትምህርት ጋር ለማያያዝ ብዙ ደክመው አልሆነላቸውም፡፡ እንደ አብዬ መንግስቱ ለማ ያሉ የባህል ጠበብት ደግሞ የግዕዝ ቅኔ ህጉና ደንቡ፣ ስርዓቱና ምጥንነቱ እንዲሁም ሰምና ወርቁ፣ ዘመናዊውን ስነጽሁፋችንን ሊያበለጽገው ስለሚችል ይዘቱን እንኳን ባይሆን ቅርጹን ልንጠቀምበት ይገባል ይሉ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሊቃውንት ቀጥሎ (በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ ክፍል አስተማሪ ሆነው የግዕዝ ስነጽሁፍ፣ የአማርኛ ሰዋሰውና የአጻጻፍ ዘዴ፣ ዐረቢኛ እስከ 1969 ዓ.ም እና ከ1972 እስከ 1974 ዓ.ም እንደማስተማራቸው) ጌታቸው ኃይሌ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡ “ቅኔ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የቅኔ ኃይሉ ግዕዝ ነው፡፡ በግዕዝ ነው የተሰጠው፡፡ ግዕዝ ያላወቀ ቅኔ አወኩ ሊል አይችልም፣ መሠረቱ ቅኔ ነውና! ግእዙን እንኳን መማር ቢያቅተን የግእዝ ስልቱን፣ የግእዝ ጉባኤ ቃና የመወድስ ስልት አምጥተን በአማርኛ  ልንገጥምባቸው እንችላለን!” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ሁሉም በየፊናቸው ግእዝን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ተሰጥቶ እንድንማር የበኩላቸውን ጥረዋል፡፡ ምንም እንኳን ጌታቸው መስካቸው የሴም ቋንቋዎች ነገረ ቃላት ቢሆንም፣በግዕዝ ሥነጽሁፍ ላይ በይበልጥ አትኩረው ሰርተዋል፡፡ (“ደቂቀ እስቲፋኖስ” ሙሉ በሙሉ ከግእዝ ቋንቋ የተረጎሙት ብቸኛ ስራቸው ነው) ካታሎግ በማዘጋጀት ስራ እያንዳንዱን መጽሐፍ ለተመራማሪ በማስተዋወቅ ረገድ ሰፊ ቦታ አላቸው፡፡ ይህንንም ሂደት በግለ-ታሪካቸው “ጤንነትና ስራ” በሚል ንዑስ ርዕስ  በዝርዝር አስፍረውት እናነባለን፡፡ “ያልታወቀ ነገር መርምሮ ማወቅና የማውቀውን ለማያውቅ ማካፈል (ማስተማር) ልዩ ደስታ ይሰጠኛል፡፡ እኔ በህይወቴ ሙሉ ተማሪ ነኝ፡፡ ምኞቴም የማውቀውን እያስተማርኩ የማላውቀውን እየተማርኩ ለመኖር ነው፤ ለሀገሬ መስራት የምችለው በአስተማሪነት ነው!..”.የሚሉን ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፤ ባልተሟላ ጤንነት ውስጥ ሆነው በተስፋ እጦት ተውጠው ሞታቸው እየታሰባቸው በተለያዩ የውጭ ሀገራት በህክምና እየታገዙ (ከጥቁር አንበሳ እስከ እንግሊዝ) ያከናወኑትን ተግባራት፣ ያገኟቸውን ሽልማቶች ድንቅ ምሁርነታቸውን እንድንመሰክር ያደርገናል፡፡… “ለዶክተር አስራት ወልደየስ…እንግዲህ ቆሜ መሄድ ካልቻልኩ መኖር አልፈልግም እለዋለሁ፡፡ የተማርከው  ልትጽፍ ልታስተምር ነው ወይስ ወታደር ልትሆን ነው? ውትድርናውን ትቶ ሌላ ስራ ቢጠራ ደግ ነበር፣ አካሄዱን አይቼ ዝም እለዋለሁ፡፡ “ለማሰብ ራስህ ደህና ነው፤ ለመጻፍ እጅህ ደህና ነው፤ ህክምናህን ስትጨርስ ስራህን ትቀጥላለህ” (ገጽ 256)  ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በሀብትም ሆነ በሹመት ከታወቁ ቤተሰቦች አልተወለዱም፡፡ እነ እገሌ የሚባሉ ዘመዶች የሏቸውም፡፡ ይሁንና መድረስ ከፈለጉበት ቦታ ለመድረስ እንዲህ ያሉ ዘመዶች ስለሌሏቸው ሳይደርሱ አልቀሩም፡ በአሜሪካ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ከሚያስተምሩና እንደ ናሳ ባሉት የምርምር ድርጅቶች ከሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ይበልጥ በስፋት ይታወቃሉ፡፡ የሰባ አምስት አመት ታሪክ በአንዳፍታ ተነግሮና ተጽፎ  እሚቋጭ አይደለም፡፡ በአንድ የጋዜጣ አምድ ላይ ተቃኝቶም እንዲሁ፡፡ በአርምሞ ካስታወሱት አሳጥረው ያኖሩልን ድርሳን ግን ከሞላ ጎደል ጠቃሚ የግለ-ታሪክ ሰነድ ነው፡፡ የተሟላ ማስታወሻ በእጃቸው ሳይኖራቸው በአይምሯቸው ብልጭ ሲል ይዘው የከቱት ድንቅ የእድሜ መንገድ ትዝታም ጭምር ነው፡፡


Read 1130 times