Sunday, 30 April 2023 00:00

ከአሽከርነትና ሎሌነት ወደ ነጻነት የሚደረግ ጉዞ!

Written by  በጸጋው ማሞ
Rate this item
(1 Vote)

የሰው ልጅ “ከጫካው ሕግ” ጀምሮ ያደረገው ዝግመታዊ የነጻነት ጉዞ እጅጉን አስደናቂ ቢሆንም፥ በዚህ ጉዞ ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን ያሳረፍነው ሱታፌ ግን እጅግ ኢምንት ይመስለኛል። ለባሕርያችን የማይስማማውን አሽከርነትንም ለምደነዋል። አቢሲኒካ መዝገበ ቃላት አሽከርነትን፥ “ታዛዥ፣ ሎሌ፣ ተከታይ፣ አንጣፊ፣ ጋራጅ አስታጣቢ፣ አልባሽ፣ መጫሚያ አቀባይ፣ ዠርባ ጠቋሚ...ሳህን አመላላሽ” ይለዋል። ፕሮፌሰር ምንዳርአለው ዘውዴ ደግሞ፤ የዘመኑን የልሂቃን አሽከርነትና ሎሌነት፥ “ስናዳራዊነት” በሚል የሚመጥን ጸያፍ ቃል ይገልጸዋል። ስናዳሪ ማለት “ነፍሱን ለከርሱ፣ ህሊናውን ለኪሱ፣ ነጻነቱንና ክብሩን ለዕለት ጉርሱ የሸጠ ኑባሬ ነው” ሲል ከሰው ተፈጥሮ አሳንሶ እንስሳዊ ጠባይ ያጎናጽፈዋል።
ነጻነት እኩልነትና ወንድማማችነት
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በበኩላቸው፥ “አሽከርነት ባሕላችን ነው... ማሰብ የጌታው ተግባር እንጅ የአሽከሩ አይደለም...ጌታው ካላሰበለት በቀር አሽከር ነጻነት ስለሌለው አያስብም” ይላሉ። አሽከሮችና ሎሌዎች ዘንድ  እውነት የሚፈተንበት አመክንዮ(Logic) እና አስተውሎት (Rationality) ስለሌሉ፥ እውነት የሚባለው የህሊና ፍሬ የላቸውም፤ የሙሉ ጊዜ ሥራቸውም አለቃቸውን ማስደሰትና ስለ እርሱ የውዳሴ ተረት መተረክ ነው። አሽከርነት ሥነ ኑባሬያዊ ደኅንነቱን (Onthological Security) ያጣ፣ ከሞቱት በታች ከሚኖሩት በላይ የሆነ፣ ኅሊና የሌለው፣ ደመ ነፍሳዊ እንስሳ ነው ማለትም ይቻላል። አሽከር ስለ ነጻነትና ስለ እውነት ሊያስብ የማይችል፣ ኢ-ሰዋዊ ጠባይ ነው።
በክርስትና ነገረ መለኮት ትምህርት ውስጥ፥ የሰው ልጅ በአምላክ አምሳልና አርአያ የተፈጠረ የአምላክ ባሕርያት ያሉት፣ ልዕለ ፍጡር እንደሆነ ይናገራል። የሰው ልጅ በነጻ ከአምላክ በጸጋ ከተሰጡት ባሕርያት ውስጥ አንዱ ደግሞ ነጻነት (freedom) ስለሆነ በነጻነት የማሰብ፣ በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ በነጻነት የመሥራት፣ በነጻነት የመኖር መብት፣ ማንም በበጎ ፈቃድ የማይሰጠው አንዱ የክርስትና መገለጫ እንደሆነ ይናገራል። ዳሩ ግን የሰው ልጆች ለዘመናት የአምባገነን ባለሥልጣንና የባለሀብቶች አሽከር ሆነው፣ ሺህ የሰቆቃ ዘመናትን አሳልፈዋል። አሽከርነት የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ሳይሆን፣ የሰው ልጆች አምላክ የሰጣቸውን እምቅ የግል ሀብት በስንፍናቸው ምክንያት ሳይጠቀሙ ሲቀሩና ለሌሎች በፈቃዳቸው አሳልፈው ሲሰጡ የሚፈጠር የቁም ሞት ነው።
በጥንታውያን የነገሥታት ዘመን፣ የንጉሥና የባላባት አሽከር- ሎሌ መሆን ክብር ነበር። አሽከሮችና ሎሌዎች በክብርና በኩራት፣ “እኔ የንጉሥ እከሌ፣ የባላምበራስ እገሌ አሽከር ነኝ” እያሉ ይፎክሩ ነበር። ለሌላ አምባገነን ባለሥልጣንና ባለሀብት ታዛዥነትን፣ አገልጋይነትን፣ ባርነትን እንደ ትልቅ ክብር ቆጥሮ፣ የራስን ክብርና ነጻነት ነፍጎ፣ በሌላ ሰው ማንነት ውስጥ ራስን ማስጨነቅ፣ የሰው ልጆች ትልቁ ስቃይ ነው። የሰው ልጆች ይህንን መራራ ስቃይ ሲቀበሉ ኖረዋል፤ አሁንም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ በዚህ የአሽከርነትና የሎሌነት ኢ-ሰዋዊ የሥነ ልቦና ማንነት የሚሰቃዩ እጅግ ብዙ ናቸው። አንዳንዶች ይኸንን የአሽከርነት ማንነት በጸጋ ተቀብለው፣ ማሰቢያ ኅሊናቸውን በፕሮፓጋንዳ ደፍነው፣ እንደ ኤሳው የሰውነት ብኩርናቸውን በምስር ወጥ ለውጠው፣ በአደባባይ ሳያፍሩ ለግፈኞች ሲያሸረግዱ ታይተዋል። እንደ ሊጋባው በየነ ያሉ ዘመን ያበቀላቸው ክስተቶች ደግሞ “ሀገሬንና ሕዝቤን እንጂ ከግፈኞች ጋር ኅብረት የለኝም” በማለት ሥልጣንን፣ ያማረ የንጉሣውያን የተዋበ ልብስን፣ የቤተ መንግሥት ጠጅና ጮማን እየናቀ፣ ከኅሊናው ጋር ቀዝቃዛውን እስር ቤት ይመርጣል። ሀገር በጣሊያን ተደፈረች ባሉት ጊዜ ግን ከእስር ቤት ወጥቶ፣ መትረጌሱን እንደ ቸኩቬራ ተሸክሞ በሰሜን የትግራይ ተራራ ሲዋጋ፣ ከንጹህ ኅሊናው ጋር ለኢትዮጵያ ሰማእትነትን ተቀበለ። ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት እንደ ሊጋባው በየነ ያሉ ነጻነታቸውን በሆዳቸው ያልቀየሩ፣ ጀግኖች እንጂ የንጉሡ አሸርጋጆች አይደሉም።
ከ2000 ዓመታት በፊት የጽርዕ (የግሪክ) ፈላስፎች፣ የሰው ልጅ አርነት ይወጣ ዘንድ ቆም ብለው በኅሊናቸው አሰላስለው የተፈላሰፉበት “ያ” ነጻነት፥ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደግሞ እንግሊዛውያን “የሰው ልጅ ነጻ ፍጡር ነውና በነጻነት ይኖር ዘንድ ይገበዋል” በማለት ከፍተኛ ንቅናቄ በመፍጠር፣ የማግና ካርታ ስምምነት አደረጉ። ከማግና ካርታ ስምምነት መካከል “ማንም ዜጋ ከሕግ ውጭ ሊታሰር፣ ንብረቱን ሊያጣ፣ ሕይወቱን ሊያጣ ሊሰደድ አይገባውም፥ ፍትሕንና መብትን ለማንም አንሸጥም” በማለት የነጻነት ነጋሪት ለሰው ልጆች ሁሉ ጎሰሙ። (“መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ፤ገጽ 29)
 እንግሊዛውያን የዛሬ 800 ዓመት የጠየቁትን ጥያቄና በሕግ የደነገጉትን የሰው ልጅ የነጻነት መብት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓለም እጅጉን በተራቀቀበት በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ አይደለም ሊጠቀምበት ይቅርና ለመጠየቅ አለማሰቡ አስደንጋጭ ነው። የእንግሊዝ ሕዝብ የዛሬ 800 ዓመት የጠየቀውንና የተገበረውን የነጻነት መብት ለምን የኢትዮጵያ ሕዝብ መጠቀሙ ቀርቶበት ለምን ለመጠየቅ እንኳን አላሰበም? አንድ ኢትዮጵያዊ ይህንን የነጻነት መብት ለማግኘት ከሀገሩ ተሰዶ የግድ አሜሪካ መሄድ አለበት ወይ? አንጻራዊ የግለሰብና የማኅበረሰብ በነጻነት የማሰብ፣ የመንቀሳቀስና የመሥራት መብት እስካልተሰጠ ድረስ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማምጣት የህልም ቅዠት ነው።
አሁን አሁንማ ኢትዮጵያ ውስጥ አሽከርነትና ሎሌነት የማይገኝ አዋጭ የኑሮ ዘይቤ እየሆነ ነው። አሽከርነት የማይገኝ ቅንጦት እየሆነ መምጣቱ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያንም በኋላቀሩ በጥንታዊው የሰው ልጅ የማኅበረሰብ ሥርዓት ውስጥ ተቸክላ እንደቆመች አንዱ ማሳያ የመደብና የጎሣ፣ የገዥና የተገዥ፣ የጌታና የባሪያ፣ የንጉሥና የአሽከር ሥርዓት መቀጠሉ ነው። ሎሌነትንና አሽከርነትን አይደለም ከዜጎቻችው ላይ ይቅርና ከውጭ አገር ዜጋ ላይ ያነሱና ነጻነትን ያወጁ አገራት በኢኮኖሚ ከፍታ ላይ ይገኛሉ። አሜሪካ እ.ኤ.አ በ1976 ዓ.ም፤ “የሰው ልጆችና የዜጎችን አዋጅ” ስላወጀችና ስለተገበረች ለሰው ልጆች ሁሉ በንጽጽር ምቹ ሁኔታን ስለፈጠረች ምሑራን ከዓለም ዙሪያ እየተሰበሰቡ አሳድገዋታል። አንድ እውቅ ኢትዮጵያዊ የፊዚክስ ባለሙያ አሜሪካን ቢሄድ፣ በንጽጽር ከሀገሩ ኢትዮጵያ ይልቅ ባእድ በምትባለው አሜሪካ የተሻለ ነጻነት፣ ክብርና ክፍያ ካገኘ በዘመናት ያካበተውን እውቀት ለአሜሪካ ያለስስት የማይሰጥበት ምክንያት ምንድነው? በግልጽ አሽከርነት ውስጥ ግን ሳይንሳዊ ምርምርም ሆነ ጥልቅ ወገናዊ አሳቢነት አይኖርም።
የፈረንሳይ አብዮት የነጻነት ትሩፋት እንደ ማሳያ
የፈረንሳይ አብዮት ትሩፋትን አሁን እኛም ብንቋደሰው ምን አለበት ነበር? የፈረንሳይ ሐቀኛ ሊቃውንት በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ (በ1789 እኤአ) ከተጋረጠባቸው ችግር ባሻገር ራሳቸውን በጥልቀት ሲገመግሙ፥ በማኅበረሰብ የእድገት ጎዳና ላይ በጨቋኝ ሥርዓት የተነሳ ባሉበት መገተራቸውን (ቆመው መቅረታቸውን) አምነው፣ በጊዜው የሚያስፈልገውን የነጻነት አብዮት በማወጅ፣ ነጻነታቸውን በብርቱ ክንዳቸው ተቀናጅተዋል። አሽከርነትንና ባርነትን ከዜጎቻቸው ላይ ለዘላለም ቀብረውት፣ በልሂቃኖቻቸው እየተመሩ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግናቸው መጓዝን ቀጥለውበታል። የፈረንሳይ ልሂቃን፥ ፈረንሳይን ከጨቋኝ ገዥዎቻቸው ነጻ ለማውጣት አብዮቱን በጠመንጃ አፈሙዝ እንዲሆን ወስነው የጦር አዋጅ አወጁ! አዋጃቸውም እንዲህ ይል ነበር፤ “ከአሁን ጀምሮ የሪፐብሊኩ ጠላቶች የሀገሪቱን መሬት ለቀው እስኪወጡ ሁሉም ፈረንሳውያን በቋሚነት ለጦሩ አገልግሎት እንዲሰጡ ይጠበቅባቸዋል፤ ወጣቱ ይዋጋል፣ ያገቡት ብረት ያቀልጣሉ፣ ሥንቅ ያቀብላሉ፣ ሴቶች ድንኳንና ልብስ ያሰናዳሉ፣ በሆስፒታሎች ያገለግላሉ፣ ሕፃናት ካረጁ ጨርቆች ቁስል መሸፈኛ ያዘጋጃሉ፣ እንዲሁም አዛውንት አደባባይ ላይ በመውጣት የጦረኞችን ወኔ ይቀሰቅሳሉ” የሚል ነበር። –ሆሞዱስ ገጽ 288።
እንደ መታደል ሆኖ የፈረንሳይ አብዮት የተሳካና ውጤቱም ያማረ ነበር። የዘመናዊው ዓለም የሰው ልጆች እሴት የሆኑትን እኩልነትን (Equality)፣ ነጻነትን(Freedom) እና ወንድማማችነት(Fraternity) የደም ዋጋ በመክፈል አምጠው፣ ወልደው፣ አሳድገው ሊተገብሩት ችለዋል። ይህ የሊበራሊዝም እሴቶች (Equality, Liberty and Fraternity) በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሰው ሁሉ የሚጋራው የሰው ልጆች ሁሉ መብት የሆነውን ፈረንሳውያን ብሔራዊ መመሪያቸው ወይም አርማቸው አድርገውታል፤ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነት ወይም ሞት (Liberty, Equality, Fraternity or Death) በማለት የዓለምን የዝግመተ ለውጥ ሂደት አፋጥነውታል ማለት ይቻላል። ለዘመናት በኃይል የተጫነውን የዜጎችን፣ የማኅበረሰብን የአሸከርነትና የሎሌነት ግንብ ደርምሰው የኹለንተናዊ ብልጽግና መሰረት የሆኑትን የሰው ልጆች መብቶችን ቢያንስ ለሕዝባቸው አረጋግጠዋል። እነዚህ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች በሦስተኛው ዓለም(ባላደጉ) አገራት በወረቀት ላይ ከመስፈር የዘለለ በገቢር የሉም። ዜጎችና ጎሣዎች ለባለሥልጣንና ለባለሀብቶች(Capitalist) አሽከር የመሆናቸው ዕድል እየጨመረ ይገኛል። ይህ ግን የሰው ልጆች ተፈጥሮአዊ ጠባይ አልነበረም። የኢትዮጵያ ሕዝብም ለሺህ ዘመናት በአጥንትና በደም የተዋሐደ ወንድማማች ሆኖ ሳለ በወረቀት በሰፈረ ፈጠራዊ የጠላት ተረክ የተነሳ እኩልነትንና ነጻነቱን አረጋግጦ ወደ ቀጣይ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጅና የኢኮኖሚ ውድድር ውስጥ መግባት ሲገባው፣ ዓለም ሰልችቶትና ንቆት ወደ ተወው አርቲፊሻል የዘውግ የርስበርስ የጦርነት የዝቅጠት አዙሪት ውስጥ ገብቷል።
መንግሥታዊ አሽከርነት
ኢትዮጵያ ውስጥ አሽከርነትና ሎሌነት ከግለሰቦች ይልቅ በካቢኔዎችና በመንግሥት ደረጃ ላቅ ያለ ይመስላል። በመንግሥት ተሿሚ ከቀበሌ ሊቀመንበር እስከ ክልልና የፌደራል ተሿሚ ባለሥልጣናት ከአሽከርነት የዘለለ ሚና የላቸውም፤ ከበላይ ጌታቸው የተሰጣቸውን ትእዛዝ ለማስፈጸም ይቻኮላሉ፣ መሪያቸው ሲስቅ አብረው ይስቃሉ፣ ሲያኮርፍ ያኮርፋሉ፣ ሲፎክር አብረው ይፎክራሉ፣ ሲሳደብ አብረው ይሳደባሉ፣ አነቃቂ ንግግር ሲናገር እነሱም ለመናገር ይፍጨረጨራሉ፣ ሃይማኖታዊ ጥቅስ ሲጠቅስ የማያውቁትን ጥቅስ ለመጥቀስ ይንደፋደፋሉ፣ ወሬ አድርሱ ሲባሉ የሚቀድማቸው የለም፤ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ሳይሆን ለበላይ ባለሥልጣንን አሽከር ሆነው ሲያገለግሉ ይኖራሉ። አሽከሮችን መመልመል የለመደ መንግሥት ሁል ጊዜ እውቀት የሌላቸውንና የባርነት ሥነ ልቦና የተዋረሳቸውን ድሆችን እየፈለገ ለሎሌነት በመቅጠር ለአገርና ለመጭው ትውልድ ጉስቁልናንና ውርደትን ያወርሳል። ኢትዮጵያ ውስጥም እየሆነ ያለው ይኸው የውርደት የታሪክ አዙሪት ነው። አሁን ላይ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ላይ ያላት ሥዕለ ኅሊና ጸያፍ የሆነ የድህነትና የርስበርስ ጦርነት ምሳሌ ነው። በዚህ ደግሞ መላ ኢትዮጵያውያን ሊያፍሩና ሊሸማቀቁ ይገባል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ አሽከርነት ከግለሰቦችና ከካቢኒዎች አልፎ ኢትዮጵያም የውጭ አገራት አሽከር እንደሆነች እንዲህ በማለት ይገልጹታል፤ “የጌታና የአሽከር ባሕላችን ድንበር አልፎ ሄዷል፤ አፄ ኃይለ ሥላሴ የአሜሪካ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ የሶቪየት ኅብረት፣ አቶ መለስ ደግሞ በባሰ ሁኔታ የአሜሪካና የአውሮፓ አሽከሮች እንደነበሩ የሚያምኑ ይመስለኛል” ይላሉ –”አድማጭ ያጣ ጩኸት” መጽሐፍ ላይ ገጽ 137።
 ታዲያ ሥርዓተ ትምህርቷን እንኳን ሳይቀር ለባእዳን አሳልፋ የሰጠች አገር፣ በሁሉም ነገር ጥገኛ የሆነች የድሀ ድሀ ሀገር አሽከር ባትሆን ነበር የሚገርመው? አሁንስ ብልጽግና ከበፊተኞቹ መሪዎች የበለጠ አሽከር የማይሆንበት አመክንዮ ይኖራል ወይ? ብልጽግና ደካማ አሽከሮችን እየመለመለ አገሪቷን እንጦርጦስ ማውረዱን እስካላቆመ ድረስ የሌሎች ኃያላን አገራት አሽከር ከመሆን አይድንም። የድህረ ቅኝ ግዛት ቅኝ ገዥ ኃያላን አገራት አድርጉ የሚሉትን አለማድረግ አይችልም። በቋንቋ ላይ ተመስርታችሁ በዘውግ ተደራጁ ሲሉን በዘር  መደራጀት፣ የትጥቅ ትግል አድርጉ ሲሉን ማድረግ፣ ተዋጉ ሲሉን መዋጋት፣ መዋጋቱን አቁሙና በዚህ መሰረት ተስማሙ ሲሉን ባዘዙን መሰረት መስማማት፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲያችሁን ቀይሩ ሲሉን መቀየር የግድ ይለናል፤ ምክንያቱም አሽከሮችን ቀጥሮ የሚያሰራ የመንግሥት ሥርዓት የሌላ መንግሥት አሽከር መሆኑ የግድ ነው ። እንደ እውነቱስ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት የአገር ውስጥን የአሽከርነት ሥርዓት እስካልቀየረ ድረስ የምዕራባውያን ሆነ የአረቦች አሽከር አለመሆን አይችልም። የራሱን ሕዝብና ልሂቃን ከሎሌነት አስተሳሰብ ነጻ ያላደረገና በሁሉም ሕዝብ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ያልመሰረተ ሀገር ከአሽከርነት አዙሪት ሊወጣ አይችልም። የባሪያ አሳዳሪዎች ባሪያዎቻቸው ነጻ እንዲወጡ እንደማይፈልጉ ሁሉ ኃያላን አገራትም አሽከር ሀገሮች ነጻ እንዲወጡ አይፈልጉም። አሽከሮችና ሎሌዎች ነጻ እንዲወጡ ከፈለጉ ዘመናዊ የነጻነት ትግሉን መቀላቀል አለባቸው። ዜጎች ነጻ ሲወጡ ሀገርም ነጻ ትወጣለች።
አሽከር ወይም ሎሌ አይደለም ጥልቅ ምርምር አድርጎ አዲስ ግኝት ወይም ለችግሮች የመፍትሄ ሀሳብ ሊያመጣ ይቅርና በራሱ ማሰብ አይችልም፤ ስለዚህ አሽከር አይደለም መሪ ሊሆን ይቅርና እንደ ሰው አይቆጠርም፥ በራሱ ሙት ስለሆነ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ዛሬም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከቀበሌ አንስቶ እስከ የሀገር ሚኒስቴር ድረስ የሚሾሙት ብቃታቸው ተፈትኖ በሙያቸው በ(Proffession) ሳይሆን የአሽከርነት መጠናቸውና ጎጣቸው ታይቶ ነው፤ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ የማይድን ካንሰር ሆኖ እያመነመናት ይገኛል። ኢትዮጵያ ትበለጽግ ዘንድ በታሪኳ አድርጋው የማታውቀውን የዜጎችን፣ የማኅበረሰብን፣ የተሿሚ ባለሥልጣናትን አሽከርነትና ሎሌነትን አንስታ ነጻነትን ማጎናጸፍ አለባት። ነጻነት ደግሞ በቀላሉ በችሮታ ስለማትገኝ ዘመኑን የዋጀ ሥልጡን የተባበረና ያላሰለሰ የዜጎችን ተጋድሎ ትሻለች።

Read 1845 times