Saturday, 08 April 2023 19:51

ከበውቄ ጋር ምን አሟገተኝ?!

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(3 votes)

ደርሶ የሚያናግረን ምን ይሆን? ‹‹እንጃባህ!›› የሚል የአንባቢ ድምጽ ጎልቶ ይሰማኛል፡፡ የሰው ልጅ ባለፈ ዘመኑ ሁሉ ሲወጣና ሲወርድ እዚህ ደረሰ፡፡ እንደወጣም አልቀረ፤ እንደወረደም አላደረ፡፡ ይሄ ለምን ሆነ? ሰው ፊቱን እንጂ ኋላውን አይመኝምና፡፡ ኋላውን ዞር ብሎ ያያል፤ ነገር ግን ወደ ፊት ይራመዳል፡፡ ይህም የተፈጥሮ ህግ ስለሆነበት ከልቡ ተማክሮ  ይተገብረዋል፡፡ በዚህ መኻል አስበን እናድራለን የሚሉ ይነሱና ሐሳብን ከሐሳብ ያፋጫሉ፡፡ እንደ ፑቲን አረር መተኮስ ቢቸግራቸው፣ እንደ ትራምፕ ‹ምላስ›ን የሚከልላቸው የለምና!
ከሰሞኑ ከበውቀቱ ስዩም ጋር ተጨዋወትነ! በዐይነ ሥጋ ከተገናኘን አመታት አልፈው ነበርና የቆጥ የባጡን ለማውራት ብንዳዳም፣ ትልቁን ጊዜ የያዘው ነገረ ቧልትና ነገረ ትህርምት ነበር፡፡ ቧልት ያው ቧልት ነውና ቃሉን መፍታት ያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ‹‹ትህርምት›› ግን ለብዙኃኑ ባእድ ቃል ይመስለኛል፡፡ በቀላሉ ለመበየን ያህል የገብጋባነት ተቃራኒ የሆነ ቃል ነው፡፡ አዲያ ሁለቱን ቃላት (እዚህ ጋ ጽንሰ ሐሳቦች ምን አመጣቸው?)
ነፍሳቸውን ይማርና መንግስቱ ለማ፣ ቧልት ይወዱ ነበር አሉ፡፡ ጽሁፋቸው፣ ንግግራቸው፣ ኧረ እንዲያውም ሁለ ነገራቸው ለቧልት ያደላ ነበር፡፡ (ስማቸውን ለመጥቀስ ያላስፈቀድኋቸው አንድ ፕሮፌሰሬ እንደነገሩን)፤ በአብዮቱ ዘመን አብዮተኛ ግጥም እንዲገጥሙ በፖለቲከኞች ይታዘዛሉ፡፡ መንጌ ለመንጌ ይተያያል እንደባለጌ ሆነና ነገሩ፣ የአለቃ ለማ ልጅ ሆዬ፤ ‹‹እስቲ ስለአብዮቱ የመጣልኝን ግጥም እዚሁ ልበልላችሁ›› ይሉና (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንደኛው ግቢ ውስጥ ብዙ ‹‹ምሁራን›› እና ካድሬዎች አፋቸውን ከፍተው ሲጠብቁ)፤ ወደ መድረክ ይወጡና ጉሮሯቸውን ይጠራርጋሉ፡፡
ከዚያም የአለቃ ለማ ልጅ፣ ታዳሚዎቹ፣ ግጥሙን ለመስማት ተነሳሽነት በማሳየታቸው፣ ምሥጋና ያቀርቡና፣ግጥማቸውን ማንበብ ይጀምራሉ ‹‹እህህህህ  ኡሁሁሂሂሂ  ኡሁሁሁሁ ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ››ይሉና፤ ቀጥለውም፤ ‹‹ለጊዜው የመጣልኝ አብዮተኛ ግጥም ይሄው ነው›› በማለት ከመድረክ ይወርዳሉ፡፡  
የጋሽ መንግስቱ ተማሪዎች ብዙዎቹ በህይወት አሉ፡፡ ይሄንን መሰሉን የገጣሚውን ገድል ያወሩልን ይሆናል፡፡ ነገር ግን መንግስቱን ያህል የቅኔ ሊቅ፣ እንዲህ ባለው ቧልት ማስታወስ አያሰቅቅም? ልክ እንዲህ ነው በውቄ ላይ ያገመጥሁበት፡፡
አዲያ ትህርምትን ለምን አነሳኸው? ቀጥሎ የምጠየቀው ቁምነገር ይመስለኛል፡፡ ትህርምት አሳቢያኑ፣ ጠቢባኑ፣ ልሂቃኑ ለትውልድ ብለው የሚከፍሉት መስዋዕትነት ነው፡፡ ስለ ነገ ብለው ዛሬአቸውን የሚሰውበት የጠባይ ትሩፋት ነው፡፡ የመንግስቱን ዘመነኛ ጸጋዬን ለዚህ አስረጅ አድርጌ ላንሳ፡፡ (ጸጋዬን ጻድቅ፤ መንግስቱን ኃጥእ ማድረጌ እንዳልሆነ ማብራራት ይኖርብኝ ይሆን?)  ሚካኤል ሽፈራው ስለ ጸጋዬ ትህርምት እንዲህ ይላል፤
‹‹ ጸጋዬ ….. በግጥሞቹና በቴአትሮቹ ውስጥ የምንሰማቸው የንስሐ ድምጾች ናቸው፡፡ ለዚያውም በዚህ ግጥም ንስሐው ስለ ትውልዱ የተገባ ንስሐ እንጂ እርሱ ራሱ በቧልትና ባረቂ ግሳት የሚወቀስ ሆኖ አይመስለኝም፡፡ እንደዚያም ሆኖ እንደ ስብሀት ያሉትን የዚያ ትውልድ ሽንፈቶች፣ ከራሱ ቀላቅሎ፣ በየጊዜው በራስ ወቀሳ ንስሀ ድምጽ ማንሳቱ ዘወትር የተለመደ ነው››
 ሚካኤል ስለ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር ሊል የፈለገውን ነገር ማሳየት አይደለም ዓላማዬ፡፡ ነገር ግን ‹‹ስብሀትን የመሰሉ የትውልድ ሰነፎች›› ባሉበት ዓለም ውስጥ ‹‹ጸጋዬን የመሰሉ ትውልድ ወክለው ንስሐ የሚገቡ›› አሳቢያን መኖር እንዳለባቸው ለመጠቆም ነው፡፡
ትህርምት ይሄው ነው፡፡ ከትውልድ ዝንፈት ራስን ማቀብ፣ ከትውልድ ዝቅጠት ራስን ማሻገር፣ ከትውልድ ክሽፈት ራስን ማቀብ፤ ሲልም ለከሸፈው፣ ለዘቀጠውና ለተዛነፈው ትውልድ ሃላፊነትን ወስዶ ንስሐ መግባት፤ እንደ ጸጋዬ የንስሐ መዝሙርን ማንጎራጎር፡፡ እኔ እንዲህ አምናለሁ፡፡ (ስድስት እንቁጣጣሽን ቀድሞኝ ቢያከብርም) በውቄ የኔን ትውልድ የሚወክል ደራሲ ነው፡፡ በውቄ ይሄንን ትውልድ የማሻገር ኃላፊነት ያለበት ብዕረኛ ነው፡፡  በውቄ ይሄንን ትውልድ ከዝንፈት መታደግ ያለበት ጭሮ አዳሪ ነው፡፡ በውቄ ይሄንን ትውልድ ከክሽፈት ጎዳና አውጥቶ የማራመድ አደራ ያለበት አሳቢ ነው፡፡ በውቄ የዚህን ትውልድ ሃጢአት ተሸክሞ ለንስሐ ማቀርቀር ያለበት የትውልድ ምሳሌ ነው፡፡ ለመሆኑ ይሄ ሁሉ የብሶት ሀተታ ከየት መጣ?
ከሰሞኑ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሯሯጥ አንድ አጭር ቪዲዮ አየሁ፡፡  ደረጀ ኃይሌ የልጅ አባት፣ አንዲት ልጅ - ልጅ አንድም ልጅ የበውቄ አጋዥ እንዲሁም በውቄ አሸማጋይ ሆነው የሰሩት፡፡ ነገሩ ዘልማዳዊውን የትዳር ጥያቄ (ሽምግልናን) መሰረት ያደረገ ቧልት ነው፡፡ በውቄን እዚያ ላይ ማየት ግን አልተመቸኝም፤ ኧረ እንዲያውም አበሳጭቶኛል፡፡
ያለንበት ዘመን ከፖለቲከኛ እስከ ሃይማኖተኛ፣ ከነጋዴ እስከ ተማሪ፣ ከቤት አጋዥ እስከ ቤት እመቤት በራሱ በኑሮውና በሁለመናው ቀልድ ለመፍጠር የሚሞክር ‹‹ቧልተኛ›› እየሆነ ነው፡፡ ይሁን! በውቄ የማይፈቅዳት መንግስቱ ለማ የሚፈቅዷት አንዲት አጠራር አለች፡፡ ‹‹መደዴ›› የምትባል፡፡
 ዘመንና ድንበር ከማይከልሉት ማኅበረሰባዊ እውነታ ሁነኛ ‹ና› ሲሉት የሚመጣ፣ ‹ሂድ› ሲሉት የሚሄድ፣ ‹ፍረስ› ሲሉት የሚፈርስ መደዴ አለ፡፡ እንደ በውቄ አይነቱ አሳቢ፤ ለዚህ መደዴ ማፌዥያ  የዕለት ‹‹ምግብ›› ከመስጠት ይልቅ  ከዚህ መደዴ መሃል ያሉ ምርጦችን አስከትሎ፣ በእውቀትና በትጋት ወደፊት መጓዝ ነው ያለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
እና አበሳጨኝ! በውቄ የሰራው የቧልት ጭውውት አበሳጨኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ተነጋገርን እላችኋለሁ፡፡ ነገር ግን እስካሁን የተንደረደርኩበት ጉዳይ ትልቅ ፍልስፍናዊ ሙግትን የሚቀሰቅስ ነው፡፡
ፈረንጆቹ ‘art to its own sake or art to purpose’   እያሉ ሲሟገቱበት እንደነበረው ዓይነት ማለት ነው፡፡ ሳምንት እንቀጥልበት፤ በተወደደ ወረቀት ከዚህ በላይ መጻፍ አያዋጣም፡፡ ያሰንብተን!

Read 2438 times