Wednesday, 05 April 2023 19:03

ግዕዝ ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
• በአንድ ወር 500 ሚ. ብር ለማሰባሰብ ታቅዷል
በምስረታ ላይ የሚገኘው ግዕዝ ባንክ አክሲዮን ማህበር፤ ዳግም የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩን አስታወቀ።
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከመላው ኢትዮጵያና ከዳያስፖራው የ500 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ በማሰባሰብና የሚፈለገውን የካፒታል መጠን በማሟላት በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት ታቅዷል ተብሏል፡፡
የባንኩ አደራጅና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በዛሬው ዕለት ወጋገን ባንክ አንደኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ቢሮአቸው በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ግዕዝ ባንክ ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለምስረታ ሂደት የሚያበቃውን የአክሲዮን ሽያጭ ማከናወን መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
ለባንኩ ምሥረታ የሚያስፈልገውን የካፒታል መጠን ለማሟላት ጥቂት ሲቀራቸው ግን በአገሪቱ ላይ በተፈጠረው የሰላምና መረጋጋት ችግር ሳቢያ ከእንቅስቃሴያቸው ተግተው መቆየታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ፡
በህዳር 2013 ዓ.ም የአክሲዮን ሽያጭ እንደሚያበቃም ለሚዲያዎች አስታውቀው እንደነበር ያስታወሱት የኮሚቴው አባላት፤ ሆኖም በተፈጠረው ድንገተኛ ችግር ሳቢያ ያቀዱትን ሳያሳኩ እስካሁን መዘግየታቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን በአገሪቱ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ዳግም የአክሲዮን ሽያጭ መጀመራቸውን ነው፣ የአደራጅ ኮሚቴው አባላት ያስታወቁት፡፡
በምስረታ ሂደቱ ላይ በመሳተፍ የባንኩ መስራች ለመሆን ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶችም፤ ከዛሬ ጀምሮ በመላ አገሪቱ ባሉ ባንኮች በተከፈቱ የዝግና የአገልግሎት ሂሳብ ቁጥሮች፣ የግዕዝ ባንክ አ.ማ የመመስረቻ አክሲዮን ግዢን ከብር 50ሺ ጀምሮ ማከናወን እንደሚችሉ ተገልጿል።
የመሥራች አክሲዮን ሽያጩ ቀድሞ እንደነበረው የአንድ አክሲዮን መጠን 1ሺ ብር ሲሆን፤ መሥራች አባል ለመሆንም 50 አክሲዮኖችንና ከዚያ በላይ መግዛት እንደሚያስፈልግ ታውቋል። የመሥራች አባል ከፍተኛው የአክሲዮን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ብር ነው ተብሏል።
ዳያስፖራዎችን በተመለከተ እንደተለመደው፣ አክሲዮኖችን ባሉበት ሆነው፣ በሚኖሩበት አገር የመገበያያ ገንዘብ መግዛት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
የአደራጅና አስተባባሪ ኮሚቴው አባላት፤በአገሪቱ ላይ ተከስቶ በነበረው የሰላም ችግር ምክንያት የአክሲዮን ሽያጫቸውን አቋርጠው በነበረበት ወቅት፣ ደንበኞች ላሳዩት ትዕግስትና ድጋፍ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 2708 times