Saturday, 01 April 2023 20:37

ለመጀመሪያ ጊዜ

Written by  ደራሲ-ኦምራን ሚኻኤል ኢቫኖቭ ትርጉም- ዮናስ ታረቀኝ
Rate this item
(0 votes)

(ኦምራን ሚኻኤል ኢቫኖቭ፤ ከ1900- 1986 የኖረ ፈላስፋና መምህር የነበረ፣ ትውልዱ ቡልጋሪያ የሆነና ከ1937 ጀምሮ ፈረንሳይ የኖረ ነው፡፡ በስራዎቹ በዋናነት የሚያነሳው ሰዎችንና ለፍፁምነት የሚደረግ ጥረትን ነው፡፡ ይህንኑ መሰረታዊ ጥያቄ ታዲያ በሚያስገርም መልኩ ነው ለመመለስ የሚሞክረው፡፡ አገላለፁ የሚያነሳቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በተግባር ለመሞከር እንድንደፍር የሚያደርጉ ናቸው፡፡ )
           
      ብዙ ሰዎች ሕይወት ተደጋጋሚና ስሜት የለሽ ይሆንባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ስለ እውነታ ያላቸው መረዳት ጠባብና ጥራዝ ነጠቅ በመሆኑ ነው፡፡ ተፈጥሮንና ነገሮችን የሚመዝኑበት መንገድ ከውጪያዊው ተፅእኖ በመነሳት በመሆኑና፣ ይህም ለእለት ተእለት ኑሮ በቂ ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡  
እስቲ ወንዶችና ሴቶች የሚተያዩበትን አጠቃላይ ሁኔታና ፀባይ እንመልከት፡፡ ለጥቂት ጊዜያት ከተዋወቁ በኋላ እርስ በእርሳቸው ከዚህ ውጪ ሌላ ስለ እሱ ወይም ስለ እሷ ምንም አዲስ ነገር የለም ብለው ይደመድማሉ፡፡ እውነትም በዚህ ምክንያት ምንም አዲስ ነገር አያገኙም፤ ይሰለቻቻሉ፤ የራሱ ጉዳይ ብለው ይቀመጣሉ፡፡ ግንኙነታቸው የሚደጋገም ታሪክ ይሆንባቸዋል፡፡ ይራራቃሉ፡፡ ይለያያሉ፡፡ ይህ የሆነው ከሰው ልጆች ገፅታ -ነፍስና መንፈስ- በተቃራኒ መቆማቸው ግልፅ ስላልሆነላቸው ነው፡፡ ከዚህ የከፋው ነገር የሌላ ሰው ፀባይ ሊያስደንቃቸው የማይችል፤ በዚህ ረገድ እራሳቸውን ልምድ ያላቸው አድርገው መመልከታቸው ነው፡፡ ይህም ክብራቸውን ከፍ ያደርገዋል ብለው ይገምታሉ፡፡ ምናልባትም ክብራቸው በውስጣቸው እንዳለው እውርነት እየፋፋ ይሄድ ይሆናል፡፡ ድርቅ ይላሉ፤ የህይወትን ፍሰት ይቆርጡታል፡፡ ሰዎች ሕይወት ያላቸው ፍጡሮች ናቸው፡፡ ተፈጥሮም በሕይወት የተሞላች ናት፡፡ ከዚህ ሕይወት ጋር ለመነካካት ግን የሰው ልጅ በውስጡ ይህንን የመረዳት ችሎታ ማዳበር ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ በቀላል ዘዴ መሆን የሚችል ነገር ነው፡፡  
እስቲ ለምሳሌ በእዚህ ልምምድ ሞክሩት፡፡ ጠዋት ስትነሱ ሰማዩንና ፀሐይን ለመመልከት ሞክሩ፡፡  በውስጣችሁም ልክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳያችሁት አድርጋችሁ ስሜታችሁን አነሳሱት፡፡  በዚህን ጊዜ እስከ ዛሬ ስትሸሹትና ጠንካራ ግድግዳ ስትገነቡለት የነበረው፤ረቂቅ የሆነውን አዲስ የህይወት ክፍል ሙሉ በሙሉ ታገኙታላችሁ፡፡ ከዚህ ግድግዳ እራሳችሁን ማራቅ እስካልቻላችሁ ጊዜ ድረስ የነገሮችን እውነተኛነት በፍፁም ማመዛዘን መረዳት አትችሉም፡፡
እውነተኛ የማመዛዘን ችሎታ የማያቋርጥ ምንጭ ማለት ነው፡፡ ያለማቋረጥ አዲስ የሚሆንና የሚታደስ፡፡ በምትሃታዊ እጅ ዳግም ነፍስ የሚዘራ፡፡ እውነተኛ ብልህነት፣ እውነተኛ የማመዛዘን ችሎታ ማለቂያ በሌለው ሐሴት ነፍስን መሙላት ነው፡፡ ይህን ከተፈጥሮ ጋር በመገናኘት ብቻ ማድረግ አይበቃችሁም፤ ከሰዎች ጋር ጭምር እንጂ፡፡ በእዚህ ያልተጠበቁ ግኝቶችን ታገኛላችሁ፡፡ ለሌሎች ሰዎችም ይበልጥ ሩህሩህና አስደሳች ሆናችሁ ትገኛላችሁ፡፡  
ዋናው ነገር ከሕይወት ጋር ግንኙነት ማድረጉ ነው፡፡ ሁሉንም ስለ መሬትና ሰማይ፤ ስለ ድንጋይ፤ ስለ ተክሎች፤ ስለ እንስሳት፤ ስለ ክዋክብት፤ ስለ ሰዎች ከነቋንቋቸው፤ ከነባህላቸውና ጠቅላላ ስለ ልዩ ልዩ አኗኗራቸው ብታውቁም እንኳን፤ በዚያ ውስጥ የሚሽከረከሩትን ለስላሳ የህይወት ፍሰቶችን ማገናኘት እስካልተማራችሁ ድረስ፤ መቼም ቢሆን የሆነ እክል፤ መከፋት የመሰልቸት ስሜት አያጣችሁም፡፡  
‹‹ከእኛ የሚጠበቀው ነገር ከባድ ነው፡፡ እንዴት ማድረግ እንዳለብን አናውቅም!›› ትላላችሁ፡፡ በፍፁም ከባድ አይደለም፡፡ አንድ ቀላል ዘዴ አሳያችኋለሁ፡፡ ነገሮችንና ተፈጥሮን ልክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳያችኋቸው አድርጋችሁ ውሰዷቸው፡፡ የዚህ ዘዴ ጠቀሜታ ፈጣሪዎች እንድንሆን ማድረጉና ይህንን ችሎታ ማዳበር ለህይወታችን ትርጉም መስጠቱ ነው፡፡  
ሙዚቀኞች ያንኑ ሙዚቃ፤ ተዋናዮች ያንኑ ትያትር መቶ ጊዜ እያቀረቡ እንዴት ነው በየጊዜው ታዳሚዎቻቸው ላይ ጠንካራ ስሜት መፍጠር የሚችሉት? ምክንያቱም በየጊዜው ልክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚጫወቱት አድርገው የማቅረብ ችሎታ ስላላቸው ነው፡፡ የኪነ ጥበብ ሰዎች ድርጊቱን ፈጻሚዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ‹ፈጣሪዎችም› ጭምር ናቸው፡፡ ለሥራዎቻቸው በየጊዜው አዲስ ሕይወት የሚሰጡ፡፡ እናንተስ ለምን እንዲህ አታደርጉም? ኪነ ጥበብ ለምን ለአርቲስቶች ብቻ ይተዋል? እናንተም በማንኛውም ጊዜ ፈጣሪ መሆን ትችላላችሁ፡፡ በምታደርጉት፤ በምታዩት ወይም በምትሰሙት ላይ ሕይወትን መዝራት… ዋናው ነገር ልክ ለመጀመሪያ ጊዜ የምታደርጉት እንደሆነ አድርጋችሁ መውሰድ ነው፡፡  
ዛሬ ጥቂት ሰዎች ብቻ የደረሱበትንና እየተጠቀሙበት ያለውን አንድ ትልቅ ምስጢር ግልፅ አደርግላችኋለሁ፡፡ ለረዥም ጊዜ ደጋግመው ያንኑ ስለሚያደርጉ ሰዎች፡፡ ልክ እንደ አውቶማቲክ፡፡ ይበላሉ፤ ይጠጣሉ፤ ይተኛሉ፤ የእግር ጉዞ ያደርጋሉ ወዘተ፡፡ ግን ያንኑ ነው በዚያው ሰዓት፤ በዚያው ስሜት፡፡ ስለዚህ ደስተኞች አይደሉም፡፡ ሆን ብዬ በምጠቀመው በዚህ ዘዴ ምን ያላገኘሁት አዲስ ነገር አለ፡፡ ሁሉንም ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደማደርገው አድርጌ በማሰብ! በዚህ አይነት ሁሉም ነገር አዲስ ይሆንብኛል፡፡ ይህም እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም በእውነት ውስጥ ምንም ነገር ሁልጊዜ አንድ አይነት ሆኖ አታዩም፡፡ ተፈጥሮና ነገሮች የሚኖሩ ናቸው፡፡ በየቀኑ አዳዲስ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ፡፡ አንድን ሐብል፤ ቀለበት ወይም አምባር ብንወስድ፣ በየቀኑ ትላንት ምሽት ከነበረው የተለየ ቅርፅና ይዘት ይይዛል፡፡ ይህንን የመረዳት ስሜት ቢኖራችሁ ኖሮ በውስጡ ባሉት ኤሌክትሮኖች እንቅስቃሴ የተነሳ ልዩነቱ ይታወቃችሁ ነበር፡፡ ይህም ቁሶቹ በየጊዜው አዲስ ከሆኑት የኮስሞስ ፍሰቶች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በሚያሳውቀው እውነታ ይገለፃል፡፡ ይህ ስለማይሰማችሁ ግን ሁሉም ነገር እንቅስቃሴ ላይ ነው፤ ይለዋወጣል ብላችሁ አንዳታምኑ አድርጓችኋል፡፡  
እውነታው ግን ምንም ነገር ሁልጊዜ ባለበት እንዳለ አለመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ፀሐይ ጠዋት ጠዋት ስትወጣ ሁልጊዜም አዲስ ናት፡፡ ይህንን የስነ ክዋክብት ባለሙያዎች ሊያረጋግጡላችሁ ይችላሉ፡፡ መሬት ላይ ሆነን በአይናችን በማየት ብቻ፣ ይህንን ለውጥ መመልከት አንችልም፡፡ ለመሳሪያዎቻቸው ምስጋና ይግባውና የስነ ክዋክብት ተመራማሪዎች፣ ፀሐይ ላይ ያለውን የሚርገበገብ ሕይወት ይመለከታሉ፡፡ ፍሰቶችን፤ ፀሐይን የሚያደምቁ ጋሶችን፤ ፍንዳታዎችን፤… ፀሐይ ላይ ለውጦች የሚካሄዱ ከሆነ ስለምን በፀሐይ ሲስተም ውስጥ ባሉት ላይ በሙሉ፣ ሰዎች ላይ፤ እንሰሳት ላይ፤ ተክሎች ላይ፤ ድንጋዮችና ብረቶች ላይ … ተፅእኖ አያሳድርም?  
ስለዚህ በየጊዜው ለሕይወታችሁ አዲስ ስሜት የሚሰጥ እውነታን ማግኘት የምትፈልጉ ከሆነ፤ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ ሁሉንም ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳገኛችሁት አድርጋችሁ ውሰዱት፡፡ በየጠዋቱ ከእንቅልፋችሁ ስትነቁ፤ ዓለምን ለመጀመሪያ ጊዜ ልታገኟት እንደምትችሉ አድርጋችሁ፡፡ ቁራሽ ዳቦ ስትበሉ፤ እሳቱን፤ ውሃውን፤ አንድን ዛፍ ወይም ተራራን ስትመለከቱ እንደዚያው፡፡ ሙዚቃ ስታዳምጡ፤ ከቤተሰቦቻችሁ፤ ከጓደኞቻችሁ ጋር ስትገናኙ፤ልክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተገናኛችሁ አድርጋችሁ… እናም በየቀኑ መኖራችሁ የተሟላና አስደሳች መሆኑ ይሰማችኋል፡፡Read 1253 times