Saturday, 25 March 2023 18:35

ቦሌ 5150 ልዩ የዱላ ቅብብሎሽ ሩጫ ተካሄደ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲጨረስ ለማነሳሳት ነው

      ባለፈው ሰሞን ቦሌ 5150  በሚል ስያሜ  የዱላ ቅብብሎሽ ሩጫ ተካሂዷል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከፍፃሜ እንዲደርስ የሚያነሳሳ   አመቺ መድረክ ሆኖ ማለፉን አዘጋጆቹ ለስፖርት አድማስ ገልፀዋል፡፡ የዱላ ቅብብሎሽ ሩጫው  የተለያዩ እድሜና ፆታ ያላቸው ተሳታፊዎች መሮጣቸው በጎዳና ላይ ከሚካሄዱ መሰል ሩጫዎች የተለየ አድርጎታል።  በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙ  11 ወረዳዎች እያንዳንዳቸው 52 ተሳታፊዎች በማስመዘገብ ከ572 በላይ ስፖርተኞች ተወዳድረውበታል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የተዘጋጀው ሩጫ  ከወጣቶች ስፖርት አካዳሚ  በመነሳት 24 ስታድዬም ላይ መጨረሻውን አድርጓል፡፡የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ታደሰ እንደገለፁት በዱላ ቅብብሎሽ ሩጫው ከስፖርት እንቅሰቃሴ ባሻገር  በልማት እንቅስቃሴ የትውልድ ቅብብሎሽ አስፈላጊ መሆኑን ግንዛቤ መፈጠሩን ጠቅሰው በየዓመቱ እያሻሻልነው እንቀጥላለን ብለዋል።
ከውድድሩ ጋር በማያያዝ የቦንድ ግዢዎች  የተከናወኑ ሲሆን አትሌቲክስ ስፖርትን ወደ ገቢ ማሠባሠብ እንቅስቃሴው በመሣብ ቦሌ ክፍለከተማ ፈርቀዳጅ ሊሆን በቅቷል። ባለፋት 7 ወራት በቦሌ ክፍለከተማ ለግድቡ ግንባታ  100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ   ከ115 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱንም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ  የሚታወቅ ሲሆን በመላው  ኢትዮጵያ የሀብት ማሰባሰብ መርሐ ግብሮች በተለያዩ  ተግባራት መከናወናቸውን ቀጥለዋል፡፡ በቦሌ 5150 የዱላ ቅብብሎሽ ሩጫ ላይ 5150 ሜትር እንዲሮጥ የተወሠነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚያመነጨውን የኃይል መጠን ለማንፀባረቅ ነው። የግድቡ ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ  መጠናቀቁ ታውቋል።





Read 760 times