Saturday, 25 March 2023 17:35

አዲሱ የትግራይ መስተዳድር በሥልጣን ዘመናቸው ለመሥራት ያቀዱትን ተናገሩ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

-”የትግራይ መሬት በአስቸኳይ ወደነበረበት መመለስ አለበት”
        - የኤርትራ ወታደር አሁንም በትግራይ መሬት ላይ አለ ብለዋል
           
       አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት በሰጡት የመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ “በክልሉ ዲሞክራሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ለማካሄድ እሰራለሁ” ብለዋል።
ህወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ ውስጥ ስሙ ከተነሳ በኋላ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሩ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የተሸሙት አቶ ጌታቸው ረዳ፤  ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚቆይበት ጊዜ አጭር በመሆኑ የክልሉን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ኃላፊነቶችን እንደሚሸከም ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው አክለውም፤ የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ተልዕኮዎች አንዱ መሆኑን አመልክተው፣ የሰላም ሂደቱ በአጭርና በረጅም ጊዜ ሰላምን በማጠናከር፣ የጦርነቱ መንስኤዎችን በመፍታት የክልሉን ዘላቂ አገራዊ ጥቅምና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ያረጋግጣልም ብለዋል። በተጨማሪም የትግራይ ክልል የግዛት ሁኔታም በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት፣ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ መቀመጡን አቶ ጌታቸው አስታውሰዋል።
“ምዕራብ ትግራይ፣ ደቡብ ትግራይ፣ የሰሜን ምዕራብ ትግራይ አካል የሆነው ጸለምቲ ወደ ነበሩበት የቀድሞ ቦታቸው አለመመለሳቸው ብቻ ሳይሆን እየደረሰ ያለው መፈናቀልና የዘር ማጥፋት አሁንም በግልጽ እየቀጠለ ነው። ከእነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በአስቸኳይ ወደ ቤታቸው መመለስ አለባቸው። ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት፣ የትግራይ መሬት የትግራይ ነው” ብለዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች ዙርያ የሚነሱ ጥያቄዎችም በሰላማዊ እና ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ መፈታት እንዳለባቸው በመግለጽ፣ “በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል ስለማይሆን፣ የአማራ የፀጥታ ኃይሎች ይህንን ተረድተው የተጀመረውን ሰላም የሚያደፈርሱ ድርጊቶችን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ አሳስባለሁ” ብለዋል።
ከትግራይ እንዲወጣ ግፊት ሲደረግበት የነበረው የኤርትራ ጦር ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ከተለያዩ የሰሜን ምዕራብና መካከለኛ ትግራይ አካባቢዎች ለቆ መውጣቱ ሲገለጽ ቢቆይም፤ ሆኖም አሁንም የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ከሆነው መሬት [ከአብዛኛው የትግራይ አካባቢዎች] አልወጣም ሲሉ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
ጦርነቱ ወቅት ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ጌታቸው  በጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን መልሶ ለማቋቋምና በክልሉ ኢኮኖሚያዊ ተሃድሶ ለመጀመር ፖለቲካዊ እና ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን ለማምጣት ቃል ገብተዋል።



Read 2548 times