Saturday, 25 March 2023 17:15

ለ3 ዓመት የሚዘልቀው “ውባንቺ ፕሮጀክት” በይፋ ተጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ፋውንዴሽኑ ከ200 ሚ. ብር በላይ የተመደበለት ፕሮጀክት ከመንግሥት ተቋማት ጋር ተፈራርሟል


      ባለፉት ዓመታት ወላጅና ተንከባካቢ የሌላቸው እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ያላቸው ታዳጊዎች ላይ አተኩሮ ሲሰራ የቆየው “ብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን”፤ ለ3 ዓመታት እንደሚዘልቅ የተነገረለትን “ውባንቺ ፕሮጀክት” ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በስካይ ላይት ሆቴል በይፋ አስጀምሯል።
ፋውንዴሽኑ፤ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር ጠቅላላ ባጀቱ ከ200 ሚ. ብር በላይ የሆነ የሦስት ዓመታት ፕሮጀክት መፈራረሙ ታውቋል፡፡
 ፕሮጀክቱ፤ በልጅነቷ ከክፍለ ሃገር ወደ አዲስ አበባ መጥታ፣ ከ11-15 ዓመት ዕድሜዋ ድረስ በህፃናት ማሳደጊያ ተቋም ውስጥ ባደገችውና በ17 ዓመት ዕድሜዋ ሊደፍራት በሞከረ አንድ ሰካራም በተገደለችው ውባንቺ ስም ነው የተሰየመው፤ታዳጊዋን ለመዘከር፡፡
“ውባንቺ ፕሮጀክት”፤ ሌሎች ወላጅና ተንከባካቢ የሌላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች፣ የውባንቺ ዓይነት ዕጣፈንታ እንዳይገጥማቸው ለመታደግና የተሻለ እንክብካቤና ደህንነት አግኝተው እንዲያድጉ ታልሞ የተቀረጸ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ከትላንት በስቲያ ፕሮጀክቱን ለማስተዋወቅ በተካሄደው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሜሮን አራጋው-  ባደረጉት ንግግር፤ “ሁሉም ህጻናት በዕድሜያቸው መጀመሪያ ላይ የተሻለ እንክብካቤና ክትትል ያገኙ ዘንድ ያገኙ ዘንድ እንደ “ብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን” ያሉ የግል ተቋማትን ሰፊ ተሳትፎ እንደሚፈልግ ጠቁመው፤ ፋውንዴሽኑ በዚህ ረገድ መንግሥትን እያገዘና የመንግሥትን ሃላፊነት እየተወጣ በመሆኑ ምስጋና ሊቸረው  ይገባዋል ብለዋል፡፡
እስካሁንም ቢሮአቸው ከፋውንዴሽኑ ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት ሃላፊዋ፤ ወደፊትም በተመሳሳይ ሁኔታ ተቋሙ ወላጅና ተንከባካቢ የሌላቸው ታዳጊዎች ላይ አተኩሮ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ድጋፍና እገዛ  ለማድረግ  ቃል ገብተዋል፡፡  
በመርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ “ህጻናቶቻችንን በጤናማና በምቹ ሁኔታ ማሳደግ ሃላፊነታችን ቢሆንም፣ይህንን ሳያገኙ የውባንቺ ዓይነት ዕጣፈንታ የሚገጥማቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት እንደሆኑ በመጠቆም፤ከዚህ አንጻር ፋውንዴሽኑ እያከናወናቸው ያሉትን ሥራዎች አመስግነዋል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤታቸው፤ ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ ጋር በአንድነትና በትብብር ለመሥራት ፍላጎትና ፍቃደኝነት እንዳለውም ሚኒስትሯ  አስታውቀዋል፡፡
“ብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን” ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል፣ወላጅና ተንከባካቢ የሌላቸውን እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ታዳጊዎች ከማህበረሰቡ ነጥሎ ከማሳደግ ይልቅ የቤተሰብ ይዘት ያላቸውን (ፋሚሊ ሃውስ) ከፍቶ አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ማኖር፣ማሳደግና ማስተዳደር በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
ተቋሙ በተጨማሪም፣ በመንግሥት ሥር በሚተዳደሩ ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ ለሚኖሩ በርካታ ቁጥር ላላቸው ታዳጊዎች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ከማመቻቸትና ወጪ ከመሸፈን ባሻገር ሙሉ የህክምና የአልባሳትና ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ ድጋፎችን እንደሚሰጥ እንዲሁም የትምህርት- ጥናት አገልግሎትና የሥነልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚያደርግም ጠቁሟል፡፡
በዚህ መልኩ አጠቃላይ ድጋፍ በማድረግም፣ ዕድሜያቸው የደረሰ ታዳጊና ወጣቶች ራሳቸውን ችለው ከተቋሙ እንዲወጡና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ፋውንዴሽኑ ይገልጻል፡፡

Read 1705 times