Saturday, 18 March 2023 20:20

ቱሪዝም ዘርፉ እንዳያንሰራራ የግብር ማነቆ ተደቅኖበታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ኢትዮጵያ እንዳላት የታሪክ የባህልና የተፈጥሮ ጸጋ፤ የቱሪዝም ዘርፉ ተጠናክሮ ለአገሪቱ የሚገባትን ያህል ጥቅም እያስገኘ አይደለም የሚለው ሃሳብ ሲወተወትበት የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ ምንም እንኳን አገሪቱ እንዳላት አቅም ያህል ባይሆንም እስከ 2019 እ.ኤ.አ. ድረስ የቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ እመርታን እያሳየ ነበር፡፡
በ2019 እ.ኤ.አ. ከ800 ሺህ በላይ ጎብኚዎችን አገሪቱ ተቀብላ አስተናግዳለች፡፡ ይህም በ2000 እ.ኤ.አ. ከነበረው ከ136 ሺህ የጎብኚዎች ቁጥር አንፃር እጅጉን የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከ2019 እ.ኤ.አ. በፊት ዘርፉ ከአምስት በመቶ በላይ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያበረከተ ቆይቷል፡፡
ይህ ሁሉ የዘርፉ ተስፋ ከ2019/20 እ.ኤ.አ. በኋላ ጨላለመ፡፡ የኮሮና ቫይረስ አለም ላይ ከደቀነው አደጋ የከፋ የሚባለው የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያደረሰው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሆቴሎች ተዘጉ፤ ሰራተኞቻቸው ተበተኑ፤ አንዳንድ ሆቴሎች ወደ ጤና ማዕከልነት እስከመቀየር ሁሉ ደረሱ፤ የአስጎብኚ ድርጅቶች የሥራ ዘርፋቸውን እንዲቀይሩ ተገደዱ! ውርጅብኙ በአለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ተብሎም ተመዘገበ፡፡
የኮሮና ቫይረስ የደቀነው ስጋት በአለም ላይ ጋብ እያለ ቢመጣም፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ግን ለብቻው ሌላ ተግዳሮት ተጋርጦበት ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከ2013 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በተለያዩ ፖለቲካዊ ውጥንቅጦች ውስጥ ማለፏ ይህ ውጥንቅጥ በአጠቃላይ ለንግድ እንቅስቃሴው በተለይ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፉ ጉሮሮ ላይ በመቆም አላላውስ ብሎት እንደዘለቀ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው፡፡
የአገሪቱ የፖለቲካ ውጥንቅጥ በተለይ ደግሞ ባለፉት አራት አመታት አይነቱን ቅርጹንና ምክንያቱን እየቀያየረ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ተግዳሮት መሆኑን ቀጥሏል፡፡ አሁንም በ2020 እ.ኤ.አ. በሰሜን ኢትዮጵያ የፈነዳው ጦርነት  በአይነቱ ልዩ የሆነና ከባድ ማነቆን በዘርፉ ላይ ጥሎ ከርሟል፡፡ ይኸኛው ተግዳሮት የቱሪስት መስህብ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ጉዳት እስከ ማድረስና በዘርፉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት አገልግሎታቸውን አቁመው ሰራተኞቻቸውን እስኪበትኑ ያደረሰ ከባድ ጊዜም ነበር፡፡
ምንም እንኳን የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉና እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች እስካሁንም እንደቀጠሉ ቢሆንም፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረው ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨቱ እንደተቀረው ኢኮኖሚ ዘርፉ ለቱሪዝም ዘርፉም እፎይታን መፍጠር ነበረበት፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ይኼ አልሆነም፡፡ በቅርቡም የመሆን ተስፋ አይታይበትም መንግስት የዜሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተጠቃሚ ብሎ በአዲስ ረቂቂ አዋጅ ላይ ካስቀመጣቸው ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ የማይገኝበት መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህ የፖሊሲ አቅጣጫ ትክክል እንዳልሆነ የዘርፉ ተዋናዮች ብዙ አመክንዮዎችን በማንሳት ይሞግታሉ፡፡
በቅድሚያ የአስጎብኚዎችና የሆቴል እንዲሁም መሰል እንቅስቃሴዎች በዘርፉ ውስጥ የተሰማሩትን የንግድ ተቋማት እጅግ ብዙ ወጪ የሚያስወጡ ቢሆንም ሁሉም እነዚህ ወጪዎች ግን በግብር ስርዐቱ አለመሸፈናቸው አንዱ ትልቁ ተግዳሮት መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
አንድ ሆቴል የምግብ አገልግሎቱን ለማቅረብ የሚገዛቸው ቁሳቁሶች በሙሉ ለማለት በሚያስችል ደረጃ፣ በደረሰኝ ተገዝተው በወጪ መልክ ከገቢዎች ጋር መወራረድ የሚችሉ አይደሉም፡፡ በተመሳሳይ መልኩም፤ አንድ አስጎብኚ ድርጅት አስጎብኚዎችን ይዞ ከአንድ የቱሪዝም ቦታ ወደ ሌላኛው ሲያዘዋውር የሚያወጣቸው የትራንስፖርት፤ የጉብኝት ቦታዎች ክፍያዎችና መሰል ወጪዎች ሁሉም ደረሰኝ ሊሰበሰብላቸው የሚችሉ ባለመሆናቸው እንደወጪ ተመዝግበው በገቢዎች ደረጃ ሊወራረዱ አይችሉም፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ በዘርፉ ውስጥ አገራቸውን በአለም ደረጃ ለማስተዋወቅና ለራሳቸውም ገቢ ለማግኘት ከአገር ውጪ የተለያዩ ክፍያዎችን በመፈጸም የተለያዩ ማስታወቂያዎችን ማሰራት፤ ከአገር ውጪ እይታን የሚጨምሩ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍና ለነዚህም እንቅስቃሴዎች ክፍያን መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድ ሆቴል፤ አሊያም የአስጎብኚ ድርጅት ከፍቶ ቁጭ ስለተባለ ብቻ ጎብኚዎች ይመጣሉ ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡
በቅድሚያ የትኞቹም እነዚህ ወጪዎችን እንዲያደርጉ የውጪ ምንዛሬ እንዲያገኙም ሆነ የክፍያ ስርዐቱን በማመቻቸት በኩል ከመንግስት የትኛውንም ድጋፍ ሳያገኙ በግል ጥረት እነዚህን ክፍያዎች በራሳቸው እየከፈሉ ጎብኚዎችን ወደ አገር ውስጥ ሲያመጡ ነው የኖሩት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የትኞቹም እነዚህ ወጪዎች በአገር ውስጥ እንደ ወጪ ተመዝግበው የሚወራረዱበት መንገድ አለመኖሩን ከግምት ውስጥ ያስገባ አይመስልም-አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ፡፡
አዲሱ የረቂቅ አዋጅ ከግምት ውስጥ ያላስገባቸው እውነታዎች በዚህም የሚያበቁ አይደሉም። ኢትዮጵያ ከኮሮና እና ከፖለቲካዊ አለመረጋጋቶቹ በፊት በአመት ከ800 ሺህ በላይ የሚሆኑ ጎብኚዎችን ያስተናገደችበት ወቅት ነበር፡፡ እነዚህ ጎብኚዎች ወደ አገር ቤት መጥተው ኢትዮጵያን እንዲገበኙ በማሳመኑ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ የሚጫወቱት እነዚህ አስጎብኚ ድርጅቶች ናቸው፡፡
በዚህ ሚናቸው ለራሳቸውና ለቀጠሯቸው ሰራተኞች የገቢ ምንጭ ከመሆን አልፈው ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የትኛውንም ያህል እያደገ ቢመጣም፣ አንድ ሊቀርፈው ያልቻለውና ህልውናውን እጅጉን እየተፈታተነ ያለው ተግዳሮት የውጪ ምንዛሬ እጥረት መሆኑ ይታወቃል፡፡
የውጪ ምንዛሬ እጥረት በአገር ውስጥ ተጠቃሚው ላይ ዋጋን ከማናሩ ባሻገር፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች በአጠቃላይ መካሄድ እንዳይችሉ እንቅፋት ሲሆን ማስተዋል የተለመደ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ገፋ ሲልም ለአንድ ሳምንት የሚሆን የውጪ ምንዛሬ ብቻ ሲቀራት የሞት ሽረት ጥረት እየተደረገ የኢኮኖሚውን ህይወት ማራዘም የተለመደ የመንግስት ተግባር ከሆነም ሰነባብቷል፡፡
እንዲህች ባለች አገር ውስጥ ለኢኮኖሚው አንድም ተጨማሪ ዶላር ሊያመጣ የሚችል ዘርፍ በምሉዕ አቅምና ፍላጎት መደገፍ አንድምታው በዘርፉ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ተቋማት አልፎ አገራዊ እንደሆነ መገመት ብዙም አዋቂ መሆንን አይጠይቅም፡፡
በአለም ላይ በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የንግድ ተቋማት ላይ ግብር ከምንጥል እነሱ ተበረታተው ከሚያመጡት የንግድ እንቅስቃሴ ብንጠቀም ይሻለናል ብለው በነዚህ ተቋማት ላይ ምንም ግብር ካለመጣል በጣም አናሳ ግብር እስከመጣል የሚደርስ ድጋፍን የሚያደርጉ በርካታ አገራት አሉ፡፡ አጅግ የሚያስገርመው ደግሞ እነዚህ አገራት እንደ ኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት እንኳን ያለባቸው አገራት አለመሆናቸው ነው፡፡
በእነዚህና በሌሎች በርካታ ምክኒያቶች የቱሪዝም ዘርፉን የተጨማሪ እሴት ታክስ ዜሮ ሊደረግላቸው ከታሰቡ ዘርፎች ዝርዝር ውስጥ አለማካተት እንድምታው ከዘርፉ አልፎ በአጠቃላይ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የቱሪዝም ዘርፉ ከኮሮና እና ከጦርነት እንዲሁም ግጭት ጠባሳዎች እንዲያገግም፤ አልፎ ተርፎም ለአገር በውጪ ምንዛሬ አምጪነት መሪ ሚናውን እንዲጫወት፣ የመንግስትን ከወትሮው የተለየ እርዳታ ይሻል፡፡
ኢትዮጵያ ዘመናዊ በሆነ መልኩ ከዘርፉ ሙሉ አቅሟን የሚመጥን ጥቅም ማግኘት እንድትችልና የቱሪዝም ዘርፉ ያንን ማድረግ ይችል ዘንድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ያሉበትን የግብር ማነቆዎች ለመፍታት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ምናልባትም ለአገሪቱ አለኝታ ሊሆን እንደሚችል የቱሪዝም ዘርፉ፣ ከእነ አካቴው አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ልብ ሊባል ይገባል፡፡


Read 1007 times