Saturday, 18 March 2023 20:11

ኢንፋንቲኖ የፊፋ ፕሬዚዳንት ሆነው ይቀጥላሉ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ከ33ኛው የዓለም ዋንጫ 11ቢ. ዶላር ገቢ ይጠበቃል

     ሰሞኑን 73ኛው የፊፋ ኮንግረስ በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ውስጥ ተካሂዷል። ስዊዘርላንዳዊው ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እስከ 2027 እኤአ ዓለምአቀፉን የእግርኳስ ማህበር በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ በሙሉ ድምጽ ተመርጠዋል። ጉባኤው ከ2,000 በላይ ተሳታፊዎች የነበሩት ሲሆን 211 የፊፋ አባል አገራት እና ሌሎች የእግር ኳስ ባለድርሻ አካላትን ማሰባሰቡ ታውቋል።
የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ጠቅላላ ጉባኤውን  ከ1998 ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ የሚያካሂድ ሲሆን የፕሬዚዳንት ምርጫ ለማከናወን በዓለም እግር ኳስ ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ ለመምከር የበጀትና የኢንቨስትመንት ውሳኔዎችን ለማሳለፍ መድረኩን ይጠቀመዋል።  ሩዋንዳ ጠቅላላ ጉባኤውና በማስተናገድ 4ኛው የአፍሪካ አገር ሆናለች። በ2005 ሞሮኮ፣ በ2010 ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በ2013 ሞሪሽየስ ጉባዔውን አስተናግደዋል።
በፖል ካጋሜ የሚመራው የሩዋንዳ  የእግር ኳስ አገራ አገሪቱን ወይ ትልቅ የስፖርት መናኻሪነት ለመቀየር ግንባር ቀደም ሆኗል። ከእግር ኳሱ ባሻገር በዓለም የባህር ዳርቻ ላይ መረብ ኳስ 20 አገራትን በሚያሳትፍ የትራያትሎን ሻምፒዮና፤ በአፍሪካ ቅርጫት ኳስ ሊግ አዘጋጅነት እየሰራች ነው። በ2025 እ.ኤ.አ ደግሞ  የዓለም ብስክሌት ሻምፒዮና ለማስተናገድ አመልክታለች። ዘኢስት አፍሪካን ስታንደርድ እንደዘገበው ሩዋንዳ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ከስፖርት ቱሪዝም እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ትጠብቃለች። በሌላ በኩል ከ73ኛው የፊፋ ኮንግረስ ጋር ተያይዞ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜና የሞሮኮው ንጉስ መሀመድ 5ኛ ለእግር ኳስ እድገት ባበረከቱት አስተዋጽኦ ልዩ የክብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ሞሮኮ ከወር በፊት የዓለም ክለቦች ዋንጫ በተሳካ ሁኔታ ማዘጋጀቷ የሚታወስ ሲሆን። በ2030 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ 24ኛውን የዓለም ዋንጫ ከፖርቱጋልና ከስፔን ጋር በጣምራ ለማዘጋጀት ማመልከቷን ለማወቅ ተችሏል።
በ73ኛው የፊፋ ኮንግረስ ላይ ትኩረት ካገኙ ዋንኛ አጀንዳዎች መካከል በ2026 የሚካሄደው የ23ኛው የዓለም ዋንጫ ገኝበታል። በ6 ሳምንታት ውስጥ 104 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካዱበት ይታወቃል። ሶስቱ የሰሜን አሜሪካ አገራ ከ23 በላይ ስታድየሞች አዘጋጅተዋል። 3 በካናዳ፣ 3 በሜክሲኮ እንዲሁም 17 አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር እስከ 2026 ዓለም ዋንጫ በሚያደርገው እንቅስቃሴ እስከ 14 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዱንም አስታውቋል።
ኳታር ያስተናገደችውን  22ኛው የዓለም ዋንጫ በአለም ዙሪያ ከ5 ቢሊዮን በላይ ድምር  ተመልካቾች በተለያዩ ሁኔታዎች መከታተላቸው፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች ደግሞ ኳታር ላይ በአካል ተገኝተው ግጥሚያዎችን መታደማቸው ከፍተኛ ስኬት ሆኖ በጉባዐየው ተደንቋል።
ከኳታር 2022 ጋር ተያይዞ ዓለምአቀፉ የእግርኳስ ማህበር ከ2019-2022 ባካሄደው የስራ ዘመን ከ7.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ  ማግኘቱም አዲስ ሪከርድ ሆኖ  ተመዝግቧል። በጉባዔው ላይም የፊፋ ጠንካራ የፋይናንስ እንቅስቃሴና ግልፅነት ውጤት  ነው ተብሏል።
ፊፋ ከዚህ ገቢው በእግር ኳስ ልማት ያዋለው ኢንቨስትመንት ሰባት እጥፍ እድገት ያሳየ ሲሆን ለሚከተሉት 3 ዓመታት እያንዳንዱ አባል ፌዴሬሽን በየዓመቱ እስከ 8 ሚሊዮን ዶላር የማግኘት መብት ይኖረዋል።
የፊፋ ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት በ2026 እኤአ ላይ 23ኛውን የዓለም ዋንጫ ለሚያስተናግዱት  ሶስት አገራት አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ  ዝግጅቱ እንዲጧጧፍ በየአቅጣጫው እንቅስቃሴ የሚደረግ ይሆናል። በተለይ አሜሪከና ሜክሲኮ  በኳታር 2022 ላይ የስታድየም መግቢያ ትኬቶችን በመግዛት የነበራቸው ተሳትፎ በሚያዘጋጁት የዓለም ዋንጫ በጎ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተወስቷል። ለ2026 የአለም ዋንጫ ፊፋ ለአዘጋጆቹ አገራት በሚደግፈው የመስተንግዶ ወጪ  ከ638 ሚሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ አቅዷል። በ2026 የአለም ዋንጫ የሚሳተፉት 48 ብሔራዊ ቡድኖች መሆናቸው 120 ጨዋታዎች እንዲካሄዱ የሚያደርግ ሲሆን በአንድ የዓለም ዋንጫ  ግጥሚያ ከገቢ አንፃር ሲታይ 4.26 ቢሊዮን ዶላር በጀት ለያስፈልገው ይችላል።

Read 841 times