Monday, 20 March 2023 00:00

የጨፈገገው የፖለቲካ ድባብ፣…አዲስ ለውጥ ነው? ወይስ አዲስ መገለጥ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 የአገሪቱ የፖለቲካ አየር ተቀይሯል። ከአመት ከሁለት ዓመት በፊት የአገሪቱን ፖለቲካ የጎበኘ ወይም የመረመረ ሰው፣ ዛሬ ተመልሶ ቢመጣ፣ ግራ ሊጋባ ይችላል። ያኔ ያየሁት አዝማሚያና የሰማሁት ቅኝት ወዴት ሄደ የሚል ጥያቄ የሚፈጠርበት አይመስላችሁም? ጣዕሙና ቃናው፣ መዓዛው ወይም ሽታው ተቀይሯል። ከመቼ ወዲህ?
የፖለቲካው መልክና ድባብ የተለወጠው ባለፉት ሳምንታት፣… ወይም ባለፉት ወራት ነው ማለት ይቻላል። በእርግጥም፣ ፖለቲካችን፣ ከዚህም ከዚያም በእልፍ አቅጣጫ እየተናጠ እየደፈረሰ እንደ አዲስ መልኩ ተቀይሯል። “አቤት ፍጥነቱ!” ያስብላል።
ግን ደግሞ፣ “የአገራችን ፖለቲካ ምኑ ተቀይሮ ነው መንፈሱ የተለወጠው” ብለን ብንጠይቅ፣ የሚያጠግብ መልስ ለማግኘት እንቸገራለን። ፖለቲካው፣ በግላጭና ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ ወይም ሲንተከተክ ቆይቶ እንደ አዲስ ተገለጠ እንጂ፣ በጥቂት ሳምንታት ወይም በጥቂት ወራት ውስጥ የተፈጠረ አዲስ ነገር የለም።
እንዲያውም፣ የአገራችን ዋና ዋና የፖለቲካ ችግሮች፣ ተባብሰው እንደሆነ እንጂ ዓመታትን ያስቆጠሩ ነባር ችግሮች ናቸው።
 እዚህም እዚያም የተለኮሱ የጥላቻ እሳቶችና የተጣዱ የጥፋት ሰበቦች፣ በየጊዜው ሲራገቡና በየቦታው ሲዛመቱ ቆይተው፣ ባለፉት ወራት ክፉኛ እየተቀጣጠሉና እየገነፈሉ፣ አገር ምድሩን ሲያዳርሱ፣ አየሩን ሁሉ አወዱት።
አውዱን ድባቡን ለወጡት።
ነገር ግን፣ ድንገት ዘንድሮ የተለኮሱና የተጣዱ የፖለቲካ ችግሮች አይደሉም። የቆዩ ናቸው።
እናም፣ ዘንድሮ ባለፉት ወራት የመጣ አዲስ ፖለቲካ ቅኝት የለም ብንል ያስኬዳል።
እና፣ ምን እንበ? የአገራችን የፖለቲካ አየር ተለወጠ እንበል? ወይስ ነባሩ ፖለቲካ እንደ አዲስ ተገለጠ እንበል?
ሁለቱም ሃሳቦች ትክክል ናቸው።
የዘንድሮ የፖለቲካ ድባብ፣ ከአምና ከካቻምና በእጅጉ የተለየ ነው። ይሄ ጥያቄ የለውም። የብዙ ሰዎች የፖለቲካ ስሜት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ግራና ቀኝ፣ ፊትና ኋላ ተገለባብጧል። ደግሞም፣ ለውጡ ጊዜያዊ አይመስልም። ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረው የፖለቲካ መንፈስ፣ በራሱ ጊዜ ተመልሶ አይመጣም። መልሶ ማምጣት ይቻል እንደሆነም እንጃ። እናም የዘንድሮው ፖለቲካ፣ “አዲስ ክስተት”፣ “አዲስ ለውጥ” ነው ማለት ይቻላል።
ግን ደግሞ፣ አዲስ የመጣ የፖለቲካ ሃሳብ፣ ዝንባሌና ተግባር አለ ወይ? እስቲ ዋና ዋናዎቹን የፖለቲካ ችግሮች እንመልከት።
ዘረኝነትን የሚያባብስ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣ ጭፍን ጥላቻና የማቧደኛ ቅስቀሳ፣… ከመኖሪያ መንቀልና ማሳደድ፣ ንብረት ማውደምና ነፍስ ማጥፋት፣… የዘንድሮ ፈጠራዎች አይደሉም። ፖለቲካንና ሃይማኖትን የማቀላቀል ሙከራና ዘመቻስ አዲስ ክስተቶች ናቸው? አይደሉም።… ሁከትና ወከባ፣ መንገድ መዝጋት፣… ማለቂያ የለውም። የክልልና የከተማ ቅርምቱም፣ ዘንድሮ የተጀመረ አይደለም።
የፖለቲከኞች የአደባባይ ዲስኩርና ከየጓዳው በኢንተርኔት የሚሰራጨው የአዳሜ ንትርክ ሁሉ፣ በጥላቻ ለተቃርኖና ለብሽሽቅ እየተነጣጠረ ነው። ይሄም አዲስ አይደለም። ከዳር እስከ ዳር ለዓመታት ሲናኝ የቆየ ነው።
የፖለቲከኞች የጥላቻ ውዝግብና ዲስኩር፣… እንዲሁም በፌስቡክና በዩቱብ እየተሰራጨ የሚዛመተው የጥላቻ ብሽሽቅ፣… እንዲሁ አየር ላይ ተንሳፍፎ አይቀርም።
አየሩን ያወደው የብሽሽቅና የፀብ ወሬ፣ መሬት ላይ ሲተረጎም፣ የጥቃት ዘመቻንና ጦርነትን ይወልዳል፤ እልቂትና ሀዘን ያመጣል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የገንዘብ ህትመትና የዋጋ ንረትም እንደ እሳት ይለበልባል። እናም፣ የዜጎች ኑሮ፣ ከድጡ ወደ ማጡ ተጎሳቁሏል።
እፎይታ በናፈቀው አገር ውስጥ፣ በየእለቱ እየተፈበረከ በሚመጣ የግርግርና የነውጥ ሰበብ፣ የቀውስ መዓት ይደራረብበታል። እረፍት በሌለው የነውጥ ወጀብ ውስጥ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በስጋትና በአደጋ እየተንገጫገጨ፣ የሥራ አጥነትና የረሃብ መከራ፣ እንደተራ ነገር ሆነውብናል።
መጠናቸውና ደረጃቸው፣ ስርጭታቸውና የድግግሞሽ ፍጥነታቸው ዘንድሮ ተባብሷል ካልተባለ በቀር፣ ሁሉም ዓይነት ችግሮች ባለፉት ዓመታት የነበሩና የታዩ ናቸው።… እየተፈራረቁና እየተደራረቡ ከመከሰታቸው የተነሳም፣ የተላመድናቸው ቀውሶች ናቸው።
የተላመድናቸው ቢሆኑም ግን፣… አዲስ የተፈጠረ መጥፎ ድባብ አገሪቱ ላይ አጥልቷል። የብዙ ዜጎች መንፈስ ተቀይሯል።
በአንድ በኩል፣ የጥላቻ ብሽሽቁና ዲስኩሩ፣ የጥቃት ቅስቀሳውና የጥፋት ዘመቻው፣ የፖለቲካው የቅራኔ ቅኝትና መተናነቅ እቅድ ሁሉ አዲስ አይደለም።
በሌላ በኩል ግን፣ የተላመድናቸው የአገራችን ችግሮች ጭጋግና ካፊያ ብቻ ሆነው አልቀሩም። እንደ ናዳ እየተዘረገፉ፣ በዶፍ እየወረዱ፣ በጎርፍና በማዕበል እየተከታሉ፣ ወደ አዲስ አደገኛ አስፈሪ እርከን ተቀይረዋል።
ክፉ ነገር ላለማየትና ተስፋ ላለመቁረጥ የሚሹ ብዙ ሰዎች፣ ዛሬ የአገሪቱን ችግሮችና አደጋዎችን አለማየት እየተሳናቸው መጥተዋል። ለስፍር ቁጥር ከሚከብዱ የአገሪቱ ፈተናዎች ጋር ለመፋጠጥ ተገድደዋል። እንደ አዲስ ተገልጦላቸዋል ማለት ይቻላል።
የአገሪቱ መከራና የፖለቲካ ቅኝት አዲስ ባይሆንም፣ ነባሮቹ ችግሮች ተደራርበውና ተዛምተው፣ ፋታ በማይሰጥ ፍጥነት እየበዙና እየገዘፉ፣ በሁሉም ቦታ በሁሉም ጊዜ የእለት ተእለት ትዕይንት ሆነዋል። አለማየት የማልቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰዋልና፣… ለብዙ ሰዎች እንደ አዲስ ሆኖባቸዋል - “አዲስ መገለጥ” እንዲሉ።
በሌላ አነጋገር፣… አዲስ መገለጥ ልንለው እንችላለን። ከመገለጥ ያለፈ፣ አዲስ ለውጥም ነው ማለት እንችላለን። ጣል ጣል፣ ጠብ ጠብ ሲል የነበረ በዶፍና በገፍ እየተዘረገፈ እየጎረፈ መምጣት ሲጀምር፣ አዲስ ድባብ፣ አዲስ የፖለቲካ አየር ተፈጥሯል ያስብላልና።
ይሄ፣ ለሁሉም ፈተና ነው። የአገር ፈተና ነው።
ለመንግስት፣ ለገዢ ፓርቲ፣ ለባለስልጣናት ትልቅ ፈተና ነው።
ለምሁራንና ለዜጎች፣ ለተቃዋቂ ፓርቲዎችና ለፖለቲከኞች ሁሉ፣ ከባድ ፈተና ነው።
አሳዛኙ ነገር፣ የሚያዛልቅ መፍትሄ ለመፍጠርና ጊዜው ሳይረፍድ ለመትጋት የሚሞክሩ ሰዎች ብዙ አይደሉም። ይሄ፣ በአገራችን እምብዛም የተለመደ ዝንባሌ አይደለም።
ይልቅስ፣ ወደ እልህና ወደ ትንቅንቅ፣ ወደ ውንጀላና ወደ ማስተባበያ፣ ወደ መራገምና ወደ ማሳደድ፣ ወደ አመጽና ወደ አምባገነንነትን መንገድ ያዘነበለ ነው - ፖለቲካችን።
ከዚህስ፣ ሁሉም እንደየአቅሙና እንደየሃላፊነቱ መጠን፣ ለመፍትሄ ቢተጋ ነው የሚሻለው።

Read 733 times