Sunday, 12 March 2023 11:39

እናቶችን “ወደ ሳቃቸው ለመመለስ” የሚተጋው ወጣት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

  “የእኔ እናት 14 ዓመት አልቅሳ ነው ወደ ሳቋ የተመለሰችው”


     የዛሬ 17 ዓመት በ1998 ዓ.ም በዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፣  በእነ ሰለሞን ዘገየ ቤት ውስጥ አንድ ህንፃ ተወለደ። ይህ ህጻን ሲወለድ ጀምሮ ባጋጠመው የብልት ችግር ሳቢያ ሽንቱን የሚሸናው በእምብርቱ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ቤተሰቡ ከማህበራዊ ህይወት ከመገለል ጀምሮ ብዙ ማህበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውሶችን መጋፈጥ ጀመረ። ህጻኑም ባጋጠመው ተፈጥሯዊ ችግር ምክንያት ለ14 ዓመታት ከቤት ሳይወጣ፣ እንደ ጓደኞቹ ሳይቦርቅና ት/ቤት ሳይሄድ ቆየ። ከዚያስ ምን ተፈጠረ? የህጻኑ መጨረሻስ ምን ሆነ?
 የዚህ ልጅ ታላቅ ወንድም መምህር ሰለሞን ዘገየ፣ ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ ብቅ ብሎ ነበር፡፡  በታናሽ ወንድሙ ችግርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከመምህር ሰለሞን ዘገየ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡ “እናቶችን ወደ ሳቃቸው የመመለስ ተልዕኮውንም” ነግሯታል፡፡ እንድታነቡት ተጋብዛችኋል፡፡           እስኪ ስለ ወንድምህ ችግርና ቤተሰብህ ስላሳለፈው ችግር አጫውተኝ?
እኔ ለቤተሰቤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ። በ1998 ዓ.ም እናቴ ስትወልድ ልጁ ሁሉም የሰውነቱ ክፍል አፈጣጠሩ ትክክል ነው። ብልቱም ሁሉም የተስተካከለ ሆኖ ተፈጥሯል። ግን ሽንቱ የሚመጣው በእምብርቱ ነው። ይህ ቤተሰባችን ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ ነው የፈጠረው። ያልተለመደና በአካባቢው ታይቶ ስለማይታወቅ ሰውም ጉድ እያለ፣ ምን አይነት እርግማን ነው እየተባባለ ቤተሰባችን በእጅጉ ሲሸማቀቅ ቆይቷል። እናቴ ሰርግና ለቅሶ  የመሳሰሉ ማህበራዊ መስተጋብሮች ላይ ስትሄድ ልጁን አውርዳ በሰው ፊት ለማጥባትም ሆነ ለማጣጠብ አትችልም ነበር። በጣም ነበር የምትሸማቀቀው። እኔም ይህን ሳይ ከአካባቢው ጠፍቼ ሁሉ ለመሄድ ብዙ ጊዜ ቃጥቶኝ ነበር። ይህ ልጅ እስከ 14 ዓመት እድሜው ከቤት ሳይወጣ፣ ሳይጫወትና  ት/ቤት ሳይሄድ ነው የቆየው።
በዚህ ሁሉ ዓመት ወደ ሀኪም ዘንድ ለመውሰድና ለማሳየት አልሞከራችሁም?
ያው ገጠር ውስጥ ስለሆነ እንደ ተዓምር ስለታየ ብዙ አልሞከርንም ነበር። በመጨረሻ አንዲት አያል ኪሮስ የምትባል የምንወዳት ልጅ ነበረች፡፡ “Help It us” የሚባል ድርጅት ውስጥ ነው የምትሰራው። በዚህ በእኛ ቤተሰብ ጉዳይ ትጨነቅ ነበርና ከሰዎች ጋር ተነጋግራ ስታበቃ፣ እስኪ እንዲህ እንዲህ ቦታ ፈረንጆች አሉና፣ ሄደህ ይህንን ነገር ሞክር አለችኝ።
እኔም መምህር ነኝ፤ከማስተምርበት ት/ቤት ፈቃድ ጠይቄ ወጣሁና አያልን በደንብ አነጋገርኳት፤ በደንብ አስረዳችኝ። ሳልውል ሳላድር ወንድሜን ይዤ የተባልኩበት ቦታ ሄድኩኝ።
የት ነው ቦታው? አዲስ አበባ ነው?
አይደለም፤ ትግራይ ውስጥ አላማጣ ነው የሄድነው። አላማጣ ያሉት ሀኪሞች አዩትና እኛ ይህንን መስራት አንችልም፤ ከአቅማችን በላይ ነው ብለው ወደ አዲስ አበባ ላኩኝ። አዲስ አበባ በአንድ ቀን ገባሁ። አዲስ አበባ ስመጣ የመጀመሪያዬ ነበር።
መቼ ማለት ነው?
2012 ዓ.ም መሆኑ ነው። ከሶስት ዓመት በፊት ማለት ነው። ከዚያ ስድስት ኪሎ አካባቢ የማዘር ትሬዛ ድርጅት ነው የሚባል “ሲስተር ሀውስ” የተባለ ድርጅት አገኘሁና ከነሱ ጋር ስለጉዳዩ መወያየት ጀመርኩኝ። በዚህ ድርጅት ምክንያት ብዙ ሂደቶች ታለፉና ኮሪያ ሆስፒታል እንዲገባ ተደረገ። በሁለት በሦስት ወር ህክምና ሽንቱን በብልቱ እንዲሸና አድርገው አስተካክለው አከሙት። ከዚያ በኋላ  በቤት ውስጥ ተገድቦ የነበረው ልጅ፣ ያ እንደ ጓደኞቹ ሳይቦርቅ 14 ዓመት የሞላው ወንድሜ፣ ዛሬ ላይ ት/ቤት ገብቶ ታሪኩ ተቀይሮና ሥነልቦናው ተስተካክሎ ጎበዝ ተማሪ ሆኗል እልሻለሁ።
ቤተሰብህስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
ቤተሰቤ በጣም ደስተኛ ነው። ሌላውን ተይው እናቴን ብታያት በጣም ነበር  የምታሳዝነው። 14 ዓመት ሙሉ ከማንም በላይ መከራ ያየችው እናቴ ናት። በአካባቢው፣ በጎረቤቶች ፊት አንገቷን ደፍታ፣ ለፈጣሪ እያለቀሰች ከሰውነት ተራ ወጥታ ነበር የኖረችው። አሁን ብታያት መልኳ ተመልሶ፣ ሰውነቷ ተስተካክሎ እንቅልፍ መተኛት ጀምራለች። ፈጣሪዋን ሌት ተቀን እያመሰገነች ነው ያለችው። አካባቢውም ጎረቤቱም በጣም እየተገረመ ነው ያለው።
ከዚያስ ወደ ሥራህ ተመለስክ?
በእርግጥ ያን ጊዜም ሥራዬን አልተውኩም። ት/ቤቱም ችግሬን ተረድቶ ፈቃድ እየሰጠኝ ነበር ወንድሜን ያሳከምኩት። አሁንም ግን ሙሉ ለሙሉ በሥራ ገበታዬ ላይ አይደለሁም።
ለምን በሥራ ገበታህ ላይ ሙሉ ለሙሉ አልተመለስክም?
እኔና ቤተሰቤ በወንድሜ ምክንያት ብዙ መከራ፣ ብዙ እንግልት፣ ብዙ መሸማቀቅ፣ ብዙ መገለል ደርሶብናል። ያውም ለ14 ዓመታት። ወንድሜ ከታከመና ወደ ጤንነቱ ከተመለሰ በኋላ እኔ እፎይ ብዬ መተኛት አልቻልኩም። ምክንያቱም እኛ ይህን ሁሉ ዓመት ይህ ሁሉ መከራ የደረሰብን መንገድ በማጣት፣ በግንዛቤ ችግር ነው። ይህ የፈጣሪ ቁጣ እንጂ ታክሞ የሚድን አልመሰለንም። እንደኛው ሁሉ በእንደዚህ አይነት የአፈጣጠር ችግር በልጆቻቸው ስንት መከራ የሚቀበል ቤተሰብ ይኖር ይሆን የሚለው ጥያቄ እንቅልፍ ነሳኝና፣ በየወረዳው በየቀበሌው እየዞርኩ እንዲህ አይነት ልጆችን መፈለግ ጀመርኩ። በፍለጋዬ ከወንድሜ ጋር ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውም ሆኑ የተለያዩ ችግሮች የደረሱባቸው በርካታ ህጻናትን ማግኘት ቻልኩኝ።
እስኪ ምን ምን አይነት የጤና እክሎችን አገኘህ?
የተቆለመመ እግር ያላቸው፣ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ያጋጠማቸው፣ የሰገራ ፊንጢጣቸው የተደፈነና በሆዳቸው የሚጸዳዱ፣ ጉንጫቸው በአንድ በኩል ያበጠ፣ ብቻ ብዙ አይነት ችግር ያላቸውን ህጻናት ማግኘት ቻልኩኝ። የወንድሜን መዳን የሰሙ ሰዎች እንዲህ  ወረዳ፣ እንደዚህ ቀበሌ፣ እንዲህ የሚባል መንደር ውስጥ እንደዚህ ልጅ ታሞባቸው የሚሰቃዩ ቤተሰቦች አሉ ከተባለ የማንንም እርዳታ ሳልጠይቅ፣ በእግሬ ጭምር ገጠር እየገባሁ ልጁን አገኛለሁ። ለምሳሌ አንዱ የሰገራ መውጫ ፊንጢጣው ድፍን የሆነ ልጅ አግኝቻለሁ ብዬሻለሁ። ከዚህ ከሰቆጣ መቀሌ ሄዶ በሆዱ በኩል ተሰርቶለት ነበር የሚፀዳዳው። ለዳግም ህክምና መቀሌ ሊሄድ ሲል በመንግስትና በህወሓት መካከል ጦርነት ተነሳ። ልጁ የትም ሄዶ መታከም ስላልቻለ ኢንፌክሽን ፈጠረበት። ልጅ ስለሆነ ወጣ ብሎ ለመጫወት ሲሞክር ቁስሉን ዶሮዎች ሁሉ ይነክሱትና ይሰቃይ ነበር።
ለእሱ ልጅ መፍትሄ አገኘህለት ታዲያ? ምን አደረግክ?
በወቅቱ በነበረው ጦርነት በላሊበላ በኩል መውጣት ስለማይቻል የመጨረሻ አማራጭ ያደረግኩት ባጃጅ ተከራይቼ፣ ታህሳስ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ልጁን ይዤ ተነሳሁና ተከዜ ድረስ ወሰድኩት። ከዚያ በጀልባ ወደ ጎንደር ተሻገርኩ። ከዚያ ሳህላ ስየምት የሚባል ወረዳ አልፌ ነው ወንዝ የተሻገርኩት። አስቢው የእኛ ዝቋላ ወረዳ ነው የሚባለው። ይሄ ህጻን ዘመዴ አይደለም፤ አይወለደኝም፤ ነገር  ግን ቤተሰቡን እናቱን ሳስብ፣ የእኔ እናት በወንድሜ  ምክንያት ያሳለፈችው መከራ ነው ሁሌ የሚታየኝ። የእኔ እናት 14 ዓመት አልቅሳ ነው ወደ ሳቅ የተመለሰችው። አሁንም የኔ ፍላጎት በየቤቱ እንደ እናቴ በር ዘግተው ተገልለው የሚያለቅሱ እናቶችን እየፈለጉ ወደ ሳቃቸው መመለስና እፎታ እንዲያኙ ማድረግ ነው። ወደ ልጁ ስመለስ ተከዜን በጀልባ ይዤ ተሻግሬ፣ ሳህላ ስየምት የሚባል ወረዳ አደርን። ከዚያ ባህር ዳር ገባን፣ ከዚያ አዲስ አበባ መጣን። ልጁ ታክሞ ተስተካክሎ ወደ ጤናው ተመልሷል። ቤተሰቦቹም እፎይ ብለዋል።
የት ታከመ? ለመሆኑ ይህን ስታደርግ ወጪውን ማን ይሸፍንልሃል?
እንግዲህ የኔ ወንድም ከዳነ በኋላ የሚያለቅስ ቤተሰብ እንዳለ በማሰብ ከኮሪያ ሆስፒታል ጋር መነጋገር ጀመርኩ። በኮሪያ ሆስፒታል ስር “ቢታኒያ ኪድስ” የሚባል በጎ አድራጎት ይመስለኛል፣ ልጆች በነጻ ያክማል። ከእነሱ ጋር በመነጋገር ለኪስ የሚሆን ገንዘብ ባይሰጡም፣ የልጆቹን የእኔን፣ የአስታማሚ ወጪ ይሸፍናሉ። በተለይ የእኔን የትራንስፖርት ወጪ ይሸፍናሉ። እኔ ስራዬን ትቼ፣ ልጆቼን ትቼ ይህን የምሰራው በቤተሰቤ የደረሰው ስቃይና መከራ እንደተቀረፈ ሁሉ የሌሎችም ስቃይ እንዲያበቃና እፎይ እንዲሉ ነው። የሚገርምሽ የልጆቻቸው ጤና ተስተካክሎ እናቶች እፎይ ብለው ሳይ ከምንም በላይ እርካታ ይሰማኛል።
እስካሁን በዚህ ሂደት ከወንድምህ ውጪ ምን ያህል ህፃናትን አሳከምክ?
እስካሁን ከ20 ያላነሱ የተለያየ ችግር ያለባቸውን ህፃናት አሳክሜ ወደ ጤንነታቸው ተመልሰዋል። እነዚህ ልጆች ሰገራ መውጫ ፊንጢጣ መደፈን፣ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ፣ እንደ እንቅርት በአንድ ጉንጫቸው በኩል ያበጠባቸውና የብልትና የሽንት አሸናን ችግር ያለባቸው ሁሉ ታክመዋል። የእግር መቆልመምን ጨምሮ ሌሎች የአጥንት ችግር ያለባቸውን ልጆች እዚህ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኝ ኪዩር በሚባል ሆስፒታል አሳክሜአለሁ። ከእነዚህ ከሁለቱ ሆስፒታሎች ጋር በመነጋገር ነው ህጻናቱን እያመጣሁ እያሳከምኩ ያለሁት። በእርግጥ የኪዩር ሆስፒታል ታካሚዎች የማረፊያ ወጪ ስለማይሸፈንላቸው ይቸገራሉ። የኮሪያ ሆስፒታል ታካሚዎች  ግን ስድስት ኪሎ በሚገኘው ሲስተር ሀውስ ማረፊያ ይፈቀድላቸዋል። ኪዩር ሆስፒታል የማዘር ትሬዛ ተቋም ከሆነው ሲስተር ሀውስ ጋር ስምምነት ስለሌለው የማረፊያና የምግብ ይቸገራሉ።
ሌሎች ለመታከም የሚጠባበቁ አሉ ወይስ 20ዎቹ ላይ አበቃህ?
የሚገርምሽ ከ30 በላይ ህክምና የሚጠባበቁ ህጻናት እጄ ላይ አሉ። እስካሁን እነዚህ ሁሉ ልጆች ከሶስት ወረዳ ማለትም ከዝቋላ፣ ከአበርገሌና ከሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች ብቻ የተገኙ ናቸው። በሌሎች ወረዳዎች ብዞርና ብፈልግ እጅግ በርካታ የጤና እክል ያለባቸው ልጆች እንደማገኝ እርግጠኛ ነኝ። አሁን ህክምና እየተጠባበቁ ከሚገኙ ልጆች መካከል የዘር ፍሬ እብጠት ያለባቸው፣ የሽንት ቧንቧቸው ተዘግቶ የሚሰቃዩ፣ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው ሁሉ አሉ።
አሁን አስተማሪነትህን ትተኸዋል ወይስ እየሰራህ ነው?
በእርግጥ ስራዬን አልተውኩትም። ነገር ግን እነዚህን ቤተሰቦች ለመርዳትና የህጻናቱን ጤንነት ለማስመለስ በምሰራው የበጎ አድራገት ስራ የዝቋላ ወረዳ አስተዳደር “ይሄ ልጅ ያለምንም ገቢ በራሱ ተነሳሽነት ይህንን ሁሉ ከሰራ ጥሩ ነውና ልጆች እየፈለግን ወደ ወረዳው እናምጣለት፤ ወደፊት ነገሮች ከተስተካከሉና በዚሁ ስራው የሚቀጥልበት መንገድ ካለ ጥሩ፣ ካልሆነ ደግሞ ወደ አስተማሪነቱ ይመለሳል” ብለው ለጉዳዩ እውቅና ሰጥተውት ነው እየሰራሁ ያለሁት:: የመምህርነት ደሞዜ ይከፈለኛል:: ት/ቤቱ  “ህብር አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት” ይባላል።
እነዚያ ህክምና የሚጠባበቁ ከ30 በላይ ህጻናት የት ነው ያሉት?
ቅድም በጠቀስኩልሽ ዝቋላ፣ አበርገሌና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች ነው ያሉት። ገና ወደ አዲስ አበባ አልመጡም።
አሁን የተገናኘነው አዲስ አበባ ካዛንቺስ ነው። ታካሚ ህጻናት ይዘህ መጥተህ ነው?
አዎ አራት ህጻናትን ይዤ መጥቼ ነው። ከአራቱ ሦስቱ ከዋግህምራ የመጡ ሲሆኑ አንዱ ደግሞ ከላሊበላ ነው የመጣው። ከዚህ በፊት ከራያ ቆቦም አምጥቼ አሳክሜያለሁ። እኔ ችግር አለ በተባለበት ሁሉ ነው የምሄደው፤ ዝምድና ብሄር የሚባል ነገር የለም። ሰው በመሆናቸው ብቻ ከስቃያቸው ታክመው መዳን አለባቸው። ቤተሰቦቻቸውም እረፍት ማግኘት አለባቸው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። አሁን በአካባቢው እኔ የምሰራው ሲሰማ እኔን ለማግኘትና ችግሩን ለመግለጽ የማይፈልግ የለም። ስልኬ ለደቂቃ አያርፍም። የሰዎቹን ችግር ሁሉንም አዳምጣለሁ።
እስኪ የአንድን ህጻን ችግር ከሰማህበት ጊዜ አንስቶ እስከሚታከምበት ድረስ ያለውን ሂደት አስረዳኝ?
ሰዎች ይጠቁሙኛል፤ ሄጄ ህጻኑን አያለሁ፤ ያለበትን ችግር በደንብ አዳምጣለሁ፤ ከዚያ ለኮሪያና ለኪዩር ሆስፒታሎች የልጆቹን ችግር እገልጻለሁ። የቀደመ የህክምና ሙከራና ሂደት ካላቸውም ዶክመንታቸውን ለሆስፒታሎቹ አሳያለሁ። ይሄ መታከም ይችላል ይምጣ ሲሉ ያን ጊዜ ከወላጆቻቸው ጋር እነጋገርና ወላጆች ተስማምተው አባት ወይም እናት አንድ አስታማሚ ያስፈልጋልና ይመደባል። ልጆቹን ከአንድ ወላጅ ጋር አድርጌ ይዤ እመጣለሁ። አንደኛ ቀዶ ጥገና ሲያደርጉ የሚፈርም ሰው ያስፈልጋል። ያንን ለወላጅ ነው የምተወው። እኔ የሰው ልጅ ፈርሜ ማሳከም አልችልም።
እስካሁን ካገኘኻሃቸው ታማሚዎች ሆስፒታሎቹ ይህን ማከም አንችልም ከአቅማችን በላይ ነው ያሉት  አለ?
የአዕምሮ ጤና ችግርና መሰል ነገሮች ካልሆኑ በቀር፣ በአካል ላይ የሚፈጠር ችግር ማለትም ቅድም ከላይ የጠቀስኩልሽ አይነት ችግሮች እስካሁን በጥሩ ሁኔታ ታክመው ተስተካክለዋል።


Read 1665 times