Sunday, 12 March 2023 10:17

ሕብረት ባንክ ያሻሻለውን የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት በይፋ አስጀመረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ቴክኖሎጂው በራሱ ባለሙያዎች አቅም መበልጸጉን አስታውቋል


          ሕብረት ባንክ ያሻሻለውን የ*811# ዩኤስኤስዲ ኮድ እና የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ፣ በራሱ የውስጥ ሰራተኞች አቅም በማበልጸግ  አገልግሎቱን በይፋ አስጀምሯል፡፡
 ሕብረት ባንክ የተሻሻለውን የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት በራሱ የአይቲ ቡድን በመተግበር በሃገራችን የመጀመሪያው ባንክ ነው ተብሏል።
ሕብረት ባንክ የተሻሻለውን የ*811# ዩኤስኤስዲ ኮድ /USSD Code/  እና የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያውን የብሔራዊ ባንክ ተወካይ፣ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እና የባንኩ ከፍተኛ  አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ከትላንት በስቲያ ሐሙስ  በባንኩ ዋና መ/ቤት በይፋ አስመርቋል። አዲሱ የሕብረት ሞባይል ባንኪንግ፤ የባንኩን ገጽታ በጠበቀ መልኩ የተለያዩ ዘመናዊ አገልግሎቶችን አካትቶ፣ ለደንበኞች አጠቃቀም ምቹና ፈጣን በሆነ ሁኔታ ተዘጋጅቶ የቀረበ መሆኑ ነው የተገለጸው።
 የተሻሻለውን “የሕብር ሞባይል አገልግሎት” አስመልክቶ የሕብር ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ፣ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋዱ ላይ በባንኩ ዋና መ/ቤት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
 ዋና ሥራ አስፈፃሚው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንዳብራሩት፤ የተሻሻለውን የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ሁለት ነገሮች ልዩ ያደርጉታል። የመጀመሪያው በውስጡ በርካታ አገልግሎቶችን ያካተተ መሆኑ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ  በራስ የውስጥ ባለሙያዎች አቅም መበልጸጉ  ነው፤ ብለዋል።
ይህም በዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ለሌሎች ባንኮችና ለሀገር አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን የሕብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ከበደ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን በመወከል የተገኙት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የክፍያ ሥርዓት ክትትልና ልማት ኃላፊ አቶ ሰሎሞን ዳምጠው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሀገር አቀፍ ደረጃ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓትን ለማሻሻልና የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ባንኮችም በዚሁ ሥራ ላይ በመሳተፋቸው በዲጂታል የክፍያ አገልግሎት አሰጣጥ እድገት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ፕሮጀክቱ በራስ አቅም መሰራቱ የውጭ ምንዛሬን ከማዳኑም ባሻገር ባንኩ ወደፊት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ለሚያከናውናቸው የሲስተም ኢንተግሬሽን ሥራዎች ጠንካራ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ሀገራችን ለምትከተለው የብሔራዊ ዲጂታይዜሽን ስትራቴጂ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው።” ብሏል፤ ባንኩ ባወጣው መግለጫ።
 በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ በራስ አቅም ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ተጠቃሽ የሆነው ሕብረት ባንክ ከዚህ ቀደምም የኮር ባንኪንግ ሥርዓቱን በሀገራችን የባንክ ዘርፍ ባልተለመደ ሁኔታ በራሱ የውስጥ አቅም ማሻሻሉን በመግለጫው አስታውሶ፤ በተጨማሪም በኦንላይን ባንኪንግ፣ በዳታ ሴንተርና በዲዛስተር ሪከቨሪ ፋሲሊቲ የኢንፎርሜሽን ሴኩሪቲ ማኔጅመንት ሲስተም ISO/IEC 27001:2013 መስፈርትን በማሟላት፣ አስተማማኝ የደህንነት ስርዓት በመዘርጋትና ሰርቲፋይድ በመሆን በሀገራችን የቀዳሚነቱን ቦታ የያዘ ባንክ መሆኑን አውስቷል፡፡



Read 1622 times