Sunday, 05 March 2023 00:00

ዳኝነት፡ ነጻነቱ በሥራ አስፈጻሚው፣ ክብሩ በዳኞች የተገፈፈ ለታ …

Written by  ፍሬው ማዕሩፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ‘ዳኞች ከመመረመሩ ይናገራል ምድሩ፣ ይገኛል ነገሩ’
                     
          በቅርቡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌስቡክ ገጽ ላይ፣ የሕግ አውጪው የመንግስት አካል ከአራት ዓመት በፊት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ የሾማቸው ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ እና አቶ ሰለሞን አረዳ በፍቃዳቸው ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ፣ በምትካቸው አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እና ወይዘሮ አበባ እምቢን መተካቱን እንዲሁም ለቀድሞዎቹ ሽኝት እንደተደረገ አነበብኩኝ፡፡
ይህ ታዲያ ከወራት በፊት የፍትህ አካላት ዋነኛ ተዋናይ ስለሆኑት ዳኞች፣ በተመሳሳይ ወቅት ሁለት ተቃራኒ ሊባሉ የሚችሉ ዜናዎችን መዘገባቸውን አስታወሰኝ፡፡
አንደኛው፤ በኦሮምያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምስራቅ ምድብ ችሎት የሚገኙ ሦስት ዳኞች ህጋዊ ሂደት ሳይጠበቅ መታሰራቸውን እንዲሁም ሌላኛው በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ዳኛ የሆኑት ግለሰብ፣ በፖሊሶች መታሰራቸውንና በእዚህም የተነሳ የወረዳው ፍርድ ቤት ሥራ ማቆሙን የሚገልጹ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ጠ/ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ሕዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም በፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ላይ፣ ዳኞች ዓይን ያወጣ ሌብነት ውስጥ መግባታቸውንና እንደውም በቴሌግራም አማካኝነት በግልጽ - በአደባባይ ጉቦ መቀባበል የተደረሰበት ዘመን ላይ መሆናችንን  ማሳወቃቸው ነው፡፡ (ከዚህ ቀደምም ጠ/ሚኒስትሩ  ኢትዮጵያ ውስጥ በሌብነት ዳኞች በቀዳሚ ደረጃ ላይ የሚቀመጡ እንደሆነ ገልጸው እንደነበር ይታወሳል፡፡)
እንግዲህ ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለት ዜናዎች፣ በጣም በተቀራረበ ጊዜ ውስጥ በሀገራችን ተፈጽመዋል የተባሉ ናቸው፡፡ በወቅቱ ሕገ መንግስታዊ ጥበቃ ያለው የዳኝነት ነጻነት በመንግስት አካላት ካልተጠበቀ፣ የሕግ ብቻ ሳይሆን የሞራል መሰረትና ሃይማኖታዊ ክብር ያለው ዳኝነት በባለቤቶቹ ከተናቀ፣ ሀገሪቱ ከገደል አፋፍ ላይ በእርግጥም ደርሳለች ለማለት ያስደፍራል፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ ስብራት ለምን ስጋት ሆነ?
ፍትሕ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ፣ ጠበብ ባለ መልኩ ትርጓሜ ይሰጠው ከተባለ፤ ፍርድ ቤት የቀረበ ጉዳይ ተገቢውን ሥነ ሥርዓት ተከትሎ፣ ሕግን ባከበረና በጠበቀ መልኩ የሚገኝ ውጤት ማለት እንደሆነ ብዙኃኑ የሕግ ልሂቃን ይስማሙበታል፡፡
ዜጎች ውል የሚገቡት፣ ሃብት የሚያፈሩት፣ በነጻነት የሚንቀሳቀሱት ሕግ ጥበቃ ያደርግልናል ብለው ነው፡፡ ሕግ ብለው በዋነኝነት የሚያስቡት ደግሞ በወረቀት ላይ ከተጻፈው ይልቅ የፍትህ አካላትን ነው ቢባል ብዙም አያከራክርም፡፡ በተለይም ችሎት ፊት ቀርበው ፍትህ ይሰጠኛል ብለው ለሚያስቡት ዳኛ የላቀ አክብሮት አላቸው፡፡ የሀገሬ ህዝብም ፍትህ ተነፈግያለሁ ሲል፣ ‘ዳኞች ከመመረመሩ ይናገራል ምድሩ፣ ይገኛል ነገሩ’ ብሎ፣ ጉዳዩን ይዞ ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱን አልተወም፡፡
ሆኖም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ የፍትህ ሥርዓቱን ሰፋፊ ችግሮች ጠልፎት ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘርፈ-ብዙ ምክንያቶችን ማስቀመጥ ቢቻልም፣ የሥርዓቱ ዋነኛ ጠባቂዎች መሆን ያለባቸው ዳኞች፣ የሚጋፈጧቸው ተግዳሮቶች፣ የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ከአቅምና  መሰል ጉዳዮች ጋር ያለውን ሰፊ ክፍተት ለጊዜው እናቆይ ብንል እንኳ፣ ከዳኛ ደጅ ማር ይዞ በመሮጥ የፈለጉትን አይነት ውሳኔ ለማግኘት ሩጫው መብዛቱን ለታዘበ አንድ ስጋት ይገባዋል፤ ይህ ሩጫ ሄዶ ሄዶ ሃገር እንዳያፈርስ!

የፍትሕ ሥርዓቱ ተጠግኖ፣ ሃገር እንዳትፈርስ ምን ይደረግ?
የትኛውም ሥርዓት የሚዘልቀውም ሆነ ተሰብሮ ለውድቀት የሚዳረገው በዋነኝነት በተቋማት ነው፡፡ ተቋማት ደግሞ የሚመሩባቸው ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች፣ ወሳኝነታቸው ሳይዘነጋ፤ የሚመሯቸው ግለሰቦች ብቃትና አቅም እንዲሁም ፍላጎትና ዓላማ ሚናቸው ትልቅ ነው፡፡
በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2014 አንቀጽ 17 ላይ የተጠቀሱትን  ጨምሮ ሕጉ የሚፈቅድላቸውን ተግባራት ፈጽመው፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በሁሉም ዘንድ የሚከበርና የሚታመን እንዲሆን አዲሶቹ ተሿሚዎች ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው፡፡
ይህ እንዲሳካ ደግሞ ቀዳሚና ዋነኛ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል ብዬ ከማስባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዳኝነት ነጻነትን በጽኑ ማስጠበቅ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ የዳኞች ሥነ ሥርዓትን የሚመለከተው ነው፡፡ ምክንያቱም መሰረታዊ የሕግ ተርጓሚው ሚና ፍትሕን ማስፈን  ነውና፡፡

የዳኝነት ነጻነት እና የዳኞች ሥነ ሥርዓት
ዳኛ ነጻነት ያለው ይሁን፡፡ ራሱን ለማስተዳደር ሥልጣን ያለው ያልሆነ ሰው ሌሎችን ሊያስተዳድር አይቻለውምና፡፡
(ፍትሐ ነገሥት፤ አርባ ሦስተኛ አንቀጽ 11፣ 420)
የዳኝነት ነጻነትን በተመለከተ በሕገ መንግስቱ ያላካተተ ሀገር የለም ማለት ይቻላል።  በመሰረታዊነት ታዲያ ስለ ዳኝነት ነጻነት መርህ ብዙዎች የሚስማሙበት ትርጓሜ፣ ዳኞች የቀረበላቸውን ጉዳይ የመንግስትም ሆነ የግለሰቦች ጣልቃ ገብነትና ትዕዛዝ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን፣የማኅበራዊ ሚዲያና የሕዝብ ስሜት ግፊትም ሆነ ሌሎች መሰል ሁኔታዎችን  ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ፣ ተከራካሪዎቹ በሚያቀርቡት ማስረጃ መሰረት ሕግን ብቻ ተከትሎ  ውሳኔ መስጠት (መበየን)  የሚለው  ነው፡፡
ሆኖም የዳኝነት ነጻነት የዳኞች ግለሰባዊ ነጻነትን ብቻ የሚያካትት ሳይሆን ተቋማዊ ነጻነትንም ጭምር የሚመለከት ነው፡፡ ይህም ማለት ፍርድ ቤቶች፣ ከመንግስት አካል አንዱ በሆነው የህግ ተርጓሚ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው፣ ከፍርድ ቤት አስተዳደር ጋር ተያይዞ ከተቀሩት የመንግስት አካላት ተጽዕኖ ነጻ ሆነው ዳኞችን ጨምሮ በስሩ ያሉ ሰራተኞችን ማስተዳደርና ከበጀት ነጻነት ጋር ተያይዞም ጥገኛ እንዳይሆኑ ማድረግን ነው፡፡
በሀገራችን የዳኝነት ነጻነትን በተመለከተ ሕገ መንግስቱ አንቀጽ 79 ላይ በግልጽ ቋንቋ አስቀምጧል፡፡ ከታች እስከ ላይ ያለ ባለስልጣን በዳኝነቱ አካል ላይ አንዳችም ተጽዕኖ እንዳያደርግ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን ከላይ በኦሮሚያ ክልል እና በአማራ ክልል በምሳሌነት እንደጠቀስናቸው ዓይነት በዳኞች ላይ የሚፈጸሙ ሕጋዊ ያልሆኑ ተግባራት  መስማት ያልተለመደ አይደለም። የፍርድ ቤት ትዕዛዞች መከበር ካቆሙማ ሰንበትበት ብሏል፡፡
በዘመነ ኢህአዴግ ፍርድ ቤቶቹ የአስፈጻሚው ታዛዥ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ቢሆኑም የሚሰጧቸው ትዕዛዞች በፖሊስ፣ በአቃቤ ህግና በሌሎች አካላት ያለመፈጸም ሁኔታ ሲፈጠር ብዙም አይስተዋልም ነበር፡፡ በዘመነ ብልጽግና  ደግሞ ዳኞች ይፈጸም ያሉት ትዕዛዝ ሰሚ እያጣ መጥቷል፡፡

የዳኞች ሥነ ሥርዓት
ሌላኛው ከፍትህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ የዳኞች ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ ሀገሪቱ ከዘመናዊ ሕጎች ጋር እስክትተዋወቅ ድረስ ስንገለገልበት የቆየነው  ፍትሕ ነገሥት አንቀጽ 43 (በእንተ ፈታሒ)፤ ዳኞች ሊፈጽሟቸውና ሊጠብቋቸው ከሚገቡ መመሪያዎች አንዱ፣ ዳኛ የእጅ መንሻ መቀበል እንደሌለበት የሚደነግገው ይጠቀሳል፡፡  
 የሀገራችን የፍርድ ቤት ታሪክም ውስጥ ሌላው ቀርቶ ዳኛ በመሆናቸው ሊያከብሯቸውና ሊተገብሯቸው የሚገባቸውን ባህሪያት እንዲሁም በሚጣሱበት ወቅት ስለሚስተናገዱበት አግባብነት በተለያየ ጊዜ የወጡ የዳኞች አስተዳደር የሥነ-ምግባና የዲሲፕሊን ክስ ሥነ-ሥርዓት ደንቦች ነበሩ። በቅርቡም ተሻሽሎ በሥራ ላይ የዋለም አለ። ሆኖም ከላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጹት ደረጃ በዳኞች በኩል ከባድ የሚባሉ ጥሰቶች እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ፍርድ በመደለያና በአማላጅ የሚሰጥ ከሆነ፣ ማኅበረሰቡም ይህን መንገድ አምኖ ከተንቀሳቀሰ አገር የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ትገባለች፡፡  

በመጨረሻም…
ዳኞች የዳኝነት ነጻነት ተከብሮ ሥራቸውን ካከናወኑ፣ ሕግ በሁሉም ላይ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ዳኞች የሚጠበቅባቸውን ሥነ ሥርዓት ጠብቀው ሥራቸውን ካከናወኑ ሀገር ትዘልቃለች፡፡
 ዳኝነት ጥበቃውም ሆነ ክብሩ ይጠበቅ ዘንድ አዳዲሶቹ  አለቆች እንዲሁም በተለይ በሙያ ውስጥ ያለነው የሕግ ባለሙያዎችም ሆነ ዛሬም ድረስ ፍትህ አገኛለሁ ብሎ  ወደ ተቋማቱ የሚሄደው ማሕበረሰብም በንቃት  መንቀሳቀስ አለብን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው:- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1791 times