Saturday, 04 March 2023 10:53

የፀጥታ ኃይሎች በምኒልክ አደባባይ በተሰበሰቡ ነዋሪዎች ላይ ከመጠን ያለፈ እርምጃ ወስደዋል - ኢሰመኮ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(6 votes)

 ኢትዮጵያ ቅኝ ገዥውን የጣሊያን ጦር ድል የነሳችበትን  ዓመታዊውን የዓድዋ ድል በዓል ለመታደም በምኒልክ አደባባይ በተሰበሰቡ ነዋሪዎች ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች አላስፈላጊና ከፍተኛ ሃይል መጠቀማቸውንና በዚህም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን  /ኢሰመኮ/ አስታወቀ።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በሰላማዊው ህዝብ ላይ  ድብደባ፣ አስለቃሽ ጭስ፣ የፕላስቲክና  እውነተኛ ጥይቶችን መተኮሳቸውንም  ኢሰመኮ ትናንት  ባወጣው መግለጫ አመልክቶ።
ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በምኒልክ አደባባይ የዓድዋ ድል በዓልን ለማክበር በተሰባሰቡ ነዋሪዎች እንዲሁም በቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተክርስቲያን ዓመታዊ የንግስና በዓል እያከበሩ በነበሩ ሰዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች፣ በኃይል አላስፈላጊ እና ከመጠን ያለፈ እርምጃ መውሰዳቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።
በምኒልክ አደባባይ ዋናው ዝግጅት ላይ ሕዝቡ እንዳይታደም ወደ አደባባዩ የሚወስዱት መንገዶች ተዘግተው እንደነበርና እንዳይተላለፍም በፀጥታ ኃይሎች ታግዶ እንደነበር ያመለከተው መግለጫው፤ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በህዝቡ ላይ ከልክ ያለፈ እርምጃ መውሰዳቸውን ጠቁሟል። በመንግስት በተወሰደው አላስፈላጊና ከልክ ያለፈ እርምጃ ሳቢያ  በርካታ ሰዎች በእድሜ የገፉና ሕፃናትም ጭምር ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል ብሏል።  በዚህም ቢያንስ የአንድ ሰው ሕይወት እንደተቀጠፈና፣ በበርካቶችም ላይ  የአካል ጉዳት መድረሱን  አመልክቷል።  በተጨማሪም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ አባሉ እንደሆነ የገለጸው ሚሊዮን ወዳጅ የዓድዋ ድል በዓልን  ለማክበር ወጥቶ  ከመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ መገደሉን ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የፀጥታ ኃይሎች የሕዝብን ደኅንነት መጠበቅና የሁሉንም ሰው ሰብዓዊ መብቶች ማስጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነታቸው መሆን ነበረበት ያለው ኢሰመኮ፤ ሕዝቡ በተለምዶ በየአመቱ  እንደሚያደርገው ምኒልክ አደባባይ እንዲሁም በአቅራቢያው በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በዓሉን ለማክበር በሰላማዊ መልኩ ተሰባስቦ እንደነበርና  በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ከልክ ያለፈ እርምጃ እንደተወሰደበት አመልክቷል።
ድርጊቱን የፈጸሙ የፀጥታ ኃይል አባላት ሊጠየቁ እንደሚገባ ያስታወሰው መግለጫው፤ “የሕግ አስከባሪዎች መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ በበቂ ሁኔታ ሥልጠና ሊሰጣቸው ይገባልም”ብሏል።


Read 1775 times